Source: https://fanabc.com
April 28, 2019

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 20 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የሱዳን የሽግግር ወታደራዊ ምክር ቤት እና ተቀናቃኝ ፓርቲዎች አዲስ አስተዳደር ለማቋቋም በመርህ ደረጃ መስማማታቸው ተነገረ።
በስምምነታቸው መሰረትም የጋራ ምክር ቤት እንደሚያቋቁሙ ተነግሯል።
የሚቋቋመው አስተዳደርም ቀጣዩ የሃገሪቱ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ሃገሪቱን የሚመራ ይሆናል።
ይሁን እንጅ ከስምምነቱ ባለፈ ትግበራው ላይ ልዩነቶች እንዳሉ እየተነገረ ነው።
ሁለቱ አካላት ይቋቋማል ከተባለው ምክር ቤት ምስረታና የአባላት ቁጥር ጋር በተያያዘ ልዩነቶች ማንጸባረቃቸው ተሰምቷል።
ወታደራዊ ምክር ቤቱ 10 አባላት ያሉት ምክር ቤት እንዲመሰረትና 7ቱ ወታደራዊ ሶስቱ ደግሞ ከሲቪሉ እንዲሆን ይፈልጋል።
በአንጻሩ ተቀናቃኞች 15 አባላት ያሉት ምክር ቤት እንዲቋቋምና 8 ከሲቪል 7 ደግሞ ከወታደራዊ ምክር ቤቱ እንዲሆኑ ፍላጎት አሳይተዋል።
ስምምነቱ መልካም ቢባልም እነዚህ ልዩነቶች ግን የምስረታው እውን መሆን ላይ ጥያቄን አጭረዋል።
ሁለቱ ሃይሎች ከስምምነት ከደረሱ እስከ ምርጫ ቀኑ ድረስ ቀጣዩን ሁለት አመት በጋራ ሃገራቸውን ይመራሉ ተብሎም ይጠበቃል።
ምንጭ፦ አልጀዚራ