Source: https://mereja.com/amharic/v2/111809
በህንድ የኢትዮጵያ ገራሚ ንጉሥ ታሪክ አህመዲን ኤም ሱሌይማን እንደተረጎመው።

ማሊክ አምበር፣
አቢሲኒያንስ ወይም ሀበሺስ በመባል ይታወቃሉ በሚኖሩበት ህንድና ፓኪስታን። ቁጥራቸዉ ከ 250-300 ሺ እንደሚጠጋ ይገመታል። በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ የህንድ ባህር ዳርቻዎች፣ በፖኪስታን ዉስጥ ባልችስታን ግዛትና በካራቺ በስፋት ሰፍረዉ ይገኛሉ።
በ 1548 በዳሞት ወይም ሀዲያ እንደተወለደ የሚነገርለት ማሊክ አምበር፣ በባርነት ከአገሩ ተሽጦ መጀመሪያ ወደ አልሙከሀ የመን ተወሰደ። በዚያም ትንሽ ከቆየ በኋላ እንደገና ተሽጦ ወደ ባግዳድ የባሪያ ገበያ ተወሰደ። በዛም ለመካ ቃዲ አል ቁዳት ተሸጠ። ተመልሶ በባግዳድ ሚር ቃሲም አልባግዳዲ ለተባለ ሰዉ ተሽጦ ወደ ህንድ ተወሰደ። የደች የባህር ነጋዴዉ peater van den broeck ማሊክን ‘የሮማ (ነጭ) የፊት ቅርፅ ያለዉ ጥቁር ካፊር’ ብሎ ይገልፀዋል።

ህንድ እንደገባ ከአሳሪዎቹ በማምለጥና ከአቢሲኒያ አብረዉት የመጡ ቁጥራቸዉ ወደ 1600 የሚደርሱ ባሪያዎችን በመሰብሰብ በርሱ የሚመራ የሽምቅ ቡድን ዲካን በተባለ አዉራጃ ዉስጥ ያቋቁማል። አካባቢዉ ካሉ የተለያዩ ሱልጣኔቶች ጋር ባደረገዉ ጦርነት ሁሉንም በማሸነፍ ስሙ እየገነነ ግዛቱን ቦታዉን እያሰፋ ይመጣል።
ማሊክ አምበርና ተዋጊዎቹን ወዳጅና አጋር ለማድረግ የተለያዩ ንጉሶች በስልጣንና ጥቅማጥቆች ሊሸነግሉት ይሞክሩ ነበር። እ.ኤ.አ ከ 1607-1626 በዲካን ለሚገኘዉ ለኒዛምሻ ሥርወ መንግስት ንጉስ ሙርታዝ ካን፣ አጋርነቱን አሳይቶ በመጀመሪያ የግዛቱ ጦር መሪ፣ በኋላም ምክትል አስተዳዳሪና ሙርታዝ ካን ካለፈ በኋላ የግዛቱ ንጉስ በመሆን አገልግሏል። ከሙርታዝ ካን ጋርም ሰፊ ግዛቶችን በመቆጣጠር ሥርወ መንግስቱን ማስፋት ችሏል።
ማሊክ አምበር የአስተዳደር ብቃቱን አዉራንግባድ የተባለችን አዲስ ከተማ በመቆርቆር፣ በዛም ተበታትኖ ይኖር የነበረን ህዝብ በአንድ በማስፈር፣ የግብርና ቀረጥ ስርዓትን በመዘርጋት፣ ከየትኛዉም በህንድ ግዛት ከሚገኙ ከተሞች በግምባር ቀደምትነት ከተማዉንና ነዋሪዉን ዉስብስብ የግንባታ ጥበብ የታየበትን የዉሀ ማስተላለፊያ ካናል በመገንባት የመጠጥ ዉሀ ተጠቃሚ ማድረግ በመቻል፣ የስነ ህንፃና የስነ ጥበብ ብቃቱን ያሳየባቸዉን በርካታ የመንግስት መቀመጫ ህንፃዎችን፣ ቤተመንግስቶችን፣ መንገዶችንና ሌሎችም መሰረተ ልማቶችን በመገንባት አሳይቷል። የግዛቱን ዋና ከተማም ከጁናር ወደ አራንግባድ ለመቀየርም ችሏል።
ማሊክ አምበርና ተከታይ አቢሲኒያዊያን ሀበሾች በጦር አመራርና በአስተዳደር ብቃት ብቻ ሳይሆን በሙዚቃዉ፣ በስነጥበብ ስራዎች በአርት፣ በአርክቴክት፣ በአስተዳደርና በሌሎችም ሙያዎች መግነን ችለዉ ነበር። ከአገራቸዉ አቢሲኒያም ወደ ዲካንና በኋላም አዉራንግባድ ሱፊ እስልምናን ይዘዉ እንደመጡና በግዛታቸዉ ሀይማኖታዊ ዉዝዋዜን (ecstacy ወይም በተመስጦ መወዝወዝን) እንዳስተዋወቁም ይነገራል።

ማሊክ አምበር ከንጉስ ሙርታዝ ካን ዕልፈት በኋላ የዲካን ስርወ መንግስትን በመጀመሪያ በምክትል አስተዳዳሪነት በኋላም ንጉስ በመሆን በግዙፉ ሙጉል ኢምፖየር ተደምስሶ እስከወደቀበት ጊዜ ድረስ አገልግሏል።
በ 1626 በ 80 አመቱ የሞተ ሲሆን ከባለቤቱ ቢቢ ከሪማ ፈትህ ካን እና ጃንክስ ካን የተባሉ ሁለት ወንዶችን እንዲሁም ሁለት ሴት ልጆችን አፍርቶ ነበር። ወንድ ልጆቹ በኋላ እንደ አዲስ ከተሸነፉበት ተነሳስተዉ ግዛታቸዉን ለማስመለስ የጣሩ ቢሆንም፣ የአባታቸዉን የቆየ ታሪክ (legacy) ማስቀጠል ሳይችሉ ቀርተዋል። ያም ሆኖ ነዋብ ሲዲ ሀይደር፣ ነዋብ ኢብራሂም መሀመድ ያቁት እና ሌሎች አቢሲኒያዉያን በተለያዩ የህንድ ግዛቶች በተለይም በሳችን ጉጅራት ዉስጥ በአስተዳዳሪነትና ንጉስነት ግዛቶቻቸዉ በኋይል ተጠቅልለዉ ወደዛሬዋ ህንድ እስከገቡበት 1948 እ.ኤ.አ መቆየት ችለዉ ነበር።

አቢሲኒያዉያን፣ ሀበሺ ወይም ሲዲዎች ለጭቆናና ለባርነት ተብሎ ወደ ህንድ የመጡ ቢሆንም፣ በሀገሩ ከኖሩበት ከአራት መቶ አመታት በላይ ብዙዉን በስልጣን እርከን፣ በዉትድርና፣ በመንግስት አስተዳደሮች፣ በተለያዩ ሙያዎችና በሌሎችም ቦታዎች ላይ በማገልገል አሳልፈዋል።
ማሊክ አምበር ዛሬ በህንድ በሚኖሩ ሲዲ ወይም ሀበሺ በሚባሉና በማሀራሽትራ የህንድ ግዛት በተለይም በአዉራንግባድ ከተማ ህዝብ ዘንድ፣ በየአመቱ ታሪኩ ይዘከራል።

ዋቢ ምንጭ፡ ከ ቢቢሲ በ 2014 በእንግሊዘኛዉ ድህረገፁ ከዘገበዉ፣ ከ Indian Times፣ ከ ዊኪፒዲያና ከሌሎችም።