April 24, 2019

ጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድና የልዑካን ቡድናቸው ከቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ዥንፒንግ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል::
በውይይቱ ወቅት ፕሬዚዳንት ዥንፒንግ የጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድን አመራርና ያለፈውን አንድ ዓመት የኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት እንደሚያደንቁ ገልፀዋል።
ሀገራቸው ለኢትዮጵያን ዕድገት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥም ገልፀዋል::
የቻይና መንግሥት የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክትን ጠቀሜታ ይረዳል ያሉት ፕሬዝዳንት ዥንፒንግ ለፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ መንግሥታቸው እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል::
ጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ሁለንተናዊ የስትራቴጂ አጋርነት በማጠናከር እንደ አዲስ ጅቡቲ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት ያሉ እዳዎችን ለመከለስ የሚረዱ ወሳኝ እንቅስቃሴዎችን ለመተግበር ያላትን ቁርጠኝነት ለፕሬዝዳንት ዥንፒንግ አስረድተዋል::

የባቡር ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ተሳታፊ የሆነችበት የቤልት ኤንድ ሮድ ማዕቀፍ ቀዳሚ ውጤት ነው::
ከአለም አቀፍ ቀጠናዊና ሁለትዮሽ መግባባቶች በተጨማሪ የወጣት ኢንጂነር ናዝራዊት አበራ እስርም እንዳሳሰባቸው ጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድ ገልፀዋል::
ሁለቱም ወገኖች በሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብር በተለያዩ ዘርፎች አጠናክረው ለመቀጠል ተስማምተዋል::
ምንጭ :-ጠቅላይ ሚንስትር ፅ/ቤት