April 24, 2019

“የብሔረሰብ አስተዳደሩ ሊታጠፍ ነው የሚለው አሉቧልታ ለፀጥታ ችግሩ ዋናው ምክንያት ነበር።” የከሚሴው መድረክ ተወያዮች
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 16/2011ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን የተመራው የክልሉ ከፍተኛ አመራር ልዑክ ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳድር የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ዛሬ በከሚሴ ከተማ ተወያይቷል፡፡
በውይይቱ ከብሔረሰብ አስተዳደሩ የተለያዩ ወረዳዎች እና ከከሚሴ ከተማ የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡
ከሰሞኑ በአካባቢው የተፈጠረው የፀጥታ ችግር የውይይቱ ማዕከል ሆኖ የመልካም አስተዳደር፣ የሕግ የበላይነት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና ውክልናን የሚመለከቱ አስተያዬቶችና ጥያቄዎች ከተወያዮቹ ተሰንዝረዋል፡፡ በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች የመብት እና የፍትሐዊ ውክልና ጥያቄ በተወያዮች ተነስቷል፡፡
“የክልሉ መንግሥትና መሪ ድርጅቱ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ብሔረሰብ አስተዳደሩን ረስተውታል” ያሉት ተወያዮቹ እየተፈጠሩ ያሉት ግጭቶችም የዚሁ ችግር አካል መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡
በተለይም ‹‹የብሔረሰብ አስተዳደሩ ሊታጠፍ ነው›› የሚለው አሉቧልታ ለተፈጠረው ችግር እና ውጥረት ዋናው ምክንያት ነው ያሉት ተወያዮቹ መንግሥት ችግሮቹ ከመፈጠራቸው በፊት ሕዝባዊ ውይይቶችን ማካሄድ እንደነበረበት ነው የተናገሩት፡፡ ተወያዮቹ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል በግልፅ እንዲታወቅም ጠይቀዋል፡፡
በውይይቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ግንባታ፣ የመብራት፣ ውኃ እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ ተወያዮቹ ‹‹ከፖለቲካ ንትርክ አውጥታችሁ የመልማት ጥያቄያችንን መመለስ የምትጀምሩት መቼ ነው?›› ሲሉም አወያዮቹን ጠይቀዋል፡፡
ከተወያዮቹ ለተነሱ ጥያቄዎች ከብሔረሰብ አስተዳደሩ እና ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
ከብሔር ውክልና ጋር ተያይዞ “በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሚሰጡ የኃላፊነት ሹመቶች የመሪ ድርጀቱ አዴፓን መስፈርት ተከትለው የሚፈፀሙ ናቸው” ያሉት የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሐሰን “በግጭቱ ካጣነው ነገር በላይ ቀሪያችን ይበልጣልና አብረንና ተከባብረን እንሠራለን” ብለዋል፡፡
“ሕዝቡ ሳይሆን አመራሩ የራሱን ዘር እየጠቀሰ መጓተቱ ነው ችግር የፈጠረው” ያሉት የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ አዴፓ የብሔረሰብ አስተዳደሩን ትናንት እየመራ ከዚህ እንዳደረሰው ሁሉ ነገም መርቶ የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ብሔረሰብ አስተዳደሩ በቀጣይ የክልሉ መንግሥት እና የመሪ ድርጅቱ ተከታታይ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው እንደተረዱ ገልፀዋል፡፡ “በብሔረሰብ አስተዳደሩ ውስጥ አግላይም ሆነ የሚገለል ብሔር መኖር የለበትም” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ “የዘር አሉባልታ ይህን ትውልድ አይመጥንም፤ ከዚህ አሉባልታም በአስቸኳይ መውጣት ይኖርብናል” ብለዋል፡፡
በውይይቱ “የአማራ ብሔርን መልዕክት በአግባቡ ያደርሳሉ” የተባሉ አካላት ወደ ወይይቱ እንዳይገቡ ተደርጓል በሚል ከተወያዮች ቅሬታ ቀርቧል፡፡ ከቅሬታ አቅራቢዎች ጋር ውይይት አድርገው ችግሩ መፈታቱን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ዋና አስተዳዳሪ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ከከሚሴ