April 27, 2019

ከእውነት ሸሽቶ የፖለቲካ አክሮባት መስራት የማታ ማታ እኛን ለትዝብት ሕዝቡን ለጉዳት ይጥላል።

አቶ አዲሱ አረጋ ከእውነት ጎን ይቁሙ፤ “የቡርቃ ዝምታ” ተራ የሀሰት ልብ ወለድ መሆኑንም መመስከርዎትን ይቀጥሉ!
(በአሰማኸኝ አስረስ)

Image may contain: 1 person, suit and closeup

ሰሞኑን የአማራና የኦሮሞ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መካሄዱ ይታወቃል፡፡ ይህ ጉዳይ መሰንበቻውን በበርካታ አውዶች ውስጥ እየገባ ሲተነተን ቆይቷል፡፡ በተለይ በማሕበራዊ ሚዲያው ውስጥ ከፍ ያለ ትኩረትን አግኝቶ ሰንብቷል፡፡ የግንኙነት መድረኩን በማድነቅ እና በመደገፍ የተሰነዘሩ ብዙ ሀሳቦች ነበሩ፡፡ ግንኙነቱ የተካሄደበትን መንገድ እና አንዳንድ ይዘቶችን አብዝተው የነቀፉም ነበሩ፡፡ በትችት ሲነሱ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ፡- “የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝቦች መካከል ምንም ጥል ስለሌለ እንዲህ አይነት መድረኮች የመንግስትን ስልጣን ለማራዘም ሆን ተብለው የሚታቀዱ ናቸው” የሚለው ዋናው ነበር ማለት ይቻላል፡፡

እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት… በመሰረቱ ይህ መድረክ ያስፈለገው የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች ስለተጋጩ አይደለም፤ አንድ ሕዝብ ከሌላ ሕዝብ ጋር ተጋጭቶ አያውቅም፤ አይጋጭምም፡፡ በዚህ የፖለቲካ ልሂቃንና አመራሮች ሴራና የብልጣብልጥነት ቁማር በበዛበት ወቅትም ቢሆን እንኳን የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች አልተጣሉም፤ አይጣሉም፡፡ የእነዚህ ሁለት ታላላቅ ወንድማማች ሕዝቦች መልካም ግንኙነት እኛ የፈጠርነው አይደለም፡፡ በእኛ ፍላጎት ወይም ሴራ የሚላላም ሆነ የሚበጠስ የአንድነት ገመድም የላቸውም፡፡ የአንድነታቸው ገመድ በደም እና በአጥንት የተጎነጎነ ነው፡፡ ተዋልደው ተዋሕደዋል። በሰው ሰራሽ ሴራ ላይለያዩ በተፈጥሮ ተጋምደዋል።

ይሁንና በተለይ ባለፉት ሦስት ዐሥርት ዓመታት ሁለቱን ሕዝቦች ለማጋጨት ብዙ በሴራና በተንኮል የተጠኑና የተቀመሩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ከተግባራቱ መካከል አንዱን አንስቼ ወደ ኋላ እመለስበታለሁ፡፡
.
የሁለቱን ሕዝቦች ዘላቂ አብሮነትና የጋራ ፍትሐዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን በተሰራበት ሴራ ከተቀዛቀዘበት መንፈስ በመቀስቀስ ወደ ተሻለ ትብብር መመለስ እና ወደ ላቀ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ለማስተባበር ደግሞ አሁን ስልጣን ላይ ያሉት የክልል መንግስታት የማስተባበር ታሪካዊ ኃላፊነት አለባቸው ብየ አምናለሁ፡፡ የተደረገውም ይኸው ነው፡፡ እንደ አማራ ክልል ከኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ጋር ያደረግነው ይህ ግንኙነት፣ በመጠን ወይም ጥልቀት ይለያይ እንደሆነ እንጂ በአይነቱ ግን ልክ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል እና ከአፋር ክልል ጋር ካደረግናቸው ግንኙነት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ወደፊትም ከጎረቤቶቻችንም ሆነ ከሌሎች ክልሎች ጋር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማድረጋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ለአማራ ሕዝብ የሚጠቅም ነው ብለን እስካመንን ድረስ ከሕዝባችን ጋር እየተመካከርን ከሁሉም የሀገሪቱ ሕዝቦች ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረን እንሰራለን፡፡

እንዲህ አይነት ግንኙነቶችን ስንፈጥር የምንመሰረተው በመርህ እና እውነት ላይ ነው፡፡ እኛ ከሀቅ ጋር የተፋታን አይደለንም፡፡ እውነት ተናግረን፣ ስለ እውነት መስክረን የሚመጣውን ዋጋ እስከ መስዋዕትነት ድረስ እንከፍላለን፡፡ ይህ የአማራ ሕዝብ ያስተማረን እሴት ነው፡፡ ‘መኖርም ለማተብ፤ መሞትም ለማተብ’ ከሚለው አማራ ነው የተወለድነው፡፡

ወደቀደመ ነገሬ ስመለስ በአማራ እና ኦሮሞ የሕዝብ ለሕዝብ መድረኮች ላይ ከቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች መካከል የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦችን ግንኙነት ታሪካዊ ዳራ መነሻ በማድረግ የቀረበው ሰነድ ይጠቀሳል፡፡ አቅራቢው የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ አዲሱ አረጋ ነበሩ፡፡ በእለቱ አንድ እውነት ተናገሩ፡፡ የሁለቱን ሕዝቦች ግንኙነት ለማሻከር በሚፈልጉ አካላት ድጋፍ የሀሰት ትርክቶች እንደተፈበረኩ፤ በይዘታቸው መርዝ ያዘሉ መጽሐፍት ጭምር እንደተደረሱ እና ለትውልዱ በከፍተኛ ቅጂ እንደተባዙ ጭምር አስረግጠው ሐቁን ገለጡ፡፡ የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝቦችን ሆን ብለው ለማጋጨት ከፍተኛ ገንዘብ መድበው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች እንደነበሩም አሰመሩበት፡፡ እነዚህ ኃይሎች የሀሰት ትርክቶች በመጽሐፍ መልክ እንዲታተሙ እና ለሕዝቡ እንዲሰራጩ በማድረግ የአማራና እና የኦሮሞ ሕዝቦችን በጥርጣሬ እንዲተያዩ ማድረግ እንደቻሉም አብራሩ፡፡ እንደምሳሌም በኤርትራዊው ተስፋዬ ገብረአብ የተጻፈውን የቡርቃ ዝምታ የተሰኘውን ልብ ወለድ አንስተው አስረዱ፡፡ ይህን ንግግራቸውን አዳራሹ ውስጥ የታደመው የአማራም የኦሮሞም ሕዝቡ በጭብጨባ ተቀብሏቸዋል፡፡

ይህን አድንቀን ሳናበቃ ግን ከጥቂት ሰዓታት በኋላ፣ (ይህ ምስክርነታቸው በሚዲያ ከተላለፈ በኋላ) አቶ አዲሱ አረጋ ከጽንፈኛ ኃይሎች ከፍተኛ ውግዘት ደረሰባቸው፡፡ እውነትን ቢናገሩም፣ ስለ እውነት ግድ የማይለው ጽንፈኛ ኃይል ቀፎው እንደተነካ ንብ ተንጫጫባቸው፡፡ ገንዘብ መድቦ ሁለቱን ሕዝቦች በማባላት የፖለቲካ ትርፍ ሲያጋብስ የነበረው ኃይል የቡርቃ ዝምታን የመሰለ የሁለቱም ሕዝቦች ማጋጫ ልብወለዳዊ የሀሰት ትርክት ለምን ተነካብኝ ብሎ ተቆጣ፡፡ በዚህ ጊዜ አንድ ጠንካራ ፖለቲከኛ በእውነት እና ስለ እውነት መቆም ብቻ ነው ነበር ምርጫው፡፡

በግሌ አቶ አዲሱ ይህንን እውነት አምነውበት፣ የድርጅት አቋም አድርገውት እና በየደረጃው መግባባት ተደርሶበት የተናገሩት እና እስከመጨረሻው ይዘውት የሚቀጥሉ ሐቅ መስሎኝ ነበር፡፡ የአማራ ሕዝብ ስለ እውነት ሲናገር፡- “እውነት ትቀጥን እንደሁ እንጂ አትበጠስም” ይላል፡፡ ፖለቲካችን፣ የምንገነባው አገር እና ለትውልድ የምናስተላልፈው ትርክት ከእውነት ጋር የታረቀ ካልሆነ ተሸንፈናል፤ ከስረናል፡፡ የሕዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጠው በእውነት ላይ ስንቆም ብቻ እንደሆነ አምናለሁ፤ ነውም፡፡ አቶ አዲሱንም በዚህ እምነቴ ውስጥ አስቀምጫቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ተቃውሞው ሲበረታባቸው ያሉትን ሁሉ ትተው ከሰዓታት በኋላ “የተናገርኩት ውሸቴን ነው፤ እንዲህ ለማለት ፈልጌ አይደለም፤ እባካችሁ ይቅር በሉኝ” እንዳሉ ስሰማ በድንጋጤ ሐፍረትም ተሰማኝ፡፡ የብልጣብልጥነትና የማታለል ዓይነት ስሜት እንደተሰማኝም መደበቅ አልፈልግም።

እርግጥ ሕዝብ አይሳሳትም፡፡ ጥቂት ሰዎች ግን ባልሆነ መረጃ ተሳስተውና ሕዝቡንም ለጊዜው አደናግረው ወደ ስሜት ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ሕዝቡ የተረዳ እለት ግን ተመልሶ ዝቅ ያረገውን እውነተኛ መሪ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ይህንን ነው የማምነው፡፡ የቡርቃ ዝምታ ተስፋዬ ገብረ አብ በገንዘብ ተደልሎ የፈበረከው የፈጠራ ትርክት ነው፡፡ የቡርቃ ዝምታ መሬት ላይ ካለው እውነቱ ጋር የማይታረቅ ሀሰተኛ ልቦወለድ ነው፡፡ በቡርቃ ዝምታ የተገነባው አኖሌም ወደፊት በሀሰት ሀውልትነቱ በታሪክ ሲወሳ የሚኖር የጥላቻ ፈብራኪዎች መታሰቢያ ነው፡፡ በሀሰት ላይ የተገባ ሀውልት ከዚህ የተለየ ነገር አይኖረውም።
.
እናም አቶ አዲሱ አረጋ፣ እርስዎ እውነቱን ስለተናገሩ ተቃውሞ ቢደርስብዎትም እንኳን፣ ይህም ስልጣንዎትን ሊያሳጣዎት ቢችል እንኳን፣ ለዚሁ ምንም ዓይነት መስዋዕትነት መክፈል አስፈላጊ ቢሆንም እንኳን ስለ እውነት ብለው ከእውነት ጎን ሊቆሙና ለሁለቱ ሕዝብ ሲሉ የሚመጣውን ሊቀበሉ ይገባ ነበር ብየ አምናለሁ፡፡
ከእውነት በመሸሽ የፖለቲካ አክሮባት መስራት የማታ ማታ ሕዝቡን ለጉዳት እኛንም ለትዝብት ይጥለናል እንጅ ሌላ ትርፍ የለውም፡፡ አሁንም አልረፈደም። አቶ አዲሱ አረጋ ከእውነት ጎን ይቁሙ፤ “የቡርቃ ዝምታ” ተራ የሀሰት ልብ ወለድ መሆኑንም መመስከርዎትን ይቀጥሉ! ሁላችንም ከሐቅ ጎን በመቆምና ለሕዝብ የሚበጀውን ፖለቲካ በመጫወት ለሀገራችን መልካም መፃኤ ዕድልን ለሕዝባችንም ፍቅርና አንድነትን እውን ልናደርግ እንጅ ገና ለገና ተቃውሞ ገጠመን ብለን ከሐቁ ልንሸሽ አይገባም።
መልካም በዓል!

መልካም በዓል!

ከእውነት ሸሽቶ የፖለቲካ አክሮባት መስራት የማታ ማታ እኛን ለትዝብት ሕዝቡን ለጉዳት ይጥላል።

አቶ አዲሱ አረጋ ከእውነት ጎን ይቁሙ፤ “የቡርቃ ዝምታ” ተራ የሀሰት ልብ ወለድ መሆኑንም መመስከርዎትን ይቀጥሉ!
(በአሰማኸኝ አስረስ)
….See More