April 26, 2019

የኢሳት “ኢዲቶሪያል ቦርድ” የሰጠው መግለጫ የጉዳዩን ፍሬ-ነገር የማይገልጥ ብቻ ሳይሆን ቦርዱ ላይ የተሰነዘረውን የአፈና ትችት የበለጠ የሚያጠናክር ነው። (ሔኖክ ዋይ. ተሰማ)

አንደኛ፣ ከቦርዱ የሚጠበቀው፤ የቴዎድሮስ ፀጋዬን ቃለ-ምልልስ፣ በመጀመሪያ ለማገድ ቆይቶ ደግሞ ከግማሽ በላይ እንዲቆረጥ የወሰነበትን ምክንያት የተቋሙን የአርትኦት ደንብ እና አንቀፅ ጠቅሶ ማብራራት ሆኖ ሳለ፣ መግለጫው የሚለው ግን በደፈናው ተቋሙ የዝግጅቶችን ይዘት ገምግሞ “ቆርጦ የማስቀረት ሙሉ ስልጣን” አለው ነው። መግለጫዉ ቀጥሎ፣ “በዝግጅቱ ላይ ያሉት ጉድለቶች ለአዘጋጁዋ በተላከው ደብዳቤ ላይ በግልጽ የሰፈረ በመሆኑ፣ እዚህ ላይ ማንሳቱ ተገቢ አይሆንም” ይላል። ቦርዱ ባጭሩ የውሳኔውን ትክክለኛ ምክንያት ለህዝብ የመግለፅ ኃላፊነት እንዳለበት፤ እንዲሁም በህዝብ መዋጮ የሚተዳደርን ድርጅት እንደሚመራ አካል የግልፅነት እና የተጠያቂነት መርሆችን ማክበር እንዳለበት የተገነዘበ አይመስልም።

ሁለተኛ፣ በመግለጫው ባይጠቀስም፣ ቦርዱ ውሳኔውን ያሳለፈው ቃለ-ምልልሱ “ለአገር ደህንነት ያሰጋል” በሚል ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል። ይህች ሰበብ ከ”ፀረ-ህዝብነት” እና ከ”አሸባሪነት” ጋር ከፉኛ የምትመሳሰል በአዲስ መልክ የቀረበች የማፈኛ ስልት መሆኗ ነው።

ሦስተኛ፣ መግለጫው እንደሚለው ከሆነ፣ “ጠንካራ ባህል ያዳበረውንና ለማንም የሚዲያ ተቋም አርዓያ መሆን የሚችለውን ተቋም [ኢሳትን]፣ ከተለመደው ባህሉ ወጥቶ በጫና የሆነ ፍላጎትን እንዲፈጽም የሚያስገድድ ኢ፟ዲሞክራሲያዊ አካሄድ ነው”።

(ሀ) ይህ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከተው ራሱ በጫና የሆነ ፍላጎትን ለማስፈፀም ሲል (በማወቅም ሆነ ባለማወቅ) ርዕዮት አለሙን የምታክል ለአገሯ ብዙ ዋጋ የከፈለች፣ የተመሰከረላት ሃቀኛ ጀግና ለአገር ደህንነት የማትጨነቅ እና የምትሰራውን የማታውቅ ጋዜጠኛ ለማድረግ የሞከረውን የኢሳት ቦርድ ነው።

(ለ) “ኢዲሞክራሲያዊ አካሄድ” ከሚገለጽባቸው ዋና ዋና መንገዶች አንዱ በህዝብ ድጋፍ የቆመ አንድ ተቋም፣ የሚደግፈው ህዝብ እንደሚጠብቅበትን የግልፅነት እና የተጠያቂነት መርሆችን ማክበር አለመቻል ወይም አለመፈለግ ነው።

ኃላፊነትን በአግባቡ ሳይወጡ ከባድ የሆነን ጥፋት አድበስብሶ ለማለፍ መሞከር በማን አለብኝነት ኢሳትን የመሰለ ታላቅ የህዝብ ሀብት ለአደጋ ከመዳረግ ያለፈ ውጤት አይኖረውም።