ሚያዚያ 14 ቀን 2011 04/22/2019
የመጨረሻው ክፍል።
“It’s a familiar story to what we’ve seen in other countries undergoing a rapid and messy democratization, and it will require a massive effort to ensure that high-quality journalism and civic dialogue prevails without compromising freedom of expression,” said Nicholas Benequista of the Washington-based Center for International Media Assistance. በግርድፉ ሲተረጎም፤ ይህ በሌሎች ፈጣን እና ውጥንቅጡ በሆነ ሂደት የዲሞክራሲ ለውጥ ባካሄዱ ሌሎች ሃገራት ያየነው ተመሳሳይ ትርከት ነወ፤ ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት አደጋ ላይ ሳይወድቅ፤ ከፍተኛ ጥራት ያለው ጋዜጠኝነት እና የዜጎች ውይይት ኧሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ ከፍተኛ ጥረት መደረግ አለበት። ይህን የተናገሩት ኒኮላስ ቤኔኩዊስታ የተባሉት የአለማቀፍ የሚድያ እርዳታ ማእከል ባለስልጣን ናቸው። ኒኮላስ ይህንን ሃሳባቸውን የሰጡት፤ ለዋሽንግተን ፖስት ጋዜጠኛ Paul Schemm ትላንት ለንባብ በበቃው “After years of repression, Ethiopia’s media is free — and fanning the flames of ethnic tension” በሚል ረስ በፃፉት ጽሁፍ ነው። ሲተረጎም፤ ከዓመታት ጭቆና በኋላ የኢትዮጵያ ሚድያ ነፃ ነው– እና የብሔር ውጥረት እሳትን እያራገበ ይገኛል። ጋዜጣው በጽሁፉ ለምሳሌነት ያነሳው ጋዜጣም፤ የእስክንድር ነጋን ሳምንታዊ ጋዜጣ ነው።
ይህ ጽሁፍ፤ በአዲስ አበባ ከተማ “ባለ አደራ ምክር ቤት” ተብሎ መቋቋሙ ተገቢ አለመሆኑን ለማሳየት፤ የፃፍኩት የመጨረሻው ክፍል ጽሁፍ ቀድም ብሎ የተፃፈ ቢሆንም፤ ለሕትመት ከመብቃቱ በፊት፤ አዲሱን “ነፃነት” ያገኘው የኢትዮጵያ ሚዲያ፤ ለሃገሪቱ የሚበጅ ሚዛናዊ እና ትክክለኛ የሆኑ ነገሮችን ከመስራት ይልቅ፤ አብዛኛው የዜና አውታር፤ “በአድማ ፖለቲካ” ተካፋይ በመሆን፤ ከሃገር እና ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ፤ የግል ጥቅሙን ለማስጠበቅ፤ ሲል፤ የብሔር ግጭቶችን የሚያራግብ “ተቋም” መሆኑ በዋሽንግተን ፖስት ተዘግቧል። በዚህ የመጨረሻ ክፍል ጽሁፌም ለማቅረብ የፈለግኩት፤ እምብዛም ከዚህ የተለየ ባይሆንም፤ ትኩረቴ ግን፤ የአዲስ አበባ “ባለ አደራ ምክር ቤት” መቋቋምን ተከትሎ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሕመድ፤ እስክንድር ላይ “ጦርነት አወጁ ዓይነት” ፕሮፖጋንዳ “በጋዜጠኞች” በመነሳቱ እና፤ በዛም ምክንያት፤ በዶ/ር ዓብይ እና በአስተዳደራቸው ላይ የተጀመረው ስም የማጠልሸት ሥራ አግባብ እንዳልሆነ ሃሳቤን ለመግለጽ ነው። የመጀመርያ ጽሁፌ ከተፃፈ፤ ጥቂት ሳምንታት ያለፉት ሲሆን፤ የጋዜጠኞቹ አድማ፤ በስፋት እና በጥልቀት ከመቀጠሉም በላይ፤ ለለውጡ አደጋ እየሆነ መጥቷል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ። ይህም አደጋ የአለም አቀፍ ትኩረት በማግኘቱ ነው፤ የዋሽንግተን ፖስት በትላንትናው እለት፤ ስለሃገራችን ሚድያ አደገኛ አቅጣጫ የዘገበው።
ጋዜጠኞች እና የዜና አውታሮቻችን፤ በሃገራችን ላይ ሊሰሩ የሚገባው ተገቢ ሥራን በተመለከተ፤ በሚቀጥለው በሰፊው እጽፍበታለሁ። ዛሬ ግን፤ “እስክንድር ነጋ ተነካ” በሚል ስሜት፤ “ከ-አብይን አትንኩ”፤ ወደ “ሴረኛው አብይ” አመለካከት በአንድ ሌሊት የተገለበጡት የዜና አውታሮች ላይ ነው ሃሳቤን የምሰጠው። የዶ/ር ዓብይ መራሹ አስተዳደር፤ ስሕተት እና ጥፋት ሲስራ ሊወቀስ፤ ሊወገዝ፤ እና አስፈላጊ ትችት ሊሰነዘርበት ይገባል። በበጎም ይሁን በመጥፎ የሚነሱ ማናቸውም የአስተዳደሩ ሥራዎች ሚዛናዊ እና ተገቢ መሆን አለባቸው ብዬ አምናለሁ። የሃገራችን ሁኔታ ያለፈቀደ በመሆኑ፤ ሃገራችን፤ ብዙ በጋዜጠኝነት ሙያ ትምህርት የቀሰሙ “ሚዛናዊ ጋዜጠኞች” የሏትም። አብዛኞቹ የሃገራችን ጋዜጠኞች የተካኑት የፕሮፖጋንዳ ሥራ ነው። ትላንት “በልማታዊ ጋዜጠኝነት” ሙያ ሰልጥነው፤ የገዥው ፓርቲ አቀንቃኝ የነበሩ የዜና አውታሮች እና ጋዜጠኞች የነበሩትን ያክል፤ በተቃውሚው ጎራም፤ በታሪክ አጋጣም ማይክሮፎን እና በዕር የጨበጡ፤ ጋዜጠኞች እና እራሳቸውን ጋዜጠኛ አድርገው የሾሙ፤ ፕሮፓጋንዲስቶች እንደ አሸን ሊፈሉ ችለዋል።
በተለይ በውጭ “በተቃዋሚነት” የተሰለፉ “ጋዜጠኞች” ባለፉት 27 ዓመታት፤ በሰሩት ከፍተኛ የፕሮፖጋንዳ ሥራ፤ ለተደረገው ትግልና ለተገኘውም ድል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በ1990ዎቹ ከተቆቋሙት የሬድዮ ፕሮግራሞች፤ መጽሔቶች እና ጋዜጦች ጀምሮ እስከ ኢሳት እና በርካታ ድህረ ገፆች፤ እንዲሁም ከዛም በኋላ የተመሰረቱት የዜና አውታሮች፤ ያበረከቱትን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እና የከፈሉትን መስዋዕትነት ታሪክ ሲዘክረው የሚኖር ጭብጥ ነው። ሆኖም፤ እነዚህ የዜና አውታሮች፤ “ለሃገር” ብለው በሚሰሩት ስራም፤ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፤ በሃገራችን እና የሃገራችንን ሕዝብ በአስተሳሰሩ ጠንካራ ድሮች እና እሴቶች ላይም ጉዳት ያደረሱ ነበሩ። በወቅቱም እነዚህን አደገኛ ሃይሎች፤ በነበረን አቅም ሁሉ ታግለን፤ ከዋና የፖለቲካ መስመር ለማስወጣት ችለናል። እነዚህ በኢትዮጵያ አንድነት ስም፤ በሃገራችን የሕዝቦች አንድነት እና ትሥሥር ላይ ይረጩት የነበረው አደገኛ መርዝ፤ በጊዜው ባንጋፈጠው ኖሮ፤ በወቅቱ ካደረሱት ችግር በበለጠ፤ ሌላ ከፍተኛ ችግር መፍጠር እና በሃገራችን የማያባራ ጥፋት ያደርሱ እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ለዚህም ነው ዛሬ፤ በአድማ ፖለቲካ ተወጥረው፤ “በሃገር አንድነት ስም” አደገኛ መርዝ እየረጩ ያሉትን የዜና አውታሮች፤ ትክክለኛ ሥራ እንዲሰሩ ልንመክር፤ ልንወቅስ፤ እና ልንተቸ፤ ከዛም አልፎ ልናወግዝ የሚገባን።
የዶ/ር ዓብይ መራሹ መንግሥት ሥልጣን ከጨበጠ ጀምሮ፤ ልክ “መለስን አትንኩ” ይሉ እንደነበሩት የዜና አውታሮች፤ በተለይም በተቃዋሚው ጎራ ተሰልፈው የነበሩ የዜና አውታሮች “አብይን አትንኩ” ወደ ሚል ፕሮፖጋንዳ ለመቀየራቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ዶ/ር ዓብይን የሚተቹ፤ ወይም ለውጥ የለም ብለው አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች፤ የዘር ግንዳቸው እየተመዘዘም ሲብጠለጠሉ አስተውለናል። ሰዎች በሚሰጡት ሃሳብ ላይ ሳይሆን፤ በማንነታቸው እየተመዘኑ፤ ዘመቻ ሲካሄድባቸውም አንበናል። ይህ የሆነው ግን፤ ጋዜጠኞቹ የራሳችን የሚሉት ጥቅም እና “ጓደኛቸው” እስከተነካ ጊዜ ድረስ ብቻ ነበር። እንደ አቶ ኤርምያስ ለገሰ እና አቶ ደረጀ ደስታ፤ ያሉ “ጋዜጠኞች” በአደባባይ ደጋግመው እንደገለፁት፤ ለዶ/ር ዓብይ ድጋፍ የሰጡት፤ በእነሱ አባባል፤ “የተቃውሞ ድጋፍ” ነበር። ይህም ማለት፤ እነሱ ይየደገፏቸው፤ በእነሱ እምነት፤ ዶ/ር ዓብይ “ፀረ ወያኔ” በመሆናቸው ነው። በሌላ አነጋገር፤ የእነዚህ ሰዎች ድጋፍ፤ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” ከሚል መርህ እንጂ፤ ዶ/ር ዓብይ፤ ለሃገር የሚጠቅም ሥራ ይሰራሉ ወይም አይሰሩም ከሚል ጭብጥ ላይ ተመርኩዘው ድጋፍ እንዳልሰጧቸው ነው የነገሩን። የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ከዚህ የበለጠ አስተዋይ፤ ከዚህ የበለጠ መዛኝ በመሆኑ፤ ለዶ/ር ዓብይ ድጋፍ የሰጠው፤ ዶ/ር ዓብይ በሚሰጡት አመራር፤ ሃገራችንን ከገባችበት ከፍተኛ አዘቅጥ እናወጣታለን ከሚል እምነት ለመሆኑ፤ በተለያዩ የድጋፍ ስለፎች የወጣውን ሕዝብ ማየት፤ የተያዙ መፈክሮችንም ማስተዋል እና፤ በበርካታ ሚድያዎች የተዘገቡትንም የሕዝብ አስተያየቶች፤ በማየት፤ የሕዝቡ ድጋፍ መሰረት ያለው መሆኑን መረዳት ይቻላል። ድሮም፤ በአሽዋ ላይ የተሰራ ቤት መሰረት የለውም እና፤ እነዚህ እራሳቸውን የፖለቲካ ተንታኝ አድርገው የሾሙ ጋዜጠኞች፤ “እነሱን የነካ” የመሰላቸው ነገር ሲፈጠር፤ የቆሙበት የአሽዋ መሰላል በቀላሉ ተናደ። ሁሉም ነገር፤ እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ካልሆነ፤ ሃገርን መስዋዕት ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም አሳዩን።
ትላንት የነበረው የፕሮፖጋንዳ ባሕርያቸው ተቀይሮ፤ ሚዛናዊ የሆነ የዜና አውታር ይሆናሉ፤ አዎንታዊ የሆነም ነገር ይሰራሉ ብለን ስንጠብቅ፤ ወደዛው ወደ ለመዱት ፕሮፖጋንዳ ባህሪ ተመልሰው፤ ትላንት የትግራይ የበላይነት ነበር፤ ዛሬ ደግሞ የኦሮሞ የበላይነት ነግሷል፤ ይሉናል። ይህን ማለት የጀመሩት ግን፤ “አዲስ አበባ ተነካ” “እስክንድር ነጋ” ተነካ ከሚል አባዜ እንጂ፤ እውነቱ ጠፍቷቸው አይደለም። እነዚህ ሰዎች፤ የኢትዮጵያዊነትን ዜግነት የመስፈር ሥልጣን የተሰጣቸው ይመስል፤ እከሌ ከእከሌ የበለጠ ወይም ያነሰ ኢትዮጵያዊ ነው ሲሉ መስማት፤ የአስተሳስብ አድማሳቸው ርቀቱ ምን ያክል እነድሆነም አሳብቆባቸዋል። ከእነሱ በላይ ማንም ኢትዮጵያዊ የለም የሚል ድምዳሜ ላይ ስለደረሱም፤ አንዱን የበኩር ልጅ ሌላውን ደግሞ የእንጀራ ልጅ ለማድረግ ይዳዳቸዋል። “ጋዜጠኛ” ደረጀ ደስታ “አብይነትዎ” በሚል ርዕስ ጽፈው ባሰነበቡት መጣጥፋቸው “[ዶ/ር አብይ]እኔ ስለ ኢትዮጵያዊነትዎ የመጠርጠርና ያለመጠርጠር ከንቱ ጨዋታ ውስጥ አልገባም። ኢትዮጵያዊነት የግድ እሚበላለጥ ከሆነ ከኔ ቢበልጡ እንጂ ያነሱ ኢትዮጵያዊ ነዎት የሚል እምነት የለኝም። እንኳን አገሬን ከፍ አድርገው እሚጠሩልኝን እርስዎን ቀርቶ አገሬን ከዚህ ችግር የጣሉብኝና ያጣጣሉብኝን አቶ መለስ ዜናዊን እንኳ በኢትዮጵያዊነታቸው አልጠረጥራቸውም። ለነገሩ ኢትዮጵያዊነት “ነኝ” ብለው በኩራት እሚናገሩት እንጂ “ነህ አይደለህም” እየተባለ እሚሰጥ እሚነሳ ነገር አለመሆኑ ይገባኛል።”(መስመር እና ድምቀት የተጨመረ)”” ይህ የአቶ ደረጀ “ስላቅ” የተላበሰ አባባል፤ የሚገልጸው፤ እነዚህ ጋዜጠኞች፤ ኢትዮጵያዊነትን የመስፈር ሥልጣን ያላቸው፤ እራሳቸውን የኢዮጵያ የበኩር ልጆች አድርገው፤ ሌላውን ግን እንደ እንጀራ ልጅ የሚያዩ መሆናቸውን የሚጠቁም ነው።
እነዚህ ጋዜጠኞች፤ በእስክንድር ነጋ መሪነት የተቋቋመው የባለአደራው ምክር ቤት ስሕተት መሆኑን ያውቃሉ፤ ግን ስሕተት ነው ለማለት፤ አድመኝነታቸው አይፈቅድላቸውም። ስሕተት መሆኑን ስለሚያውቁም ነው፤ አቶ ሃብታሙ አያሌው በአንድ ዝግጅታቸው ላይ፤ እስክንድር ላይ ተቃውሞ የተነሳው ስለአዲስ አበባ ጉዳይ ስለተናገረ ነው ያሉት። ሆኖም፤ እስክንድር ላይ ተቅውሞ የተነሳው፤ የራሱን “አማራጭ መንግሥት” በማቋቋሙ መሆኑን፤ ሊያነሱት አይፈልጉም። እስክንድር ነጋን በመደገፍ፤ ለዶ/ር ዓብይ ደብዳቤ የፃፉትም 42 “ምሁራን” ስለባለአደራው ምክር ቤት ምንም ያነሱት ነገር የለም። በደብዳቢያቸውም፤ “የባለአደራ ምክር ቤቱ” መቋቋም ትክክል ነው ሲሉ አላነበብንም። እስክንድር ነጋ በመጀመርያ አነሳሱ “ኦሮምያ በአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም አላት” የሚለውን በመቃወም ነበር። ይህ ግን በሕግ መንግስቱ ላይ የሰፈር በመሆኑ፤ ሕገ መንግሥቱን በተመለከተ ውይይት ሲደረግ የሚነሳ ጉዳይ መሆን አለበት። “ባለአደራው ምክር ቤት” ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ተገቢ ጥያቄዎችን አንስቷል ብዬ ባምንም፤ እስክንድር ነጋ እና “ምክር ቤቱ” የሄዱበት መንገድ ፍፁም ስህተት እና አላስፈላጊ ነው ብዬም አምናለሁ። ደጋግሜ እንደገለጽኩት፤ ዜጎች ሃሳባቸውን የመግለጽ እና የመደራጀት መብታቸው መከበር አለበት፤ ግን በምንም ሁኔታ፤ ጥቂት ሰዎች ተሰባሰበው፤ የራሳቸውን “አማራጭ መንግሥት” የማቋቋም መብትም ሆነ፤ የራሳቸውን “አማራጭ ከንቲባ” የመምረጥ መብት የላቸውም። በእኔ እምነት፤ “የባለ አደራ ምክር ቤቱ” የአዲስ አበባን ከተማ አስተዳደር ስራዎች ለማጣጣል (undermine)፤ ምክትል ከንቲባውንም የዘር ጥላቻ መሰረት ያደረገ ጥላሸት በመቀባት፤ ለማዋከብ የተቋቋመ ነው። እስክንድርም ሆነ አጋሮቹ፤ ጥያቄያቸውን በተለያየ መድረክ የማንሳት እድል ነበራቸው፤ አሁንም አላቸው። ይህ ከሆነ፤ “ምክር ቤት” እና በየክፈለ ከተማው ተመሳሳይ ነገር መመስረት ለምን አስፈለገ? ባለ አደራ ምክር ቤቱ “ሕዝብ ወክሎናል” ቢልም፤ ባለአደራው ምክር ቤቱ በቅርቡ እንደገለፀው፤ ወክሎናል የሚለው “ሕዝብ” 10 ሺህ እንደሚሆን ነው። ይህ ቁጥር፤ በአዲስ አበባ ነዋሪ ከሆነው፤ ለአቅም ከደረሰው በሚሊዮኖች ከሚቆጠር ሕዝብ አንድ ከመቶ እንኳን እንደማይሆንም ልብ ማለት ያስፈልጋል። ስለዚህ ጥያቄው የትኛው የከተማ ነዋሪ ነው የወከላቸው? የሚልም ሊህን ይገባዋል።
ትላንትና በአንድ ሬድዮ፤ የአቶ ሃብታሙ አያሌውን ቃለ ምልልስ ሰሰማ የታዘብኩትን እዚህ ላይ ላንሳ። አቶ ሃብታሙ ያንፀባረቁት፤ በበርካታ የዜና አውታሮች እየተራገበ ስለሆነም ስሕተት የመሰለኝን ልሰንዘር። ዶ/ር ዓብይ፤ የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ስልጣን ሲረከቡ፤ በግልጽ የተናገሩት፤ የኢሕአዲግን የፖለቲካ ፕሮግራም እንደሚያስፈጽሙ ነው። የኢሕአዲግ ሊቀመንበር፤ መሆናቸውን እና አሁን ላለው ሕገ መንግሥት ታማኝ ሆነው እንደሚሰሩ፤ በማያሻማ ሁኔታ አስረግጠው ተናግረዋል። ትላንት ደጋፊ ዛሬ ደግሞ “ተቃዋሚ” ለሆኑት ጋዜጠኞች ይህ ለምን አዲስ ሆነ? ሃገሪቱን ዛሬ እየገዛ ያለው እና ትላንትም ሲገዛ የነበረው ኢሕአዲግ ነው። ይህንን ያልተገነዘበ ሰው ካለ፤ ለውጡን በምን እንደተረዳው ቢያስተምረን ደስ ይለኛል። በትላንቱ ሕወሃት መራሹ ኢሕአዲግ እና በዛሬው፤ ኦዴፓ መራሹ ኢሕአዲግ መካከል ግን ከፍተኛ ልዩነት አለ። የሕወሃት መራሹ ኢሕአዲግ ላለፉት 27 ዓመታት፤ ከጫፍ እስከጫፍ በዜጎቻችን ላይ ከፈተኛን በደል ፈጽሟል፤ የሃገሪቱን ሃብት መዝብሯል፤ ዜጎችን ያለአግባብ አስሯል፤ ገርፏል፤ አካል አጉድሏል፤ በአሰቃቂ ሁኔታም ገድሏል፤ ምርጫ በማጭበረበር፤ ሃገሪቷ ላይ አምባገነናንዊ መንግስት አንግሷል። ድርጅቱንም ሃገሪቱንም በበላይነት ይቆጣጠር ስለነበር፤ በብዛት የሾማቸው ባለሥልጣናት፤ የድርጅቱ አባላት ነበሩ፤ ይህ ደግሞ በየትም ሃገር የተለመደ አሰራር ነው። እኔ በምኖርበት ሃገር፤ የዲሞክራት ፓርቲ ስልጣን ሲይዝ በብዛት የሚሾመው ዲሞክራትን እንጂ ሪፓብሊካንን ወይም ሊብረተርያንን አይደለም።
ዛሬም ኢትዮጵያ ውስጥ የምናየው፤ ከዚህ የተለየ አይደለም፤ ሃገሪቱን እና ገዥውን ፓርቲ የሚመራው ኦዴፓ ነው፤ ስለዚህ፤ ኦዴፓ በብዛት የሚሾመው የድርጅቱን አባላት ነው። ይህ ለጋዜጠኞቻችን ለምን ሚስጥር እንደሆነ አይገባኝም። ኦዴፓ የሚሾማቸው ሰዎች፤ የፖለቲካ ፕሮግራሜን ከግብ ያደርሱልኛል የሚላቸውን ሰዎች ነው። መጠየቅ ያለብን ጥያቄ፤ የአሁኑ የኦዴፓ የፖለቲካ አጀንዳ ምንድነው? የሚል መሆን አለበት። ከፖለቲካ ተንታኞቹ ጋር መንገድ ላይ የምንተላለፈው እዚህ ላይ ነው። ትላንት የሕወሃት አጀንዳ፤ ሃገሪቱን በዘር በመከፋፈል፤ ኢትዮጵያዊነትን በማንኳሰስ፤ ለጥቂት ባለሥልጣኖች እና ለጋሻና ጃግሬዎቹ ጥቅም በመቆመ፤ እስከተቻለው ድረስ፤ ሕዝቡን ለረጅም ጊዜ ረግጦ ለመግዛት ነበር። ሕዝቡ ይህን እምቢ በማለትም ነው ከጫፍ እስከጫፍ ሲታገል የነበረው። የኦዴፓ መራሹ ኢሕአዲግ ግን የፖለቲካ አቅጣጫው እና አጀንዳው ከዚህ የተለየ ነው። ኦዴፓ፤ ከሕወሃት በተለይ መልኩ፤ እየሰራ ያለው እና ዋና አጀንዳው፤ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ከፍ በማድረግ፤ ሥልጣንን የሕዝብ ለማድረግ ነው። እደግመዋለሁ፤ ኦዴፓ እየሰራ ያለው፤ ሥልጣንን የሕዝብ ለማድረግ ነው። ይህንን የሚያደርገውም አሁን ያለውን ሕገ መንግሥት በመጠቀም ነው።
አቶ ሃብታሙ፤ በቃለ ምልልሳቸው ላይ ያነሱት ቅሬታ በሁኑ ስዓት ሕገ መንግስቱ አለመቀየሩ ነው። ሕገ መንግስቱ ይቀየር ማለት የማንኛውም ዜጋ መብት ነው። ግን ሊቀይረውም፤ ሊያሻሽለውም፤ የሚችለው ሕዝቡ ድምጽ በመስጠት ብቻ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ደጋግመው እንዳነሱት፤ ሕገ መንግስቱ ለውይይት ሊቀርብ የሚገባው፤ ሕዝብ የመረጠው መንግስት ሲመሰረት ነው። ይህ ግልጽ ያልሆነለት ሰው ካለ፤ ጉደለቱ ከግለሰቡ እንጂ፤ አሁን ካለው የሃገሪቱ አመራር አይደለም። ብዙ ሰዎች የሚያነሱት፤ ዶ/ር ዓብይ፤ ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያ እያሉ ቢናገሩም፤ አስተዳደራቸው ግን “ኢትዮጵያን” አይመስልም ይላሉ። ይህ እውነትነት ያለው አባብል ቢመስልም፤ መሰረታዊ ነጥቡን የሳተ ነው። ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት፤ ኦዴፓ፤ እየወሰደን ያለው፤ “ቃል ወደ ተገባላት ተራራ” ነው። ወደ ተራራው ጉዟችንን ጀመርን እንጂ ተራራው ላይ አልደረስንም። ኢትዮጵያን የሚመስል፤ አስተዳደር የምንፈልግ ሁሉ፤ እራሳችንን ከዘር ፖለቲካ አጽድተን፤ ወደ ዜግነት ፖለቲካ መሸጋገር ይኖርብናል። ዶ/ር ዓብይ እና ኦዴፓ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙ፤ እኛም ልናግዛቸው እና ግፊት ልንፈጥርባቸው ይገባል። ለዚህ ጉዞ እንቅፋት የሚሆነውን ሃይልም፤ ማንም ይሁን፤ ልንመክር፤ ልንገስጽ፤ ልንወቅስ፤ አስፈላጊም ከሆነ ልናወግዝና ልንታገል ይገባናል። የዶ/ር ዓብይ መንግሥት፤ ሃገራችንን ወደ ዲሞክራሲያዊ ስልተ ስርዓት ለማሻገር ተቋማትን እየገነባ ነው። የምርጫ ቦርድን በአዲስ መልክ ማዋቀር ብቻ ሳይሆን፤ አባላቶቹ፤ ከሌላ ሃገር ልምድ እንዲቀስሙ፤ ወደ ውጭ ለሥልጠና ልኳል። ፍርድ ቤቱን በአዲስ መልክ እያዋቀረ ነው፤ ተቃዋሚ እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ባሻቸው መንገድ የመደራጀት መብታቸውን ከማክበር ጀምሮ፤ የጋራ አሰራር እንዲኖርም እየሰራ ይገኛል። ከዚህም አልፎ፤ የዜና አውታሮች፤ ያለምንም ስጋት በሃገር ውስጥ የመንቀሳቀስ መብታቸውን አክብሯል፤ ምንም እንኳን በርካታ የዜና አውታሮች፤ ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ ቢያሰራጩም። ይህ በአንድ ዓመት ውስጥ የተከናወነ ነው። ከዚህም አልፎ፤ በሚቀጥለው ዓመት በሃገሪቱ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ እየሰራ ይገኛል። ዶ/ር ዓብይ እና አስተዳደራቸው፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የገቡት ቃል ይህንን ነው፤ ይህንንም እየፈጸሙ ይገኛሉ። ለአድመኛ ጋዜጠኞች ግን፤ ዛሬ ይህ ሊገለጽላቸው አልቻለም። በትላንት ቃለ ምልልሳቸው፤ አቶ ሃብታሙ አዲስ አበባ ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ እና ስብሰባ ማካሄድ ተከልክሏል ብለው ነበር፤ የሚገርመው ግን፤ እሳቸው ይህንን ባሉ ማግስት፤ የሕክምና ሙያ ተማሪዎች፤ በአዲስ አበባ እና በሃገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ ውለዋል። የፖለቲካ ተንታኞቻችን “ጭብጥ” ይህን ይመስላል። አድመኛ ጋዜጠኞቻችን፤ ከዚህ ዘልቀው በመሄድ፤ ‘አሁን ካለንብት ጊዜ፤ የሕወሃት ጊዜ ይሻል ነበር’ ሲሉ መስማት፤ የራሳቸውን “በቀል” ከግብ ለማድረስ የሚጓዙበት መንገድ ምን ያክል ጥልቅ እንደሆነ ያሳያል። “ሥልጣን ላይ ያወጣነህ እኛ ነን፤ እኛ እናወርድሃለን” የሚል ግብዝነትንም የተካነ አካሄድ አስተሳስበ ሲያራምዱም እያየን ነው።
ከዚህም በመነሳት ነው፤ አቶ ኤርምያስ ለገሰ፤ ዶ/ር አብይን “የሚያጋልጥ” የሃሰት “ዶሴ” ለሕዝብ አቀርባለሁ ብለው፤ ምንም ጭብጥ የሌለው፤ እጅ እግሩ የጠፋበት፤ የተፈበረከ ነገር፤ ያለምንም ሃፍረት ለሕዝብ ያቀረቡት። ምንም እንኳን አቶ አበበ ገላው እና፤ እጅግ የማከብረው አርቲስት ታማኝ በየነ፤ ከአቶ ኤርምያስ ጋር ሆነው ለሕዝብ በቀረቡበት ወቅት “የፖለቲካ ልዩነት” አለን በማለት፤ የአቶ ኤርምያስን የከሰረ ፕሮፖጋንዳ ለማድበስበስ ቢሞክሩም፤ ይህ ከፖለቲካ የሃሳብ ልዩነት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። አቶ ኤርምያስ ለሕዝብ ያቀረቡት፤ “የበቀል ፕሮፖጋንዳ” ውሸት እንጂ የፖለቲካ ሃሳብ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ ማንንም ሰው ተገቢ በሆነ እና ጭብጥ ባለው ነገር መተቸት፤ ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ ብቻ ሳይሆን፤ ከጋዜጠኞች እና ከዜና አውታሮች የምንጠብቀው የሙያ ግዴታ ነው። ነገር ግን፤ ጋዜጠኞች፤ እነሱ የሚፈልጉትን የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ ብቻ የዜና አውታሮችን፤ ያለአግባብ ሲጠቀሙ፤ የሕዝብን አመኔታ የሚያጡ ፕሮፖጋንዲስቶች ይሆናሉ።
በመጨረሻም ይህን ልበል።ይህንን ጽሁፍ ስጀምር፤ አፕሪል 5፣ የአባቴ የልደት ቀን ነበር። አባቴ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ የራሱን ድርሻ ጥሎ አልፏል። እኔ፤ ትምህርቴ የንግድ፤ የሂሳብ አያያዝ፤ የኢኮኖሚ እና የሕግ እንጂ፤ የጋዜጠኝነት ሙያ የለኝም። ሆኖም፤ በተለያዩ የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ውስጥ የመሳተፍ ዕድል አጋጥሞኛል። በጨቅላ እድሜዬ በኢትዮጵያ የዜና አገልግሎት ሬድዮ ላይ ከመቅረብ ጀምሮ፤ በ2007 (እአአ) በአዲስ አበባ ጋዜጣ እስከማሳተም ድረስ ተሳትፍያለሁ። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1993 በመሰረትኩት “ልዩ ሬድዮ” (ከጋዜጠኛ ወንድወሰን ከበደ “ልዩ ሬድዮ” ጋር አንድ አይደለም) ለዋሽንግተን እና ለአካባቢው፤ ስናስተላልፈው የነበር፤ የማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ፕሮግራም ነበር። ከዛ በኋላም፤ ሕብረት ሬድዮ በሚል ሥም፤ በWUST Radio ፕሮግራም በመስራት ወደ ሁለት ዓመታት በላይ፤ ከሕብረት ሬድዮ ጋር ሰርቻለሁ። ሕብረት ሬድዮን ለቅቄ ከወጣሁ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ፤ “AIT Entertaiment” በሚል በተቋቋመው በሬድዮ ፕሮግራም፤ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ፕሮግራም ሰርቻለሁ። በተለያዩ ሬድዮ ፕሮግራሞችም ቃለ ምልልስ በማድረግ ተሳትፍያለሁ። የመጨረሻ በሕዝብ መገናኛ የነበረኝ ተሳትፎ፤ በሚያዚያ 1999 አዲስ አበባ ስናሳትመው የነበረ “የቡና ቁርስ የተሰኘች ጋዜጣ ነበረች፤ እሷም በ4ተኛ እትሟ፤ በኢሕአዲግ መራሹ መንግስት በደረሰብን ወከባ፤ ማስፈራርያ፤ እና በተጋረጠብን አደጋ ህትመቱን ለማቆም ተገደናል። ከዚህ ባለፈ፤ በሕዝብ መገናኛ ያለኝ ተሳትፎ፤ የተለያዩ ጽሁፎችን በመፃፍ ለተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ማቅረብ እና በራሴ ድህረ ገጽ በማተም ነው። በተሳተፍኩባቸው የዜና አውታሮች ሁሉ፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሚዛናዊ ሆኖ ለመስራት መሞከር፤ ምን ያክል ከባድ እና አደገኛ መሆኑንም አይቻለሁ፤ አብረህ ማደም አለብህ፤ ካላደምክ፤ አንተም ላይ ይታደምብሃል። ይህ ነው የዜና አውታሮቻችን አሰራር።
ከላይ ያለውን የራሴን ልምድ ያጋራሁበት ምክንያት፤ ምንም እንኳን “ጋዜጠኛ” ባልሆንም፤ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ውስጥ በነበረኝ ተሳትፎ ያየኋቸው ጉድለቶች ዛሬም እየተንፀባረቁ በማየቴ፤ ከማውቃቸው ነገሮች የምነሳ መሆኔን ለመጠቆም ነው። በተለይ፤ ከሁሉም በላይ በሕብረት ሬድዮ ውስጥ እንድሳተፍ ያደረገኝ ነገር፤ ዛሬ ለማነሳቸው ነጥቦች ብዙ ጠቋሚ ነገሮች አሉት። ሕወሃት፤ የሥልጣን መንበሩን ከተቆጣጠረ በኋላ፤ በተቀዋሚነት ከተመሰረቱት ተቋማት ውስጥ “ሬድዮ ፕሮግራሞች” ይገኙበታል። እነዚህ ሬድዮ ፕሮግራሞች፤ በዛ ወቅት የተቋቋሙበት ዓላማ አንድ እና አንድ ብቻ ነበር፤ ይኽወም፤ ሕወሃት እና ሻዕብያ በሃገር ላይ የሚሰሯቸውን በደሎች፤ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ እና ሕወሃትን/ሻዕብያን “መታገል” ነበር። ሕዝቡ በሕወሃት/ሻዕብያ ላይ እንዲነሳ ይሰሩ የነበሩ የቅሰቀሳ ሥራዎች፤ እውነት ይሁን ውሸት ማንም አይፈትሻቸውም፤ ውሸት እንኳን ቢሆን፤ ውሸት ነው ብሎ ደፍሮ በአደባባይ ለመናገር የማይቻልበት የፖለቲካ ድባብ ነበር። በተለይ የዋሽንግተንን እና የአካባቢውን ነዋሪ በፍርሃት አሸማቀው የያዙት የሬድዮ ፕሮግራሞች፤ ከእነሱ የተለየ ሃሳብ የሚያቀርብን ሁሉ “ወያኔ እና ሻዕብያ” የሚል ታርጋ እየለጠፉበት፤ ብዙውን ለሃገሩ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችለውን ሃይል ከፖለቲካ መድረኩ እንዲወጣ አድርገዋል። የነጋዴው ሕብረተሰብ፤ እነሱን ካልደገፈ፤ ማህበረሰቡን በማሳደም የንግድ ተቋማትንም እስከ ማዘጋት ደርሰዋል። በወቅቱ ገንነው ይሰሙ የነበሩ ጥቂት የሬድዮ ፕሮግራሞች፤ እራሳቸው ላይ “የንግስና አክሊል” ደፍተው፤ የኢትዮጵያዊ ዜግነት ለማን እንደሚገባው ዜግነት መስፈር የጀመሩበት ወቅትም ነበር። ምንም እንኳን “የአንድነት ሃይል ነን” በሚል መርህ ቢንቀሳቀሱም፤ ሥራቸው ፍፁም በታኝ እና ፀረ አንድነት ነበር።
ሕብረት ሬድዮ የተቋቋመው ይህንን ጽንፈኛ ሃይል በመታገል፤ ለሕዝቡ የተሻለ አማራጭ ለመስጠት እና፤ ጽንፈኛው ሃይል በተቆጣጠረው የዜና አውታር የሚሰራውን ሃገር በታኝ ተግባርም ለማጋለጥ ነበር። በዚህም ሥራችን፤ አክራሪውን ሃይል፤ በሃሳብ፤ በድፍረት የሚሞግት አማራጭ ሬድዮ ፕሮግራም ፈጥረናል። በእኛ ላይ የተከፈተውን የስም ማጥፋት ዘመቻ በመመከት፤ አክራሪ ሃይሉን፤ በሃሳብ ማሸነፍ በመቻላችን፤ ከተማይቱ ላይ ተጭኖ የነበረው “የፍራቻ ጉም” ተገለጧል። በዚህም ምክንያት፤ ብዙዎች ያለስጋት የሚፈልጉትን ለማድረግ ችለዋል። ከዚህም በዓይነቱ የሚጠቀሰው፤ ትግላችን ከሕወሃት እና ከሻዕብያ ጋር እንጂ፤ ከትግራይ እና ከኤርትራ ሕዝብ ጋር አለመሆኑን በማስረገጣችን፤ በርካታ የትግራይ ተወላጆች፤ ፀረ ሕወሃት አመለካከታቸውን እንዲያንፀባርቁ በር መክፈታችን እና በአርቲሰት ደበበ እሸቱ እና፤ አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ለተከሰተው ረሃብ እርዳታ ለመሰብሰብ ወደ አሜሪካ በመጣበት ወቅት፤ ይህ ቡድን ሥራውን እንዳይሰራ በአክራሪው ሃይል የተፈጠረበትን መሰናክል እንዲቋቋም ማድረጋችንም ነው። ቡድኑ፤ ይህን መሰናክል በጣጥሶ የተላከበትን ተለኮ እንዲፈጽም ለቡድኑ “ድምጽ” መሆናችን እና ከማህበረሰቡ ጋር እንዲገናኝ አማራጭ መድረክ መስጠታችን እራሱን የቻል ስኬት ነበር። ያኔ ዝም ብንል ኖሮ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አያዳግትም።
ዛሬም፤ እንዲህ ፈጦና ገጦ የመጣውን፤ በሃገራችን የዲሞክራሲ ሂደት ላይ ጋሬጣ የሚሆነውን አካል፤ ተው ልንል ይገባል። ሕዝቡን የሥልጣኑ ባለቤት ለማድረግ የተጀመረው ጉዞ፤ ያለ እነከን ይቀጥላል ማለት አይቻልም። እንከኑን በማረም፤ ትግሉን በማገዝ፤ አንዱ እግራችን፤ ሌላኛውን እግራችንን እንዳይጠልፍ፤ አረማመዳችንን በማስተካከል፤ ሕዝቡ የሥልጣኑ ባለቤት እንዲሆን መታገል አለብን። ትላንት ለሃገር ውለታ ሰሩ የምንላቸው ሰዎች፤ ስሕተት ሲሰሩ እያየን ዝም የምንል ከሆነ፤ የሕዝባችንን ስቃይ የምናራዝም መሆኑን ልብ ልንል ይገባል። በተደጋጋሚ እንደተነገረው፤ ሕወሃት ለ27 ዓመታት ረግጦ የገዛን፤ ጉልበት ስለነበረው ሳይሆን፤ እርስ በእርሳችን በመጠላለፍ እና “እኛ በምንደግፋቸው ሃይሎች” ስሕተት ሲሰራ በዝምታ ማለፋችን ነው። ዓፄ ኃይለሥላሴ እንዳሉት መጥፎ ነገሮች እያደጉ እና ድል እያደረጉ የሚመጡት፤ መጥፎ እና አድገኛ ነገሮችን የሚያዩ ሰዎች፤ አድገኛነታቸውን መናገር እና ማጋለጥ ሲገባቸው ዝም በማለታቸው ነው። ስለዚህ፤ በዝምታ አንለፍ።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቧቿን ይባርክ።
አስቀድሜም መልካም ፋሲካ እላለሁ።