April 26, 2019

“ኢትዮጵያዊው ሙሴ” እየተባሉ ሲቆለጳጰሱ የነበሩት ዶ/ር አብይ አህመድ ጉዞ ላይ ናቸው። ያው ጉዞ ይቀናቸው የለ። አንዱ ብድር ያሰርዙልናል፣ ሌላው ደግሞ የውጭ ምንዛሬ ይዘው ይመጣሉ ብሎ ተስፋ የሰነቀው ብዛቱ የትየለሌ ነው። ነገሩ እሳቸውም መክሊቴ “ልመና” ነው ብለዋል፣ ብዙሃኑ ቢጠብቅ አይፈረድበትም። እኔም እላለሁ እሳቸው በመክሊታቸው ይስሩ፣ መንበሩን ግን ኢትዮጵያን በቀጣይ ሺህ አመታት ሊያሽከረክር የሚችል የፖለቲካ ሃዲድ የሚያነጥፍ ለ”ኢትዮጵያዊ ሞኦ ዚዶንግ” ያስረክቡ።

ይህ የልመና እና የብድር ስረዛ ሽር ጉድ እየተደረገ ያለው ከ1949 በኋላ እንደሚሳኤል የተወነጨፈችው እዚህ ለመድረስም 70 አመት ያልፈጀባት የቻይና ሪፐፕሊክ ጉያ ስር ነው። ቻይና የማንቹ ስርወ መንግስት በ1911 ከተወገደ በኋላ በውጭ ሃይሎች ብዝበዛ እና በኢኮኖሚ ዝቅጠት፣ ፖለቲካ ቀውስ እና የእርስ በእርስ ጦርነት ስትማቅቅ የነበረች ሀገር ናት። ቻይና በኮሚኒስታዊ ስርዓት እናራምዳለን በሚሉ እና በናሽናሊስት ሃይሎች መካከል ከ1927 ጀምሮ እስከ 1949 ድረስ የእርስ በእርስ ጦርነት መከራዋን በልታለች። ቻይና ከጎረቤት ሀገራት ጋርም በተለይ ከጃፓን ጋር በጦርነት ተናክሳ ተከታክታለች።

ቻይና በተለይ 1916 እስከ 1928 ባለው ወቅት በተለያዩ ግዛቶች ተከፋፍላ በክልላዊ ገዥዎች እና ከማዕከላዊ መንግስት ፈቃድ ውጭ ግብር በማስገበር፣ የራሳቸውን አርማ፣ ገንዘብ አትመው እና ህግ አውጥተው ቻይናን ብትንትኗን አውጥተው  የኛውን “ዘመነ መሳፍንት” ታሪክ አሳልፋለች። ለሁለት ጊዜ የተነሱ የእርስ በእርስ ጦርነቶች እና ሁለንተናዊ ሀገራዊ ተቃርኖ ተደማምሮ ቻይናን ድቅቅ አድርገዋት እርዛት፣ ችጋር  ቸነፈር መገለጫዋ የነበረች የአለማችን ጭቁን ሀገር ነበረች። ይህ ሩቅ አይደለም፣ የግማሽ ምዕተ አመት ታሪክ ነው።

ታዲያ ይህ ታሪክ ከግማሽ ምዕተ አመት ባልበለጠ ጊዜ እንዴት ተቀየረ የሚለው ጥያቄ “ኢትዮጵያዊ ማኦ” ሆይ ወዴት ነህ እንድል አስገድዶኛል።

“ማኦ ዚዶንግ”

ከገጠሪቱ ቻይና እና ከድሃ ቤተሰብ የተወለደው ማኦ በአብዮታዊ ትግል በ1949 ስልጣን ከያዘ በኋላ የቻይናን ኮሚኒስታዊ ፓርቲ እየመራ የሀገሪቱን ቀጣይ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ጉዞ በምናቡ ሳለ። ለዚህም ያለመታከት በብዙ መከራ የተጠረነፈችውን ቻይና በተለያየ የለውጥ እርከን ውስጥ ድፍቆ የሚያስቀጥል የረጅም አመታት የፖለቲካ ሃዲድ አነጠፈ። ከአለማቀፍ ግንኙነት ተዋናዮች መካከል “ግለሰቦች” ከሚባሉት ውስጥ ስሙ ገኖ የሚታየው ማኦ በትግል ወቅት በ1919 አንድ ጋዜጣ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር።

The world is ours, the nation is ours, and society is ours. If we do not speak, who will speak? If we do not act, who will act? ሲል ጠይቋል።

ማኦ ስልጣን በወጣ በማግስቱ የመንግስት ስርዓቱ በህዝብ ቅቡል (political legitimacy) እንዲሆን ዋናው መሳሪያ ድህነትን መስበር ከተቻለ ብቻ አንደሆነ አመነ። የመጀመሪያውን የአምስት አመት መርሃ ግብር ከ1953-1957 በአብዛኛው የተማከለ እና የእዝ ኢኮኖሚ ሞዴልን መሰረት በማድረግ የኢንዱስትሪ ጅማሮዎችን እና የትላልቅ ፋብሪካዎች ግንባታ መሰረት ለመጣል ታስቦ የተደረገ ውጤታማ ፖሊሲን ተግብሯል።

የመጀመሪያው እቅድ ሲጠናቀቅውም ከኢኮኖሚ ፖሊሲ ያለፈ በተለይም ከሶቪየት ህብረት የሶሻሊዝም ርዕዮተ አለም የተለየ አቅጠጫ ቻይና አላት የሚል እሳቤውን በሚያሳይ መልኩ “The Great Leap Forward” የተሰኘውን ሁሉ አቀፍ ንቅናቄ 1958 እስከ 1962 መተግበር ጀመረ።  የንቅናቄው ዋና አላማም የቻይናን ግብርና መር ኢኮኖሚ በፈጣን እና ተቀጣጣይ የኢንዱስትሪ ኢኮኖሚ ለመታካት ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ንቅናቄ ብዙ ዋጋ ያስከፈለ፣ ብዙም ውጤታማ ያልሆነ፣ ይልቁንም ከ18 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያለቀበት እና ቻይናን ለከባዱ የቻይና ቸነፈር “Great Chinese Famine” ለሶስት አመት እንድትመታ አስታዋጽኦ እንዳደረገ የታሪክ መዛግብቶች ያስረዳሉ

ማኦ ሌላውን ሪፎርም ቀጠለ የቻይና የባህል አብዮት “The Cultural Revolution”  ከ1966 እስከ 1976 በዋናነት የማህበረሰባዊ እና የፖለቲካ ለውጥን መሰረት አድርጎ ትልቅ ንቅናቄ በቻይና ምድር አወረደ።  ይህ አብዮት ቀደም ሲል በተተገበረው ንቅናቄ የደረሰውን ጉዳት እና  ተቀባይነቱ የቀነሰው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ እንደገና እንዲያገግም እድል የሰጠ ነበር።    የቻይናውያን “ሁሉ በል” የአመጋገብ ባህልም መሰረቱን የጣለው እና እኛ “እሯ” እያልን  ይምንጠየፋቸውን ምግቦች፣ ሳር ቅጠሎች፣ አረሞች፣ የዱር አራዊት፣ ነፍሳት ሳይቀር  እንክት አድርጎ መብላት እንደሚቻል አቅጣጫ ያሳያቸው ያው “የቻይና አባት” ማኦ ዚዶንግ ነበር።

ማኦ ቻይና አለምን እንደምታስደምም ጠንቅቆ ያቅው ነበር። አፍሪካ እና አጠቃላይ ታዳጊ ሀገራት (the global south) የምንላቸው የቻይና ሸቀጦች ማራገፊያ እንደሚሆኑ ጠንቅቆ ያውቀው ነበር። ቻይና ሃያላን ሀገራትን ጥላቸው እንደምትሄድ ይታየው ነበር። ዛሬ www.pwc.com ድረገጽ ባደረገው ትንበያ በ2050 ቻይና የአለማችን ሃያል ሀገር (hegemonic power) እንደምትሆን በተቃራኒው አሜሪካ ተንሸራታ አራተኛ እንደምትሆን ያስነብባል።

ይህ ሁሉ የለውጥ ግስጋዜ ማኦ በ1919 “አለም የኛ ናት፣ ሀገሪቱ የኛ ናት፣ ማህበረሰቡ የኛ ነው፤ እኛ ካልተናገርን ማን ይናገር፤ እኛ ካልተገበርን ማን ይተግብርልን።” ሲል ያስቀመጣት ከውስጥ ወደ ውጭ የምትረጭ ዘመን ተሻጋሪ እና ሁሉ አቀፍ እይታ ዛሬ እውነት ሁናለች።

የኛዋ ሀገርም “ኢትዮጵያዊ ማኦን” ትሻለች። “ኢትዮጰያዊ ማኦ” ሆይ ቢሻህ ኩስምን ካለው የድሃ ገበሬ ቤት፣ ብትፈልግ ንጥጥ ካለ የሃብትም ቤት፣  ከሆንም ከምሁር እንዲያው ከማንም ተወለድ እባክህ ና እና፦

ኢትዮጵያ ዘመን ተሻጋሪ የሚያስፈነጥር (leapfrogging) ስትራቴጂ እና እቅድ ያስፈልጋታል። ይህ ከሆነ እንደ ማክስ ቬበር (Max Weber) ያሉ ሶሾሎጂስቶች እና ፈላስፎች እንደሚሉት ዘረኝነት፣ ጎሰኝነት እና ጥቃቅን እሳቤዎች እየከሰሙ ይሄዳሉ።  ኢትዮጵያውያን የጋራ ሰንደቅ፣ የጋራ ራዕይ፣ የጋራ ህልም እንዲኖራቸው “ኢትዮጵያዊ ማኦ” ያስፈልጋታል።

“ኢትዮጵያዊው ማኦ ዚዶንግ” ሆይ ወዴት ነህ?

“አካዳሚክ ኑዛዜ”

ለጽሁፉ የሚከተሉትን እና ሌሎች ድረገጾችን ተጠቅሜያለሁ። በጽሁፉ ላይ ያሉ አመተ ምህረቶች የግሪጎሪያን አቆጣጠር ናቸው።

Sponsored by Revcontent