Source: https://mereja.com/amharic/v2/111692
በኢሳት የአፋኙ ቡድን ጫና በርትቷል፡፡ Reyot – ርዕዮት
ጋዜጠኛና የመብት ተሟጋች ርዕዮት አለሙ በ“ትኩረት” ዝግጅት ላይ ከቴዎድሮስ ጸጋዬ ጋር ያደረገችው ቃለምልልስ በእነ ሲሳይ አጌና አፋኝ ቡድን እንዳይተላለፍ ታገደ፡፡

የተለየ ሀሳብ ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን ስም በሃሰት በማጠልሸትና ማናቸውንም የአብይ አህመድን አስተዳደር የሚተቹ ድምጾች ለመድፈቅ በመስራት ላይ ያለው ይህ ቡድን ማክሰኞ April 16 2019 በኢሳት ስቱድዮ ተቀርጾ አርብ April 19 2019 በኢሳት ቴሌቪዥን ሊሰራጭ የነበረውን ዝግጅት እንዳይተላለፍ አድርጓል፡፡ ይህ በሀሳብ ነጻነት ላይ የተፈጸመ ግልጽ ጭቆና ከመሆኑም በላይ፣ ስለሀሳብ ነጻነትና ስለዜጎች መብት እንቆማለን ሲሉ በኖሩ ግለሰቦች መደረጉ ተግባሩን ይበልጥ አስነዋሪና አሳፋሪ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በበርካታ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያን የማፍረስ አጀንዳቸውን ሸሽገው ለማያውቁት ኦነጋውያን የኢሳትን መድረክ ካለገደብ ሲቸር የኖረው ይህ ቡድን፣ ከኢትዮጵያዊነት በቀር ሌላ ያልተሰበከበትን ይህንን ውይይት “ለአገራዊ ደህንነት ሲባል” በሚል ተልካሻ ምክንያት ዝግጅቱ እንዳይሰራጭ ከልክሏል፡፡ አገራችን ከምን ጊዜውም በላይ የልዩ ልዩ ሀሳቦች መዋጮ በምትፈልግበት በዚህ ወቅት፣ ትላንት የአፈና ሰለባ የሆኑና ለዜጎች ሃሳብን የመግለፅ መብት ጥብቅና ሊቆሙ ይገባቸው የነበሩ ግለሰቦች፣ ዛሬ ከአገዛዝ ጋር ወግነው፣ ከሞራል፣ ከሙያና ከስነምግባር ሚዛን ወድቀው በአምባገነናዊ ተግባር መሰማራታቸው እጅጉን ይገርማል፡፡
የዚህ ከልካይ ቡድን ነውረኛ ተግባርም፣ ኢሳት ከምስረታው ጀምሮ በሀገራችን ሰፍኖ የኖረውን የህወሃት አገዛዝ ለማስወገድ በተደረገው ትግል አማራጭ የሃሳብና መረጃ ምንጭ ከመሆን የቀደመ ባለውለታነቱና አምባገነንነትን የመቃወም ታሪኩ ጋር ፍጹም የሚቃረን ነው፡፡ ተቋሙ በዜጎች ድጋፍና መዋጮ የጎለበተ እንደመሆኑ፣ ይህ የአፈና ተግባር ልዩ ልዩ ሀሳቦችን ከማስተናገድ ተፈጥሮአዊ፣ ሙያዊና ስነምግባራዊ ግዴታው ጋር አብሮ የማይሄድ ነው፡፡
ስለሆነም፣ ይህ እጅግ የተሳሳተ የአፈና ውሳኔ ታርሞ፣ የውይይቱን ይዘት ተመልክቶ ህዝቡ እራሱ ይፈርድ ዘንድ ጋዜጠኛና የመብት ተሟጋች ርዕዮት አለሙ ከቴዎድሮስ ጸጋዬ ጋር ያደረገችው የ51 ደቂቃ ገደማ ቃለምልልስ ሳይቆራረጥ ለህዝብ እንዲቀርብ ግፊት እንድታደርጉ ለኢትዮጵያውያን ወገኖች በጠቅላላ፣ ለሀሳብ ነጻነትና ለዜግነት መብት ለታገላችሁ የኢሳት ደጋፊዎችና ተመልካቾች ደግሞ በተለይ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ በዚሁ አጋጣሚ፣ ለውድ ሀገራችሁ፣ ለህሊናችሁ፣ ለእውነትና ለመርህ ለቆማችሁ በኢሳት ውስጥ ላላችሁ ባለሞያዎች ያለንን ልዩ ክብር መግለፅ እንወዳለን፡፡
አዲስአበቤነት ይለምልም፤
ኢትዮጵያ ምን ጊዜም በክብር ትኑር፡፡