April 25, 2019

BBC Amharic – የሁለት ጊዜ ኦሎምፒክ እና አራት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮን ባለድሉ ኃይሌ ገብረሥላሴ ከእንግሊዛዊው አትሌት ሞ ፋራህ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ነው።

Image result for mo farah and Haile

ጉዳዩ ወዲህ ነው። እንግሊዛዊው ሯጭ ሞ ጥሬ ገንዘብ፣ የእጅ ሰዓት እንዲሁም ሁለት ተንቀሳቃሽ ስልኮች ብሰረቅም ኃይሌ ሊረዳኝ አልቻለም ይላል።

«በኃይሌ እጅጉን አዝኛለሁ» ሲሉ ተደምጧል የ36 ዓመቱ ሞ ፋራህ።

የ46 ዓመቱ ኃይሌ በበኩሉ እንደውም ሞ ፋራህ ስሜን በማጥፋት እና ‘ቢዝነሴ’ እንዲጎዳ በማድረግ ልወቅሰው እፈልጋለሁ ብሏል።

ሞ ፋራህ ወቀሳውን ያቀረበው እሁድ ለሚካሄደው የሎንዶን ማራቶን ዝግጅት በማድረግ ላይ ሳለ ከጋዜጠኞች ለቀረበለት ጥያቄ ነው።

ፋራህ እንደሚለው ስርቆቱ የተፈፀመው ኃይሌ በሚያስተዳድረው ሆቴል ውስጥ ነው።

«እስቲ አስቡት፤ ሆቴሉ የሱ ነው። ሦስት ወራት የቆየሁበት ሆቴል ውስጥ እንዲህ ዓይነት ዝርፍያ ሲፈፀምብኝ ሊረዳኝ አለመሞከሩ አናዳጅ ነው» ሲሉ ምሬቱን አሰምቷል።

ፋራህ እንደሚለው ስርቆቱ የተፈፀመው መጋቢት 14፣ 2011 ዓ. ም. ነው።

በወኪሉ አማካይነት ሃሳቡን ለቢቢሲ ስፖርት ያካፈለው ኃይሌ፤ ፋራህ ለፈፀመው ስም ማጥፋት በሕግ ሊጠይቀው እንዳሰበ አሳውቋል።

ከሎንዶን ማራቶን ጋዜጣዊ መግለጫ በፊት ሞ ፋራህ የላከለኝ የፅሑፍ መልዕክት ማስፈራሪያ ያዘለ (ብላክሜይል) ነው ይላል ኃይሌ።

ኃይሌ እንደሚለው ሆቴሉ የሚያርፉ ሰዎች ከ350 ዶላር በላይ ይዘው ከሆነ እንዲያሳውቁና ምስጢራዊ ሳንዱቅ እንዲሠጣቸው ወይም ደግሞ ሕጋዊ ከለላ እንዲደረግላቸው ይደረጋል።

ፋራህ ግን ገንዘቡን መያዝ ፈለገ፤ ይህ ማለት ለሚጠፋው ገንዘብ ሆቴሉ ተጠያቂ አይደለም፤ ይላል ኃይሌ በወኪሉ አማካይነት የላከው መልዕክት።

አክሎም በስርቆቱ የተጠረጠሩ አምስት የሆቴሉ ሠራተኞች ተይዘው ምርመራ ቢካሄድባቸውም ፖሊስ ምንም አይነስ ማስረጃ ባለማግኘቱ ለቋቸዋል።

ፋራህ 50 በመቶ ቅናሽ ተደርጎለት የከረመበትን ሆቴል 81 ሺህ ብር ገደማ ክፍያ እንኳ ሳይከፍል ነው የሄደው ሲል ኃይሌ ይወቅሳል።

አልፎም ፋራህ ሆቴሉ ውስጥ ሳለ ያልተገባ ባህሪ አሳይቷል፤ ባለትዳር አትሌት አንጓጧል፤ እኔ በመሃል ገብቼ ባልገላግል ኖሮ በሕግ ይጠየቅ ነበር ሲል ተፈጠረ ያለውን ያስረዳል።

ሞ ፋራሃ ለዚህ ወቀሳ ምላሽ እንዲሰጥ ተጠይቆ ነበር። እርሱም በወኪሉ አማካይነት ወቀሳው እጅግ እንዳበሳጨው አሳውቋል።

«ሞ የቀረቡበትን ወቀሳዎች ሁሉ አይቀበላቸውም። ሁኔታውን ለማደነጋገር የቀረቡ ናቸው። የሆቴሉ ሠራተኞች ቁልፍ ተጠቅመው የፋራህን ንብረት ዘርፈዋል። ሆቴሉ ውስጥ ምስጢራዊ ሳንዱቅ አልነበረም። ሞ ፋራህ ግን እንዲገጠምለት ጠይቆ ነበር» ሲሉ ወኪሉ አትቷል።

በተጨማሪም «ፖሊስ በቦታው ነበር። የሆቴሉ አስተዳደሮችም ክስተቱን መፈጠሩን አምነው ከሞ የሕግ ሰዎች ጋር በመምከር ላይ ነበሩ። እንደውም ሆቴሉ ገንዘቡን መልሶ እንደሚከፍለው ነግሮት ነበር። ነገር ግን ሞ ሆቴል ሲቀይር ትቶታል» ይላል።

ሞ ፋራህ የላከው መልዕክት አክሎም «ኃይሌን በግል ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም። አሁን ግን እርሱም ሊያነጋግረን ፈቃደኛ ከሆነ ሞ ፋራህ ራሱን ወይንም ጠበቆቹን ማናገር ይችላል። ጉዳዩ መፍትሄ እንዲያገኝ እንፈልጋለንና» ሲል ይቋጫል።