“ከ219 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮባንድ ዕቃ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን በጀርመን ተራድኦ ድርጅት (GIZ) ስም በሀሰተኛ ሰነድ 4,100 ኪ.ግ 287 ዓይነት ዕቃዎች ሚያዝያ 5 ቀን 2011 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውለዋል”– የገቢዎች ሚኒስትር
ጠቅላላ ግምታዊ ዋጋው 219,368,600 ብር የሆነ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ዕቃ በዲፕሎማቲክ የቀረጥ ነፃ መብት ሽፋን ወደ ሀገር ሊገባ ሲል ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በዛሬው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በጀርመን ተራድኦ ድርጅት (GIZ) ስም በሀሰተኛ ሰነድ 4100 ኪ.ግ 287 ዓይነት ዕቃዎች ሚያዝያ 5 ቀን 2011 ዓ.ም በቁጥጥር መዋሉን ገልፀዋል፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ውስጥ 118,440,000 ብር የሚገመተው ካኖን ካሜራዎች ሲሆኑ 52,362,200 ብር የሚገመተው የስማርት ስልኮች ስክሪኖች ናቸው፡፡ ቀሪው የተለያዩ የተሽከርካሪዎች መለዋወጫዎች፣ መድሃኒት፣ ፕሮጀክተር፣ የብር ጌጣጌጥ እና ልዩ ልዩ ኬብሎች ናቸው፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያረጋገጠው 410 ኪ.ግ ሲሆን ቀሪው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስም በተሰራ ሀሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ነው የኮንትሮባንድ ወንጀሉ የተፈፀመው፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሶስት የጀርምን ተራድኦ ድርጅት ሰራተኞች እና ሁለት የዘራይደር የጉምሩክ አስተላላፊ ድርጅት ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ውለው የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ክፍል ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር
