April 24, 2019

በቻይና ጅብ ተከታታይ ፅሁፍ አራተኛ ክፍል ቻይና ለጅቡቲ ወደብ 1 ቢሊዮን ዶላር ብድር በመስጠት በዕዳ ጫና ሲጥ… እንዳደረገቻት ገልጩያለሁ። የዕዳ ጫናው ጅቡቲን አስጨንቋት ወደላይ ያስመልሳት ጀምሯል። በዚህ ምክንያት ሉዓላዊ መሬቷን ለመጣ ሀገር ሁሉ የጦር ሰፈር እንዲገነባበት ማከራየት እያከራየች ነው። ይህን በመጠቀም ቻይና ከሀገሯው ውጪ የመጀመሪያውን የጦር ሰፈር በጅቡቲ አቋቁማለች። በዚህ አመት የየካቲት ወር ላይ ደግሞ ጅቡቲ ወደቡን ለማስተዳደር ከዱባይ ኤሜሬት ኩባንያ ጋር የገባችውን ውል በማፍረስ ለቻይና መስጠቷ ተገልጿል። በዚህ ምክንያት ዱባይ ኤሜሬት ጅቡቲን በለንደን ፍርድ ቤት ለመገተር ጥድፊያ ላይ ናት።

በሌላ በኩል የህወሓት/ኢህአዴግ ሊቀመንበር ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ህልፈትን ተከትሎ ቻይና እ.አ.አ. በ2013 (2005) ዓ.ም ብቻ ለኢትዮጵያ 6.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ሰጥታለች። ቻይና እ.አ.አ. ከ2000 2014 ዓ.ም ለኢትዮጵያ የሰጠችው ብድር በጠቅላላ 12.3 ቢሊዮን ዶላር ነው። ከዚህ ውስጥ ግን ከግማሽ በላይ የሚሆነው (6.533 ቢሊዮን ዶላር) ብደር የተሰጠው በ2013 (2005) ዓ.ም ብቻ ነው። ከዚህ አመት ጀምሮ ባሉት አራት አመታት (ከ2014 – 2017) ውስጥ የኢትዮጵያ የዕዳ ጫና በ13% አሻቅቦ 59% ላይ ደርሷል። በዕዳ ጫና ምክንያት በተፈጠረ የውጪ ምንዛሬ እጥረት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ቁርጠት ይዞታል። በዚህ አመት የመጋቢት ወር ላይ ኢትዮጵያም እንደ ጅቡቲ ሊያሰመልሳት እያጥወለወላት ነበር።

“የቻይና ጅብ” ኢትዮጵያ አጥወልውሏት እስክትወድቅ በጉጉት እየጠበቀ ባለበት የመጋቢት ወር ላይ የአሜሪካ ምክር ቤት የጦር አገልግሎት ዋና ኮሚቴ (House Armed Service Committee) ተቀምጧል። የኮሚቴው አባላት፤ ጅቡቲ እንዴትና ለምን “በቻይና ጅብ” ተበላች፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍረካ ሀገራትን ቀረጣጥፎ እንዳይበላቸው የአሜሪካ መንግስት ምን ማድረግ አለበት? “የቻይና ጅብን” ለመግታት አሜሪካ ምን ዓይነት ስትራቴጂካዊ ስልት መከተል አለባት? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በአፍሪካ የአሜሪካ ኮማንድ (U.S. Africa Command) ዋና አዛዥ የሆኑትን ጄኔራል “Thomas D. Waldhauser” ላይ እያከታተሉ ያዘንቡባቸዋል። ጄኔራሉ ደግሞ የዓይን እማኝነታቸውን በተረጋጋ መንፈስ ይገልፃሉ።

በዚህ አመት የመጋቢት ወር ላይ በአፍሪካ የአሜሪካ ኮማንድ ዋና አዛዥ ጄኔራል “Thomas D. Waldhauser” ለአሜሪካ ምክር ቤት የጦር አገልግሎት ዋና ኮሚቴ (House Armed Service Committee) አባለት የሰጡት የዓይን-እማኝነት መረጃ በጉዳዩ ዙሪያ የሀገሪቱ መንግስት ምን አይነት አቋም እንዳለው ለማወቅ ያስችላል። በመሆኑም የኮሚቴው አበላት ቻይና በምስራቅ አፍሪካ እያደረገችው ስላለው እንቅስቃሴ እና በቀጣይ መወሰድ ሰላለበት እርምጃን አስመልክቶ ከጄኔራል “Thomas D. Waldhauser” ጋር ያደረጉትን ውይይት ለብቻው ለይተን በማውጣት እንደሚከተለው አቅርበናል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በዶላር እጥረት ስትቃትት፣ በህዝባዊ አመፅ ስታቃስት ቻይና ጅቡቲ ቁጭ ብላ እየተመለከተች። ኢትዮጵያ ከምትውጠው በላይ የጎረሰችው ዕዳ አስጨንቋት ኢኮኖሚያዋ የዶላር ቁርጠት ይዞታል። የገቢና ወጪ ንግዷ የሚተላለፍበት ደም-ስር በቻይና ቁጥጥር ስር ውሏል። አንዴ ተዝለፈልፋ ከወደቀች የቻይና ጅብ ዘልሎ ከላይ ይከመርባታል። ዱባይ ኤሜሬት አንዴ የኤርትራን አሰብ ወደብ፣ ሌላ ግዜ የፑንትላንድን ወደብ ለማልማትና ለመጠቀም ወዲያና ወዲህ ትራወጣለች

የአሜሪካ ምክር ቤት የጦር ጉዳዮች ኮሚቴ በአፍሪካ የአሜሪካ ጦር አዛዥ ጋር ከተወያየ በኋላ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን ከቻይና ጅብ ለመታደግ ወስኗል። የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባልደረቦች ወደ አፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ መመላለስ ጀምረዋል። በዚህ አመት የመጋቢት ወር ላይ የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት አፍሪካዊያን ከቻይና የዕዳ ወጥመድ ራሳቸውን እንዲጠብቁ አስጠንቅቀው ሄደዋል፡፡ በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳይ ሃላፊዎች ወደ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ሳውዲ አረቢያ እና ዱባይ ኤሜሬት መመላለስ ቀጥለዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካን ኢምባሲ ባልተለመደ መልኩ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ በይፋ አቋሙን ማንፀባረቅ ጀምሯል። በተለይ በየካቲት ወር የፀደቀውን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በይፋ ተቃውሟል። በየካቲት ወር መጨረሻ አከባቢ ደግሞ የህወሓቶችን አቋም በመተቸት ለእነ ለማ መገርሳ ድጋፉን ገልጿል፡፡ የቀድሞ ጠ/ሚ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ስልጣን እንደሚለቁ ማሳወቃቸውን ተከትሎ የአሜሪካ ዲፕሎማቶችና ምሁራን አንጋፋ የህወሓት ባለስልጣናትን በይፋ “kleptocrats” ብለው እስከመዝለፍ ደረሱ፡፡ በአንፃሩ ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር መሆን አለባቸው ሲሉ ድጋፋቸው ገለፁ፡፡ በእርግጥ “የአሜሪካኖቹ ተግባር ህወሓቶችን መግፍት ነው ወይስ መፈንቅለ መንግስት ነው?” የሚለውን በቀጣይ ክፍል እንመለከታለን፡፡

“የቻይና ጅብ” ክፍል 3፡ የኢትዮጵያ የውጪ ዕዳ በ1% ከጨመረ ባቡር መስመሩ ለቻይና ተላልፎ ይሰጥ ነበር!

April 24, 2019

ስዩም ተሾመ

ከታች በምስሉ ላይ እንደሚታየው ያለባቸው የዕዳ ጫና በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ከኢኮኖሚ አልፎ በሀገራቱ ሉዓላዊነት ላይ የህልውና አደጋ ተጋርጧል። ትላንት ባወጣሁት ሁለተኛ ክፍል የቻይና ጅብ ሲርላንካን እንዴት አድርጎ እንደበላት ተመልክተናል። እንደ ፓኪስታን (Pakistan)፣ ኔፓል (Nepal) እና ማይንማር (Myanmar) ያሉ ሀገራት ደግሞ እንደ ሲሪላንካ ሉዓላዊነታቸውን ላለማስደፈር የቻይና መንግስት የሚሰጠውን ፈንድና ብድር አንቀበልም ብለዋል። በእነዚህ ሦስት ሀገራት በ20 ቢሊዮን ዶላር ሦስት ሃይል ማመንጫ ግድብ ለመስራት የነበረውን ዕቅድ ውድቅ አድርገውታል። ሀገራቱ ቻይና በምትሰጠው ብድር ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ የገቡ ሲሆን የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶቹን ውድቅ ያደረጉበት ምክንያት አንድና ተመሳሳይ ነው።

ፓኪስታንን መሃል ለመሃል አቋርጦ የሚሄደውን የንግድ መስመር (ኮሪዶር) 44 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል። አብዛኛው ብር ከቻይና መንግስት ፈንድና ብድር የተገኘ ሲሆን ፓኪስታንን ለከፍተኛ የዕዳ ጫና ዳርጓታል። የቻይና መንግስት ይህንን ምክንያት በማድረግ አዲስ ለሚገነባው የሃይል ማመንጫ የሚሰጠው የ14 ቢሊዮን ዶላር ብድር ዋስትና እንዲሆነው የሚገነባውን ግድብ ጨምሮ አንድ ሌላ ነባር የሃይል ማመንጫ ግድብን በማስያዣነት እንዲሰጠው ይጠይቃል። የፓኪስታን መሪዎችን ይህን በመቃወም አዲሱን ግድብ ለማስራት የነበራቸውን ዕቅድ ውድቅ ያደርጉታል።

የኔፓልና ማይንማር መንግስታት ደግሞ የሃይል ማመንጫውን ግንባታ የሚያከናውኑት የቻይና ኩባንያዎች አላስፈላጊ ጥቅምና ሙስና በመጠየቃቸው እንደሆነ ጠቁመዋል። ስለዚህ የቻይና መንግስት በሀር መንገድ ፕሮጀክት በሚሰጠው ብድር አማካኝነት በከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ የወደቁ ሀገራትን እያደነ፤ እንደ ሲሪላንካ ሉዓላዊ መሬታቸውን ይቆጣጠራል፣ እንደ ፓኪስታን የሀገራቱን የተፈጥሮ ሃብት ለመቆጣጠር ይሞክራል፣ እንደ ኔፓልና ማይንማር ደግሞ የቻይና ኩባኒያዎች በሙስና እና ሕገ-ወጥ ተግባራት ይሰማራሉ።

ጅቡቲ ከስሪላንካ 4000 ከ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች። ልክ እንደ ቀድሞ የስሪላንካ መሪ ጅቡቲም አምባገነን የሆነ መሪ አላት። ከታች ባለው ምስል ላይ እንደሚታየው በቻይና የሀር መንገድ ዕቅድ መሰረት ከስሪላንካ የተነሱ ትላልቅ የንግድ መርከቦች በኬኒያ የላሙ (Lamu) ወደብ በኩል አድርጎ ወደ ጅቡቲ ይመጣል። በመሆኑም ከቻይና በተገኘ ብድር ጅቡቲና ኬኒያ ላይ ትላልቅ ወደቦች ተገንብተዋል። ከሁሉም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በተሻለ ኬኒያ ዴሞክራሲያዊ ናት። ምንም እንኳን ኬኒያ ውስጥ ከፍተኛ ሙስና ቢኖርም የሀገሪቱ መንግስት ሥራና አሰራር ከየትኛውም የምስራቅ አፍሪካ የተሻለ ግልፅነትና ተጠያቂነት አለው። ለዚህ ደግሞ በቅርቡ የተካሄደውን ፕረዘዳንታዊ ምርጫ እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል።

Doraleh Multipurpose Port, Djbouti

አሁን ላይ በስሪላንካ አፉን ከፍቶ የሚውለውን የ“Hambantota” ወደብ እና የጅቡቲን “Doraleh Multipurpose Port” የገነባው “China Merchants Ports Holding Company – CMPort” በመባል የሚታወቀው የቻይና ኩባንያ ነው። የቻይና እና ጅቡቲ መንግስት በጥምረት የሰሩት የዶራሌህ (Doraleh) ወደብ በጠቅላላ 3.4 ቢሊዮን ዶላር የፈጀ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ወጪ የተሸፈነው ከቻይና መንግስት በተሰጠ ብድር ነው። በተመሳሳይ የቻይና መንግስት ለኬኒያ ከፍተኛ ብድር ያበደረ ቢሆንም እንደ ጅቡቲ የሉዓላዊነት አደጋ አልጋረጠም።

የጅቡቲ የብድር መጠን በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን የሀር መንገድ ከሚያልፍባቸው 68 የዓለም ሀገራት በተለየ የሀገሪቱ አመታዊ የምርት መጠን 88% ሆኗል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 90% የሚሆነው ብድር የተሰጠው ከቻይና ነው። አንድ ሀገር ያለበት የውጪ ብድር መጠን ከ50% ላይ ከሆነ የሀገሪቱ ተጨማሪ ብድር የማግኘት ዕድል በጣም አነስተኛ ይሆናል። የብድር መጠኑ ከ60% በላይ ሲሆን ግን የዕዳ ጫናው በሀገሪቱ ሉዓላዊነት ላይ አደጋ ይጋርጣል። የጅቡቲ የብድር መጠን ከዚህ አልፎ 88% መድረሱና ከዚህ ውስጥ 90% ከቻይና መንግስት የተገኘ መሆኑ ያለ ምንም ጥርጥር የሀገሪቱ ሉዓላዊነት ተገፍፏል ብሎ መደምደም ይቻላል።

ነገር ግን የጅቡቲ ዋና የገቢ ምንጩ ኢትዮጵያ ናት። ከወደብ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ በአመት ለጅቡቲ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ትከፍላለች። ስለዚህ ጅቡቲ ውስጥ ትልቅ ወደብ ከመገንባት በተጨማሪ የኢትዮጵያን የውጪና ገቢ ንግድ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ የሚያስችል የትራንስፖርት መስመር መዘርጋት አለበት።

በዚህ መሰረት ከቻይና ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ በተገኘ 3 ቢሊዮን ዶላር ብድር ከፍተኛ በሚባል የወለድ መጠን የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ተዘረጋ። የቻይና መንግስት ከሁሉም ሀገራት በተለየ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ብድር ሰጠ። በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ የብድር መጠን ከአመታዊ የምርት መጠን አንፃር ከአራት አመት በፊት ከነበረበት 46.8% ተነስቶ 59% ደረሰ። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የኢትዮጵያ የብድር ጫና ከፍተኛ “High” ደረጃ ላይ መድረሱን አስታወቅ። ከዚህ በኋላ አንድ ፐርሰንት ጨምሮ 60% ከሆነ የዕዳ ጫናው ኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ይጥለዋል።

በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትርፋማ አለመሆን እና የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር ሥራ ከመጀመሩ ሁለት አመታት ቀደም ብሎ የብድር ዕዳው እንዲከፈል መደረጉ ዓይነተኛ ማሳያ ነው። በቻይና ኩባንያ የሚሰራ የባቡር ሃዲድ ተጠናቅቆ ስራ ከመጀመሩ ሁለት አመታት ቀደም ብሎ ከቻይና ባንክ የተገኘ ብድር እንዲከፈል የሚያደርግ አሰራር ኢትዮጵያን የዕዳ ጫና ውስጥ ለመክተት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ዓላማ ሊኖረው አይችልም።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከጅቡቲ አንፃር በጣም ትልቅ ስለሆነ እንደ ምንም ተንገጫግጮ 59% ላይ ቆሟል። አንድ ፐርሰንት ተጨማሪ ብድር ቢወስድ ከ60% የዕዳ ጫና ቀይ መስመር ያልፋል፡፡ ልክ በፓኪስታን፣ ኔፓልና ማይነማር እንደጠየቀችው፣ በስሪላንካና ጅቡቲ በተግባር እንዳደረገችው የቻይና መንግስት የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር፣ የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር መስመር ወይም የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መሬት ወይም የተፈጥሮ ሃብት ለሰጠችው ብድር በማስያዣነት እንዲሰጣት መጠየቋ አይቀርም ነበር። ባለፉት ሦስት አመታት በሀገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እጥረት የተከሰተው ከዚህ ጋር በተያያዘ ነው። “የቻይና ጅብ” ኢትዮጵያን እንደ የፍየል ቆለጥ “አሁን ከአሁን ወደቀች” እያለ አፉን ክፈቶ እየተጠባበቀ ሳለ ዶ/ር አብይ “ዱብ…” አለ።

“የቻይና ጅብ” ክፍል 2፡ በብድር ያነክሳል! በዕዳ ጫና ይነክሳል! በወታደር ይጨርሳል! (ስዩም ተሾመ)

April 24, 2019

ቻይናዎች “አንድ ሀገር መበልፀግ ከፈለገ መንገድ መገንባት አለበት” የሚል አባባል አላቸው። በዚህ መሰረት ሀገሪቱ በየብስና ባህር ላይ “የሀር መንገድ” (Silk Road & Silk Maritime) ለመገንባት አንድ (1) ትሪሊዮን ዶላር በጀት መድባለች። ይህ የሀር መስመር በሚያልፍባቸው 68 ሀገራት ውስጥ 900 የሚሆኑ ትላልቅ የአስፋልት መንገዶች፣ የባቡር መስመሮች፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ የባህር ወደቦች፣ የመብራት ማመንጫ ግድቦችና ማሰራጫዎች፣ የጋዝ (ነዳጅ) ማስተላለፊያ ትቦዎች ለመገንባት ወይም ለመዘርጋት የተመደበ ከፍተኛ በጀት ነው።

ይህ አንድ ትሪሊዮን ዶላር የሚገኘው ከቻይና ልማት ባንክ (China Development Bank CDB), ከቻይና ኢምፖርት-ኤክስፖርት ባንክ (China Ex-Im Bank)፣ ከኢሲያ መሰረተ-ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ (Asia Infrastructure Investment Bank – AIIB), ከሀር መንገድ ፈንድ (Silk Road Fund-SRF)፣ የቻይና ግንባታ ባንክ (China Construction Bank – CCB)፣ የቻይና ግብርና ባንክ (Agricultural Bank of China – ABC)፣ እንዲሁም ከቻይና መንግስት ኢንቨስትመንት ፈንድ (State owned Investment Fund) እና ከቻይና ግል ባንኮች ናቸው።

በዚህ መልኩ ከሚገኘው ውስጥ የተወሰነው በቻይና መንግስት ድጋፍ ወይም ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (FDI) የሚውል ነው። የተቀረው ግን እንደ ሁኔታው በአነስተኛ ወለድ ወይም በገበያ ላይ ካለው መጠን ትንሽ ዝቅ ባለ የወለድ መጠን በሀር መስመር ላይ ላሉ ሀገራት በብድር መልክ የሚሰጥ ነው። የቻይና መንግስት በድጋፍ መልክ ከገነባቸው ወይም በቀጥታ ኢንቨስት ካደረገባቸው ውስጥ፤ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአፍሪካ ሕብረት ዋና ፅ/ቤት፣ የጥሩነሽ-ቤጂንግ ሆስፒታል፣ እንዲሁም በቻይና መንግስት ድጋፍ የተሰሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ትምህርት ቤቶች እንደ ምሳሌ ይጠቀሳሉ። የተጠቀሱት የመሰረተ ልማት ግንባታ የሚከናወነው በቻይና ድጋፍ ወይም እርዳታ ብቻ ሳይሆን በቻይና ተቋራጭ ድርጅቶች አማካኝነት ነው። በኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ ደግሞ የድርጅቱ አመራር ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹ ሰራተኞች ቻይናዊያን ናቸው።

ሌላው ከቻይና ባንኮች በተገኘ ብድር የሚሰሩ ትላልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች የሚሰጡት ለቻይና ተቋራጭ ድርጅቶች ነው። እነዚህ ተቋራጭ ድርጅቶች ከባለሙያዎች ባለፈ አንዳንዴ የጉልበት ሰራተኞችን ጭምር ከቻይና ያስመጣሉ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ግንባታን እያከናወነ ያለው የቻይና ተቋራጭ ድርጅት (CCCC) ሰራተኞች ከሞላ-ጎደል ሁሉም ቻይናዊያን ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ በትላልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የተሰማሩት የቻይና ተቋራጭ ድርጅቶች የሚጠቀሙት የግንባታ ግብዓቶች በዋናነት ከቻይና ኢንዱስትሪዎች የተገዙ ናቸው።

በመጨረሻም የቻይና መንግስት የሚገነባቸው 900 የሚሆኑ ትላልቅ የአስፋልት መንገዶች፣ የባቡር መስመሮች፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ የባህር ወደቦች፣ የመብራት ማመንጫ ግድቦችና ማሰራጫዎች፣ የጋዝ (ነዳጅ) ማስተላለፊያ ትቦዎች በዋናነት የቻይና የውጪ ንግድን ለማቀላጠፍና ለማስፋፋት ዓላማ ያደረጉ ናቸው። በመሆኑም ከቻይና መንግስት በሚሰጥ ድጋፍና ብድር የሚሰሩት የመሰረተ ልማት አውታሮች በሙሉ የሀገሪቱን የጥሬ ዕቃ ፍላጎት በሟሟላት እና ለኢንዱስትሪ ምርቶች ተጨማሪ ገበያ በማግኘት ላይ ማዕከል ያደረጉ ናቸው።

በዚህ መሰረት የቻይና መንግስት በባህርና የብስ ላይ ለሚገነባው የሀር መስመር ከመደበው አንድ ትሪሊዮን ዶላር ውስጥ አብዛኛው ተመልሶ ወደ ቻይና ይሄዳል። አንደኛ፡- በቻይና ተቋራጭ ድርጅቶች የግብዓት ግዢ፣ ለሰራተኞች በሚከፍሉት ደሞወዝ፣ ለቻይና መንግስት በሚከፍሉት ግብር እና ከሥራው በሚያገኙት ትርፍ፤ ሁለተኛ፡- ለቻይና ባንኮች በሚከፈለው ብድርና ወለድ አማካኝነት ዶላሩ ተመልሶ ወደ ቻይና ይሄዳል። በሌላ በኩል የቻይና ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃዎችን በአንስተኛ ዋጋ ስለሚገዙ የምርት ወጪያቸው ይቀንሳል እና ለምርቶቻቸው ደግሞ ተጨማሪ ገበያ ያገኛሉ። በዚህ ምክንያት ቻይና ከውጪ ንግድ የምታገኘው ገቢ በብዙ ቢሊዮን ዶላር ይጨምራል።

ከላይ በተገለጸው መሰረት ቻይና ለሀር የንግድ መስመር ግንባታ የመደበችው አንድ ትሪሊዮን ዶላር ከመመለሱም በላይ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በፍጥነት እንዲያድግ ያስችለዋል። በአንፃሩ የሀር መንገድ ፕሮጀክት አካል የሆኑት ሀገራት ደግሞ ትላልቅ አስፋልት መንገዶች፣ የባቡር መስመሮች፣ የአየር ማረፊያዎች፣ የመብራት ማመንጫ ግድቦች፣ የነዳጅ ማስተላለፊያ ትቦዎች እና የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት አውታሮች ይኖሯቸዋል። ሁለተኛ እነዚህን መሰረተ ልማቶች ለመገንባት ከቻይና መንግስት ባንኮች የወሰዱት ብዙ ቢሊዮን ዶላር ብድርና ወለድ ይከመርባቸዋል።

በመሰረቱ ታዳጊ ሀገራት ከፍተኛ የሆነ የመሰረተ ልማት አገልግሎት እጥረት አለባቸው። በመሆኑም ከቻይና መንግስትና ባንኮች ባገኙት ብድር የገነቧቸው መሰረተ ልማቶች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ከማቀላጠፍ አንፃር አዋጭ ከሆኑ ሀገራቱ የዕዳ ጫና ውስጥ አይገቡም። በብድር የተገነቡት የመሰረተ ልማት አውታሮች አዋጭ ካልሆኑ ግን ሀገራቱ የዕዳ ጫና ውስጥ ይወድቃሉ። የመሰረተ ልማት አውታሮች አዋጭነት እንዲኖራቸው የኢንዱስትሪዎች ምርትና ምርታማነት እና የሀገሪቱ የውጪ ንግድን ማደግ አለበት።

በሀር መንገድ ፕሮጀክት የሚሰጠው ብድርና ድጋፍ ከቻይና ጋር የሚደረገውን ንግድ ለማቀላጠፍ ነው። ስለዚህ ሀገራት ከቻይና መንግስት በሚሰጣቸው ፈንድና ብድር አዳዲስ እንዱስትሪዎችን ለመገንባት ወይም ነባር ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት አያገለግልም። በፕሮጀክቱ መሰረት የሚገነቡት የመሰረተ ልማት አውታሮችም ቢሆን የቻይናን የውጪና ገቢ ንግድ ለማሳደግ እንጂ የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ ዓላማ ያደረገ አይደለም። በዚህ ምክንያት የሀገራቱ ምርትና ምርታማነት አያድግም፣ በውጪ ንግዱ ላይ ተጨባጭ ለውጥ አይመጣም። ስለዚህ የሀገራቱ የብድር ወለድ እየጨመረ ሄዶ በዕዳ ጫና ውስጥ ይወድቃሉ።

ከዚህ አንፃር በቻይና የሀር መንገድ ፕሮጀክት ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላት ሲሪላንካ አይነተኛ ማሳያ ነች። በአምባገነንነታቸው የሚታወቁት የቀድሞ የሲሪላንካ ፕረዜዳንት በአብዛኛው በአነስተኛ ብድር ከቻይና መንግስትና ባንኮች 4.8 ቢሊዮን ዶላር ተበድረዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ በ1.8 ቢሊዮን ዶላር በአመት አንድ ሚሊዮን መንገደኞች የሚያስተናግድ የአውሮፕላን ማረፊያ በፕረዘዳንቱ የትውልድ ሰፈር ገነቡ። “Mattala Rajapaksa International Airport” በሚል በአምባገነኑ መሪ ስም የተሰየመው እጅግ ዘመናዊ የሆነ አውሮፕላን ማረፊያ ተመርቆ ሥራ የጀመረው እ.አ.አ. በ2013 ነው።

It was only 10 in the morning but the next arrivals weren’t until the following day. Image: Wade Shepard

ከሦስት አመት በኋላ በአመት አንድ ሚሊዮን መንገደኞች ያስተናግዳል የተባለው አውሮፕላን ማረፊያ በሳምንት አንድ አውሮፕላን ብቻ ማስተናገድ ጀመረ። ምክንያቱም ማረፊያው የተገነባው በፕረዘዳንቱ ልዩ ፍላጎት እንጂ በገበያ አዋጭነቱ አይደለም። በዚህ ምክንያት የአውሮፕላን ማረፊያው በየአመቱ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ አለው። ከቅርብ ግዜ ወዲህ በሳምንት አንድ በረራ እንኳን ማስተናገድ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ብዛት ያላቸው የዱር እንስሳት በአውሮፕላን ማረፊያ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመግባታቸው ነው።

The passenger terminal of Mattala Rajapaksa International Airport. Image: Wade Shepard

አስገራሚው ነገር በአውሮፕላን ማረፊያው ከገቡት የዱር እንስሳት ውስጥ አንዱ ዝሆን ነው። በዚህ መልኩ ያለ በቂ የአዋጭነት ጥናት በ1.8 ቢሊዮን ዶላር የተገነባው የአውሮፕላን ማረፊያ በመጨረሻ የዝሆን ማረፊያ ለመሆን በቅቷል። ከአውሮፕላን ማረፊያው በተጨማሪ ወደዚያ የሚወስደው ትልቅ አስፋልት መንገድ ጭምር ባዶ ነው። ከዚያ በተጨማሪ በሲሪላንካ ዋና ከተማ የተገነባው የኮሎምቦ ወደብ ከቻይና መንግስት በተገኘ ብድር የተሰራ ነው። ይህም ወደብ ልክ እንደ አውሮፕላን ማረፊያው ባዶ ነው።

The virtually empty road leading to the virtually empty airport. Image: Wade Shepard

ከላይ በተገለጸው መሰረት ስሪላንካ ከቻይና መንግስት በተገኘ ብድር የገነባቻቸው መሰረተ ልማቶች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ እሴት የሚጨምሩ አይደሉም። በዚህ ምክንያት ሀገሪቱ በከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ ወድቃለች። ይህን ተከትሎ የቻይና መንግስት በሰጠው ብድር የተሰራውን ወደብ በ99 ዓመት ሊዝ ገዝቶታል። ለዚህ ደግሞ የቻይና መንግስት የገዛውን ወደብ ለመጠበቅ በሚል የባህር ሰርጓጅ መርከቦቹን እና ወታደሮቹን በስሪላንካ ባህርና መሬት ላይ ማንቀሳቀስ ጀምሯል።

The Hambantota port on Sri Lanka’s southern coast. China has been shoring up its presence in the Indian Ocean.CreditLakruwan Wanniarachchi/Agence France-Presse — Getty Images

እ.አ.አ. በ2015 አምባገነኑ መሪ ከስልጣን ተወግዶ በአዲስ ፕረዜዳንት ቢተካም በሀገሪቱ ላይ የተጋረጠው የዕዳ ጫና ፈቀቅ አላለም። አዲሱ ፕረዜዳንት ወደ ስልጣን እንደመጣ የወሰደው የመጀመሪያ ተግባር የሀገሪቱ አየር መንገድ ወደ “Mattala Rajapaksa International Airport” የሚያደርገውን በረራ ለማቋረጥ የቀረበውን ጥያቄ ተቀብሎ ማፅደቅ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የቻይና ኩባንያዎች በሀገሪቱ የንግድና ግንባታ ሥራዎች ላይ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርቧል። አንድ የቻይና ዲፕሎማት እንደተናገሩት ስሪላንካ ያላት አማራጭ ፊቷን አዙራ ቻይናን ማቀፍ ነው። ምክንያቱም የቻይና መንግስትና ባንኮች በሰጡት ብድር ምክንያት የተፈጠረው የዕዳ ጫናው በስሪላንካ ላይ የሉዓላዊነት አደጋ ጋርጧል። ይህ የቻይና ጅብ ነው!