April 24, 2019

የሰሞኑ እሸት ወሬ – አዲሱ አረጋ ‹‹የቡርቃ ዝምታ›› መፅሃፍን በግልፅ ተችቷል፡፡ ብዙዎች በትችቱ ዙሪያ የተሰማቸውን ተናግረዋል፡፡ በስተጠርዝ በኩል ያሉት፣ ትችቱን ደግፈው ሲቆሙ፣ በስተዚህኛው ጥግ ያሉት ደግሞ አብጠልጥለው ተችተውታል – አዞረው አዲሱ አረጋን፡፡ ከመተቸት ባለፈ፣ መሬት ‹‹አንቀጥቅጥ›› የተቃውሞ ሰልፍ አስደርገዋል፡፡ እኔ ከሁለቱም ወገን የፀነፈ አይደለሁም፤ ከድጋፍ ሰጪውም – ከተቃውሞ አውራጁም!
ለመንደርደር ያህል፣ ስለ‹‹የቡርቃ ዝምታ›› የሚሰማኝን ልግለጥ፡፡ ይህ መፅሃፍ ታትሞ ለገበያ ሲቀርብ፣ በየሚዲያው (ያኔ ሚዲያዎች – ነፃዎቹ – ፕሬሶች ነበሩ፡፡) ውቅሰት ወ ውድሰት ወርደው ነበር፡፡ ወቃሾቹ ከመፅሃፉ የምዕራፍ ሰበዝ እየሰበዙ መርዛማነቱን አጋርተውናል፡፡ አንዴ በ‹‹ጦቢያ›› መፅሄት የታተመው ፅሁፍ፣ ርዕሱ ‹‹በመርዝ የተቦካ ቂጣ›› የሚል ነበር፡፡ ራሱ ተስፋዬ ገብረአብ፣ ከአንድ ‹‹አድናቂው›› እንዲህ የሚል አገላለፅ ያለው ደብዳቤ ከመፅሃፉ ጋር መጥቶለት እንደነበር ተናግሯል፣
‹‹በመርዝ የተቦካው ቂጣ ቤቴ እንዲቀመጥ ስላልፈለግሁ፣ መልሼ ልኬልሃለሁ፡፡››
መፅሃፉ ከታተመ – ከ20 ምናምን ዓመታት በኋላም፣ እንደአዲስ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ የተስፋዬ ስምም በየአጋጣሚው ይነሳል፡፡ በአኳያው፣ የመፅሃፉ ደራሲ ‹‹የቡርቃ ዝምታ›› አማሮችን ለአደጋ ያላጋለጠ፣ እንደህዝብነታቸው ያከበረ መሆኑን ይገልጣል፡፡ በይፋ ብቻ ሳይሆን በውስጥ ለውስጥ ግንኙነትም ወቅት ይናገራል፡፡
አንድ ጊዜ – ዓመተ-ምህረቱ ተዘነጋኝ – ከተስፋዬ ጋር የስልክ ግንኙነት አድርገን ነበር፡፡ ተስፋዬ ከላይ የጠቀስኩትን አገላለፅ ደግሞልኝ ነበር፡፡ እኔ ግን አምርሬ ተቃወምሁት፡፡ ምክንያቴ ግልፅ ነበር፤ መፅሃፉ ‹‹በመርዝ የተቦካ ቂጣ›› ነውና፡፡
‹‹የቡርቃ ዝምታ››ን ከአንዴ – አስራ ሶስት ጊዜ ደጋግሜ አንብቤዋለሁ፡፡ በየገፁ የተቀበሩ ፈንጅዎችን (የየምዕራፍ ርዕሶችንም ልብ ይሏል፡፡) ነቅሼ ማውጣት እችላለሁ፤ ጊዜና ወረቀቱ የለም እንጂ፡፡ እኔ የሚሰማኝ ‹‹የቡርቃ ዝምታ›› ታላቅ የታሪክ ቅብዠራን ለመፍጠር ታልሞ (በሟቹ ክንፈ ገብረመድህን አነሳሽነት) መፃፉ ነው፡፡ ሌላ ታሪክ የለውም፡፡ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከሪያ ታልሞ አልተፃፈም፡፡ ማስረጃዎችን – እንዳልኩት – መጥቀስ አያቅተኝም፤ ግን ብዙ ስለተባለበት ትቼዋለሁ፡፡
ከሶስት ቀን በፊት፣ አምቦ ከተማ ድል ያለ ድግስ አስተናግዳ ነበር፡፡ የብአዴንና የኦህዴድ አመራሮች ተገናኝተው ፈንጥዘዋል፤ ተጎራርሰዋል፤ ጠጅ ተገባብዘዋል፡፡ በብአዴን የተወከለው አምባቸው መኮንን ስለኦሮሞ የአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም በመናገሩ ‹‹አሰቃቂ›› ውግዘት (ከእኔ ጨምሮ) ከበርካቶች ዘንቦበታል፡፡ ወደፊት – በሌላ ፅሁፍ የአምባቸውን ጉዳይ እመለስበታለሁ፡፡ (የጠጅ ፖለቲካን ሳንረሳ!) በኦህዴድ የተወከለው ሽመልስ አብዲሳ ደግሞ፣ ስለኦሮሞና አማራ ህዝቦች የታሪክ ትስስር የሚያወራ ‹‹ዘጋቢ›› ንግግር አድርጓል፡፡ በቅርብ ሰዎቹ ‹‹የአብዲሳ አጋ ልጅ›› ተበሎ የተጠራው ሽመልስ፣ ‹‹የኦሮ-ማራ›› ጥምረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል፡፡
‹‹ኦሮ-ማራ›› – የብአዴንና የኦህዴድ ጥምረት እንጂ የህዝቡ የልብ ፍላጎት እንዳልሆነ ከተረዳሁ ቆይቻለሁ፡፡ እናንተም እንዳልተሞኛችሁ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ‹‹ኦሮ-ማራ›› የኦህዴድና የብአዴን ‹‹ፍቅር›› የመለያየት ጥላ ሲያጠላበት፣ የምትመዘዝ የድግስ ካርድ ናት፡፡ ዛሬም ድግሱ ቀጥሏል፡፡ (በነገራችን ላይ የ‹‹ኦሮ-ማራ›› ቃል ፈጣሪ አቶ ያሬድ ጥበቡ ናቸው፡፡ አቶ ያሬድ በበርካታ መጣጥፎቻቸው ይህችን ቃል ተጠቅመውባታል፡፡ ሲነጥቁ ይሉኝታ የሌላቸው – የብአዴንና የኦህዴድ ሰዎች የራሳቸው ቃል አድርገውታል፡፡ የያሬድንም ስም በየትኛውም መድረክ ላይ ለምስጋና አንስተው አያውቁም፡፡
በድግሱ ላይ አዲሱ አረጋ ያደረገው ‹‹መዘዘኛ›› ንግግር፣ ብዙ ብሔርተኞችን አንጫጭቷል፡፡ ወትሮም፣ ንዝንዝና ውዝግብ የማያጣው የኦሮሞ ፖለቲካ፣ ዛሬም በአዲስ አጀንዳ መዋከቡን ቀጥሏል፡፡ የተቃውሞ – ውግዘቱ መነሻ ‹‹የቡርቃ ዝምታ›› ነው – በመርዝ የተቦካው ቂጣ፡፡ በስራ አጥነትና ኢኮኖሚ ድቀት የታወረውን ወጣት ‹‹ሂድ ወደዚህ፣ ሂድ ወደዚያ!›› የሚያስብሉት ዘውጌ ብሔርተኞች ናቸው፡፡ በዕውነት፣ በአሁኑ ጊዜ ችግር ለተጣባባት፣ ይልቁንም የኢኮኖሚ ቀውስ የሞት ጥላ ላረፈባት ሃገር፣ አንድ ንግግር ‹‹ተደረገ!›› ተብሎ፣ አንድ ኤርትራዊ ‹‹ደራሲ›› ‹ተነካ!› ተብሎ፣ ጉድ ማፍላት ማንንም አይጠቅምም፤ አንድ የፌስቡክ ተጠቃሚ እንዳለው፣ ‹‹ከባነር ሻጮች በስተቀር››፡፡
እንደዚህ ስል ግን አዲሱ አረጋ ‹‹አይተች!›› ማለቴ አይደለም፡፡ አዲሱ የህዝብን ጨጓራ የሚገሸልጥ ንግግር ማድረጉን አልተዘነጋለትም፡፡ ለራሱ ቡድንና ወገን ጥያቄ (የ150 ዓመት ጥያቄ) ለማስፈፀም እንደሚጥር በጓዶቹ ስም ምሏል፡፡ አማሮችና ሌሎች ብሔሮች ከኦሮሚያ ሲፈናቀሉ፣ ግድ አልሰጠውም፡፡ አስመስሎ መብላት ዋና ግቡ ነውና፡፡ አንድን ዕውነት ስለተናገረ፣ የስድብ ናዳ የሚያወርዱበት ሰዎችም ያው የአዲሱ ቢጤዎች ስለሆኑ፣ ከሁለቱም የሚለይ ማንም የለም፡፡
ፅሁፌን ልጠቅልል፡፡ የሃገራችን ጠላጥ ጠንቀኛው የዘውግ ፌዴራሊዝም ነው፡፡ ለፌዴራሊዝሙ ስምረት ሁሉ ካድሬዎች የቀድሞ ካድሬ የድርሻውን ተወጥቷል፡፡ አዲሱ አረጋና ተስፋዬ ገብረአብ በዚህ መስፈሪያ ቢሰፈሩ፣ ሁለቱም ዕኩል ናቸው፡፡ ለእኛም – ለኢትዮጵያም የሚጠቅመው ሁለቱንም ንቆ መተው፣ የሃገር-አድን ትግሉን ማጧጧፍ ብቻ ነው፡፡ የዘር ፖለቲከኞችን ሆድቃ የሚሞላን ፍሬ-ከርስኪ ሃሳብ – ድርጊት በእንጭጩ መቅጨት ለነገ የማይባል ግዴታ ነው፡፡