ሐራ ዘተዋሕዶ

April 24, 2019 L

pat banned gen mgr0

***

Bete Kihnet Logo

የሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንን የሥራ አስፈጻሚነት እና የአስተዳደር ተግባር በማዕከል ደረጃ የሚያከናውነው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ አራት የመምሪያ እና የድርጅት ዋና ሓላፊዎች ዝውውር አደረገ፡፡

በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ፣ ከትላንት በስቲያ ሰኞ፣ ሚያዝያ 14 ቀን 2011 ዓ.ም. የሓላፊዎች ዝውውር የተደረገባቸው፥ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ፣ የቅርስ ጥበቃ እና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ፣ የበጀት እና ሒሳብ መምሪያ፣ የብዙኀን መገናኛ አገልግሎት ድርጅት እና የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደር እና ልማት ድርጅት ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት የቅርስ ጥበቃ እና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ዋና ሓላፊ መጋቤ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ ወደ ስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የተዛወሩ ሲኾን፣ የመምሪያው ሓላፊ የነበሩት መልአከ ብርሃን ፍሥሓ ጌታነህ የበጀት እና ሒሳብ መምሪያ ዋና ሓላፊ ኾነዋል፡፡

megabe-selam-kesis-solomon-tolcha

መጋቤ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ

በሥነ መለኰት፣ በካውንስሊንግ፣ በሕግ እና በቱሪዝም ማኔጅመንት ዲፕሎማዎችና የመጀመሪያ ዲግሪ ያሏቸውና በቅርስ ጥበቃ በርካታ ሥልጠናዎችን የወሰዱት መጋቤ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተለያዩ አድባራት፣ በጸሐፊነት እና በስብከተ ወንጌል ሓላፊነት ሠርተዋል፡፡ በቅርሳ ቅርስ መምሪያው በዋና ሓላፊነት በቆዩባቸው ያለፉት ስድስት ዓመታት፣ በላሊበላ ቤተ ሩፋኤል – ቤተ ገብርኤል እና ቤተ ጎልጎታ – ቤተ ሚካኤል ጥገናዎች፣ በዩኔስኮ የመስቀል – ደመራ በዓል ምዝገባ እና የበዓለ ጥምቀት ምዝገባ ሰነድ ዝግጅት፤ ለስድስት ወራት የተዘጋውን የአዲስ ዓለም ደብረ ጽብረ ቅድስት ማርያም ሙዝየም አስከፍቶ ለእይታ በማብቃት፣ የእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት እና የምስካየ ኅዙናን መድኀኔዓለም ገዳማትን ሙዝየሞች በማደራጀት እንዲሁም በልዩ ልዩ ቅርሶች ማስመለስና የሕገ ዝውውር ቁጥጥር በርካታ ተግባራትን ማከናወናቸው ተገልጿል፤ በሎንዶን ሙዝየም የሚገኙና የእንግሊዝ ፓርላማ ይኹንታን እየጠበቁ ያሉ 11 ታቦታትን ለማስመለስ፣ በመንግሥታቱ በተደረሰው ስምምነት መሠረት፣ ከፍጻሜ ለማድረስ የበኩላቸውን ጥረት በማድረግም ላይ ነበሩ፡፡

ወደ በጀት እና ሒሳብ መምሪያ የተዛወሩት የአቋቋም ዐዋቂው መልአከ ብርሃን ፍሥሓ ጌታነህ፣ በአካውንቲንግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ሲኾን፣ በሞያው ቀደም ሲል የሕፃናት እና ቤተሰብ ጉዳይን ጨምሮ በተለያዩ ድርጅቶች እንደሠሩበት ተጠቅሷል፡፡ ላለፉት 8 ዓመታት መምሪያውን በብቃት የመሩት የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ወ/ሮ ጽጌሬዳ ዓለሙ፣ ወደ ቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ተዛውረው በቁጥጥር ክፍል ሓላፊነት ተመድበዋል፡፡

የጠቅላይ ጽ/ቤቱን አሠራር ለማሻሻል በጥቅምት ወር 2003 ዓ.ም. ከውጭ ተመድበው ከነበሩት አራት ከፍተኛ ባለሞያዎች አንዱ የኾኑት ወ/ሮ ጽጌሬዳ፣ የሒሳብ አያያዙን ለረጅም ጊዜ ከተሠራበት ኋላቀር የነጠላ አመዘጋገብ ወደ ኹለትዮሽ ሥርዓት በማዘመንና ሞዴላሞዴሎችን ከዚኹ አንጻር በማሻሻል ለኦዲት አመቺ እንዲኾኑ አድርገዋል፤ በየመምሪያዎቹ ሲንቀሳቀስ የነበረውን የበጀት አጠቃቀም ማዕከላዊ በማድረግ፣ ከምዝበራና ብክነት ጠብቀዋል፤ የመምሪያውንና የልዩ ልዩ አህጉረ ስብከት ሠራተኞችን በሥልጠናዎች በማሳተፍ አብቅተዋል፤ ከ2003 እስከ 2005 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሔደው የውጭ ኦዲተር ምርመራ፣ “ተቀባይነት የሌለው እና ሞያዊ አስተያየት ለመስጠት የማያስችል” (Non audit-able/Disclaimer) ተብሎ የነበረው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሒሳብና ንብረት አያያዝ በእጅጉ ተሻሽሎ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ እየተካሔደ ለሚገኘው ኦዲት ምቹ ኹኔታ ፈጥረዋል፤ አህጉረ ስብከትም በምሳሌነት የሚከተሉት ኾኗል፡፡

የውጤታማዋ አካውንታንት ወ/ሮ ጽጌሬዳ ዓለሙ ዝውውር፣ በኪራይ የሚያስተዳድራቸው ቤቶችና ሕንፃዎች እየተበራከቱና እየገዘፉ ለመጡት ድርጅት ተደማሪ አቅም እንደሚፈጥርለት ይታመናል፡፡ የቀድሞው የድርጅቱ ቁጥጥር ወ/ሮ ጽጌ መንገሻ ደግሞ፣ ወደ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተዛውረው በቁጥጥር ሓላፊነት ተመድበዋል፡፡

የኢኦተቤ – ቴቪ ጣቢያ ሥርጭቱን ከመጀመሩ በፊት በነበረው ቅድመ ዝግጅትና ሥርጭቱን ከጀመረበት ካለፈው ሐምሌ 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የብዙኀን መገናኛ አገልግሎት ድርጅቱን በዋና ሥራ አስኪያጅነት የመሩት መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፣ ወደ ውጭ ጉዳይ መምሪያ ተዛውረው በዋና ሓላፊነት ተመድበዋል፡፡ የብዙኀን መገናኛ አገልግሎት ድርጅት ቦርድ፣ በቀጣዩ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ፣ የቴሌቪዥን ጣቢያውን በዋና ሥራ አስኪያጅት የሚመራ ባለሞያ ሓላፊ አወዳድሮ እንደሚቀጥር ተጠቁሟል፤ እስከዚያው ድረስ መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል የውጭ ጉዳይ መምሪያውን በዋናነት እንደያዙ ሥራውን በጊዜያዊነት እየመሩት እንደሚቆዩ ታውቋል፡፡

eotc-tv4

መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል

በባለሞያዎችና በሥራ መሣሪያዎች እየተጠናከረ የሚገኘው የኢኦተቤ-ቴቪ፣ በመሪ ዕቅድ የታገዘ አስተዳደራዊ ለውጥ ለማካሔድ እየተዘጋጀች ለምትገኘው ቤተ ክርስቲያናችን ዓይነተኛና ትክክለኛ ድምፅ ለመኾን ይችል ዘንድ፣ አንጻራዊ ተቋማዊ ነፃነቱን አስከብሮ በቅንጅትና በብቃት የሚመራው ቀናዒና ትጉህ ኦርቶዶክሳዊ ሓላፊ ይሻል፡፡ በአባቶች ዕርቀ ሰላም የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ አስተዳደራዊ አንድነት በተመለሰበት ኹኔታ፣ የውጭ ጉዳይ መምሪያው አሠራር፣ የወቅቱን ሉላዊ ዕድሎች የሚጠቀምና ተግዳሮቶቹን የሚቋቋም መኾን ይኖርበታል፡፡ በዚህ ረገድ ለመምሪያው አዲስ ያልኾኑት መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፣ በሥነ መለኰት፣ በአገራዊና ዓለም አቀፋዊ ብሂላት ጥናት እንዲሁም በቋንቋዎች ክህሎት ያካበቱት ልምድ፣ ተቋሙን እንደሚለውጠውና አገልግሎቱን በአግባቡ እንደሚያራምደው ተስፋ ይደረጋል፡፡

ከውጭ ጉዳይ መምሪያው፣ በድክመት ተገምግሞ እና ባለመታዘዝ አቤቱታ ቀርቦበት በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ ሰሞኑን ከሓላፊነት የተነሣው ‘አባ’ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ፣ ወደ ቅርስ ጥበቃ እና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ተዛውሮ በዋና ሓላፊነት ተመድቧል፡፡ ከሚታወቅበት የኑፋቄ ዝንባሌና ከፈጸማቸው አሻጥሮች አንጻር፣ ሹመት ሳይኾን ተጠያቂነትና ንሥሓ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ኦርቶዶክሳዊነትን እየሳነሰ ፕሮቴስታንታዊነትን እያነጋገሰ ለሚሸቃቅጥ ግለሰብ፣ ቅርሳቅርስ መምሪያውን በዋና በሓላፊነት መስጠቱ በማንኛውም መመዘኛ ቢታይ ሥላቅ ነው፡፡ የመምሪያው ባልደረቦች ጥንቃቄ ያድርጉበት፤ ጠቅላይ ጽ/ቤቱም የቅርብ ክትትል በማካሔድ ሓላፊነቱን ይውሰድ!!

በሕገ ቤተ ክርስቲያንና በቃለ ዐዋዲ ደንቡ ድንጋጌዎች፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቱ፣ የሓላፊዎች ዝውውርና ዕድገት የሚያደርገው፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ተጠንቶ ለቅዱስ ፓትርያርኩ ሲቀርብና ቅዱስነታቸው ሲስማሙበት ነው፡፡ በዚህም መሠረት፣ ከትላንት በስቲያ ሰኞ የተደረገው የመምሪያዎች እና የድርጅቶች ሓላፊዎች ዝውውር፣ በፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እና በጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ምክክር የተፈጸመ መኾኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ይህም በውጭ ፖለቲከኞች ግፊትና በውስጥ አድርባዮች ሤራ፣ በቅዱስ ፓትርያርኩ እና በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ መካከል ተካርሮና ሻክሮ የሰነበተው ግንኙነት ተወግዶ መግባባት መስፈኑን ያመላክታል፤ ተብሏል፤ በአንዳች ሰበብ እንዲያገረሽ ካልተፈለገ በቀር!


ቤተ ክህነት፥ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ነው፡፡ የአስተዳደሩ ማዕከልና ርእስ ደግሞ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ነው፡፡ የሕግ አውጪውን የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔዎችና መመሪያዎች የሚያስፈጽምባቸውና አስተዳደሩን የሚመራባቸው፥ 16 መምሪያዎች፣ 5 ድርጅቶች እና 3 መንፈሳዊ ኮሌጆች በሥሩ ያስተባብራል፤ ይቆጣጠራል፡፡

መምሪያዎቹ፡- የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ፣ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ፣ የትምህርት እና ማሠልጠኛ፣ የካህናት አስተዳደር፣ የሊቃውንት ጉባኤ፣ የገዳማት አስተዳደር፣ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ፣ የአስተዳደር፣ የዕቅድ እና ልማት፣ የበጀት እና ሒሳብ፣ የቁጥጥር አገልግሎት፣ የቅርስ ጥበቃ እና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር፣ የውጭ ጉዳይ፣ የሕግ አገልግሎት፣ የመንፈሳዊ ፍ/ቤት እና የተቸገሩ አብያተ ክርስቲያን ርዳታ ማስተባበሪያ ናቸው፡፡ ድርጅቶቹ፡- የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፣ የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ የአልባሳት ማዳራጃ እና ምርት ሥርጭት፣ የጎፋ ጥበበ እድ ማሠልጠኛ፣ የቁሉቢ ቅዱስ ገብርኤል ንዋየ ቅዱሳት ማደራጃ፣ የቤቶች እና ሕንፃዎች አስተዳደር እና ልማት ናቸው፡፡ መንፈሳውያን ኮሌጆቹም፥ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ እና የመቐለ ቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ናቸው፡፡