April 24, 2019

ቦይንግ በ2019 የመጀመሪያ ሶስት ወራት 737 ማክስ አውሮፕላኖቹን ማስረከብ ባለመቻሉ የትርፍ መጠኑ 20 በመቶ መቀነሱን ይፋ አደረገ።

የአሜሪካ አውሮፕላን አምራች ኩባንያው በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት ያቀደውን ያክል የትርፍ መጠን ማሳካት እንደማይችልም ከወዲሁ ይፋ አስታውቋል።

የቦይንግ ምርት የሆኑት 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዢያ ያደረሱትን አደጋ ተከትሎ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች በረራ እንዳያደርጉ መታገዳቸው ይታወሳል።

ቦይንግ ከአውሮፕላኖቹ ጋር በተያያዘ ጥርት ያለ ሙሉ መረጃ ሲኖረኝ የገበያ ድርሻዬን በተመለከተ መረጃዎችን ይፋ አደርጋለሁ ብሏል። ቦይንግ በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዥያ ለደረሱት አደጋዎች ምክንያት ነው የተባለውን የበረራ መቆጣጠሪያ ስርዓት አሻሽላለሁ ቢልም ማሻሻያው እስኪደረግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች አሁንም ከሰማይ እንዲርቁ ተደርገዋል።

በሁለቱ የአውሮፕላን አደጋዎች 346 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። የኢቲ 302 የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት መውጣቱን ተከትሎ የቦይንግ ከፍተኛ ኃላፊዎች የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን እንደሚቀበሉት መግለጻቸውም የሚታወስ ነው።

የቦይንግ ኩባንያ ሊቀመንበር፣ ፕሬዚደንት እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴኒስ ሚሌንበርግ ” . . . የኢቲ 302 የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት እንዳሳየው እንደ ከዚህ ቀደሙ [ላየን ኤየር] ኤምካስ የተሰኘው ሶፍትዌር በተሳሳተ መረጃ ‘አክቲቬትድ’ (ሥራውን እንዲጀምር) ሆኖ ነበር” ማለታቸው ይታወሳል።

ቦይንግ በ737 ማክስ አውሮፕላኖቹ ኪሳራ ቢገጥመውም፤ ለጦር አገልግሎት ከሚውሉ ምርቶቹ ግን ትርፍ ማግኘት መቀጠሉ ተነግሯል።
► መረጃ ፎረም – JOIN US