April 25, 2019
መገናኛ ብዙሃን ሰርክ ዜና ቢያደርጉት ሰሚ ጆሮ ያገኙ አይመስልም ፡፡ ዛሬም ብዙዎች ህይወታቸውን ሰውተውበታል አካላቸው ገብርውበታል ፡፡ በጉልባት ብዝባዛ ብዛት የልጅነት ወዛቸውን እጥተውበታል ፡፡ አልሞላ ያለው የአረብ አገራት ኑሮ አጉብጦቸውም ቢሆን ከሚደርስባቸው ስቃይ እና መከራ ጋር ሁሌም እንደተጋፈጡ ነው -እኒያ የህገወጥ ስደት ሰለባዎች፡፡ የህገ ወጥ ስደት ሰላባዎች ስቃይ ከወደ መካከለኛው ምስራቅ አካባቢ መስማት ደግሞ የተለመደ ሆኖል፡፡ በተለይ ደግሞ በሴት እህቶቻችን ላይ የሚደርሰው ስቃይ እና ፈተና ይበረታል ፡፡ በህገ ወጥ መንገድ ተጉዘው አረብ ሀገራትን መኖሪያቸው ያደረጉ ሴቶች እያሳለፉ ያሉትን ሁኔታ ሲናገሩ ሁሌም እንባቸው ይቀድማል፡፡ ቃላት ከሚገልፀው በላይ የሆነን መከራ እያሳለፉ ነውና ፡፡ ሰርቼ ያልፍልኛል፤ ከእኔም ተርፎ ደሃ ቤተሰቤን እደግፋለው የሚል ተስፋን ሰንቀው በብዙ ውጣ ውረድ የሚመኙት አረብ ሀገር ቢደርሱም የሚደርስባቸው የጉልባት ብዝበዛ ከሚያገኙት ጥሪት ጋር አይነፃፀርም ፡፡ ብዙዎች አረብ አገራት ለመድረስ በተቀናጀ መንገድ ለሚንቀሳቀሱት ህገ ወጥ የሰው ልጅ አዘዋዋሪዎች እና ደላሎች አረብ ሀገር ለመግባት ተገቢ ያልሆነ ገንዘብ ከፍለው ለኪሳራ የተዳርጉ ናቸው፡፡ የገቡት በህገወጥ መንገድ እንደመሆኑ ኑሮቸውም ቢሆን ከዛሬ ነገ እያዝ ፣ እታሰር እና እባረር ይሆን በሚሉ ስጋቶች የተሞላ ነው፡፡ ስለ እነዚህ የደላሎች እና የህገ ወጥ አሰሪ እና ሠራተኛ ኤጀንሲ ሰላባዎች ብዙ ቢነገርም፣ ብዙ ቢባልም ፣ ብዙ ቢሰማም ዛሬም ብዙዎች ህገ ወጥ መንገድን ተከትለው ይተማሉ፡፡ ለሌላ ብዝበዛ እና የክፉ ዜና ሰላባ ለመሆን
በመካከለኛ ምስራቅ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ብዙዎቹ ህጋዊ አይደሉም። አብዛኛዎቹ ፓስፖርትና የመኖርያ ቪዛ የላቸውም። በህገወጥ መንገድ ቀይባህር በማቋረጥ በሳውዲ አረብያ በመሳሰሉ ሀገራት ለስራ ፍለጋ የሄዱ ናቸው። ዛሬም በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የነዳጅ ሀብት በተቸራቸው በሃብታሞቹ የአረብ ሀገራት ሳይደርሱ በመንገድ ላይ ይሞታሉ፤ የመን ላይ ባለው የርስበርስ ጦርነት ሰለባ ይሆናሉ። ከሰሞኑን እንኮን ቀይ ባሕርን አቋርጠው ወደ ሳውዲ አረቢያ እና የመን በጀልባ በመጓዝ ላይ የነበሩ 70 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የመገልበጥ አደጋ ገጥሞቸው ህይዎታቸው አልፎል፡፡ ከብዙ ስቃይ በሆላ እንኮን የሚመኙት አረብ ሀገር የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አስፈላጊውን የሰነድ ግብአት ስለሌላቸው ለእንግልት፣ የመብት ጥሰት እና የጉልባት ብዝበዛ የተጋለጡ ናቸው። ግን ዜጎቻችን ህጋዊ መንገድን ተከትለው ቢሄዱ ይህን ሁሉ ስቃይ ፣ መከር እና እንግልት ማስቀራት በተቻለም ነበር፡፡
ህገወጥ ስደትን ይገታል በሚል ኢትዮጵያ በ2018 አዲስ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አዋጅ አውጥታ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ነች፡፡ የቆየውን አዋጅ በአዲሱ የሥራ ስምሪት አዋጅ መተካት ያስፈለገው ወደ ውጭ አገር በመሄድ ለመሥራት ፍላጎት ያላቸው ሰራተኞች መብቶቻቸው እና ደህንነታቸው ተጠብቆ ባላቸው ችሎታና አቅም ሠርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ነው፡፡ በአዋጅ ቁጥር 923/2008 መሰረት በውጭ አገር ለስራ የሚሰማሩ ዜጎች ዕድሜያቸው ከ18 አመት በላይ የሆኑ ፣ 8ኛ ክፍል ያጠናቀቁ (ወደ 9ኛ ክፍል የተዛወሩ)፣በሚሄዱበት የስራ መስክ ስልጠና ወስደው የብቃት ማረጋገጫ ያገኙ፣ የቅድመ ጉዞ ስልጠና ወስደው ሰርተፊኬት የያዙ፣ የጤና ኢንሹራንስ የተገባላቸው፣ ሙሉ የጤና ምርምራ ያደረጉና ከወንጀል ነጻ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህን ያሟሉ ዜጎች በአስቀጣሪ ኤጀንሲ በኩል ወይም በራሳቸው አማካኝነት ሥራውን በማፈላለግ እና የቅጥር ፎርማሊቲዎችን በማሟላት ቪዛውን አግኝተው በህጋዊ መንገድ መሄድ ይችላሉ፡፡
ወደ አረብ አገራት በቤት ሠራተኝነት የሚሄድ ስራ ፈላጊዎች ሊጓዙ የሚችሉት በኤጀንሲዎች አማካኝነት ብቻ ነው፡፡ የስራ ስምሪት ማድረግ የሚቻለውም አገሪቷ የሁለትዮሽ ስምምነት ወደተፈራረመችባቸው ሀገራት ብቻ ነው፡፡ የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ስምምነት የተፈራረመችው ከሳውዲ አረቢያ፣ ኳታርና ጆርዳን ጋር ሲሆኑ ከሀገራቱም ጋራ መንግስት የደሞዝ ስምምነት አድርጎል፡፡ ስምምነት በተፈፀመባቸው ሀገሮች የደመወዝ መጠን ስንመለከት ከኳታር መንግስት 1200 ለቤት ሠራተኛና 1300 ለእንክብካቤ (care giver) የኳታር ሪያል፣ ከጆርዳን መንግስት ለጀማሪ 225 ዶላር፣ ልምድ ላላቸው 250 ዶላር፣ ከሳውዲ አረቢያ መንግሰት ጋር 1000 የሳውዲ ሪያል በራዊ ክፍያን ይከፍላሉ፡፡ ታዲያ ውጭ ሀገር በህጋዎ መንገድ ሂደው መስራት ከፈለጉ ስልጠናዎችን ሊወስዱ ግድ ነው፡፡ ለውጭ አገር ሥራ ስምሪት የሚሰጡ ስልጠናዎች ሶስት ሲሆኑ እነሱም በቤት አያያዝ (HOUSE HOLD SERVICE) በቤት ውስጥ ስራ (DOMESTIC HELP) እና በእንክብካቤ ስራ (CARE GIVING) ናቸው፡፡ ሠልጣኞች ስልጠናውን በግላቸው ሊሠሩበት፣ በአገር ውስጥ ሊቀጠሩበት እንዲሁም ወደውጭ አገር ሊሰማሩበት የሚችሉባቸው ናቸው፡፡ይሁን እንጂ ወደአረብ አገር መሄድ የሚፈልጉ ሰልጣኞች ከላይ በተጠቀሱት ሦስት ሙያዎች ከሰለጠኑ በኋላም የብቃት ምዘና ማረጋገጫ ተፈትነው ማለፍና ሰርተፊኬት መያዝ ይኖርባቸዋል፡፡ ስልጠናው በየክልሉ በተመረጡ 66 የማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ ይሰጣል፡፡ በቅርቡ የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ እንዳስታወቀው መንግስት ከ360 በላይ ለሚሆኑ አሰሪ እና ሠራተኛ አገናኝ አጀንሲዎች ህጋዊ ዕውቅና ሰጥቶል ፡፡ ታዲያ ወደ አረብ አገራት ሂደው በህጋዊ መንገድ ለመስራት ካሳቡ እነዚህን ህጋዊ ኤጀንሲዎችን ብቻ መጠቀም ግድ ይልዎታል፡፡
ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ መሄድ ለራስም ፣ለቤተሰብም ብሎም ለሀገርም ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ መብትዎ ቢጣስ ፣ የጉልበት ብዝበዛ እና መሰል ጥቃት ቢደርስብዎት ለመንግስት ወይም ለላከዎት ኤጀንሲ ሀይ ማለት ይችላሉ ምክንያቱም ህጋዊ መንገድን ተከትለው የመጡ ህጋዊ ሠራተኛ ነዎትና፡፡ ፊልፕኒስ ዜጎችዋ በሌላ ሀገር ልካ በማሰራት ከአለማችን በመሪነት ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሀገር ነች። እንደ ሀገሪቱ መንግስት መረጃ ከሆነ ከ2.3 ሚልዮን በላይ ፊልፕኒሳውያን በውጭ ሀገራት ይሰራሉ። ብዙዎችም የአረብ ሀገራት ሠራተኞች ናቸው፡፡ አብዛኛው ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ የሚሰራ ፊሊፕኒሳዊ ህጋዊ በሆነና የሀገሪቱ መንግስት ባቋቋማቸው ኤጀንሲዎች በኩል የሚሄድ ነው። ህገ ወጥ ስደት በፊሊፕኒስ ሀገር ውስጥ እምብዛም አይደለም። ሰራተኞቹም መብታቸው ተከብሮ እየሰሩ ነው፡፡ በዚህም ሀገሪቱ በየዓመቱ ሠራተኞችዋ የሚልኩትን ረብጣ ሚሊዮን ዶላር ታፍሳለች፡፡
ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ወደ አረብ ሀጋራት ከሄዱት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መካከል ከ 60-70% ወይም በቁጥር ሲሰላ 300,000- 350,000 የሚሆኑት ስደተኞች በ ህገ ወጥ ወይም መደበኛ ያልሆነን መንገድን ተከትለው ወደ አረብ አገራት የገቡ ናቸው ፡፡ ብዙዎችም በሳውዲ አረቢያ ፣ ኩዌት እና ሊባኖስ ውስጥ እየሰሩ ያሉ ናቸው፡፡ ስለ እነዚህ ስደተኞች ታዲያ መንግስት ቢሆን መረጃ ላይኖረው ይችላል፡፡ በደል እና ብዝበዛ ቢደርስባቸው ሰሚ ወገን አያገኙት ፡፡ የሀገሪቱ መንግስት ህገወጥ እንደ መሆናቸው መጠን ለመብታቸው መከበር ዕቁብ አይሰጥም፡፡ ኢትዮጵያም ህገወጥ እንደመሆናቸው መጠን ለእነዚህ ዜጎች ከለላ ለመስጠት ትቸገራለች፡፡ በተቃራኒው ህጋዊ መንገድን ተከትለው የሄዱት ግን መብታቸው ተከብሮላቸው ይሰራሉ ፣መብታቸው ቢነካ እንኮን የመክሰስ መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡ መንግስት እና ስራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በህጋዊ መንገድ የሄዱ ሠራተኞችን ተገቢ ካልሆነ በደል እና ብዝበዛ የመከላከል ሀላፊነት አላባቸው፡፡ የላክዎት ኤጀንሲም ህጋዊ ስደተኛ የውጭ አገር ሠራተኞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድጋፍ ያደረጋሉ፡፡ በውጭ አገር ስራ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙ መርዳት ግዴታቸው ነውና ፡፡ በህገወጥ መንገድ በደላሎች እና አስተላላፊዎች ድጋፍ የሚደረግ የስደት ጉዞ እስከ ህይዎት መስዋዕትነት ያስከፍላል፡፡ ጉዞው ተሳክቶ የአረብ አገራትን ቢረግጡም ኑሮው ሰቃይ የተሞላበት እና ስጋት ያዘለ ነው፡፡ በሕገ ወጥ የሰው ልጅ አዘዋዋሪዎች በኩል በሚሰጠው ያልተጨበጠ ተስፋ ቁብ ሳይሰጡ ህጋዊ መንገድን ተከትለው እና መስፈርረቱን አሞልተው መሄድን ቀዳሚ ምርጫዎ ያድርጉ፡፡ ይህም እርስዎን እና ተስፋ የጣለበዎትን ቤተሰብዎን የበለጠ ተጠቃሚ ያደረጋልና፡፡