April 29, 2019
Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሞና የሶማሌ ህዝቦችን አንድነትንና ወንድማማችነትን ለማጠናከር ያለመ የህዝብ ለህዝብ ኮንፈረንስ በአዳማ ከተማ እንደሚካሄድ የኦሮሚያ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው እንደገለጹትኮንፈረንሱ የኦሮሞና የሶማሌ ህዝቦችን ወንድማማችነት በማጠናከር በሰላም፣በልማትና በአገር ግንባታ ውስጥ እያበረከቱ ያሉትን ሚና ለማስቀጠል የታለመ ነው።
መድረኩ ሁለቱ ህዝቦች የጋራ አኩሪ እሴቶቻቸውን ለአገራዊ አንድነትና ለውጥ ትርጉም ባለው መልኩ ለመተግበር እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
ኪራይ ሰብሳቢ አመራሮችና ጥቅማቸው የተነካባቸው አካላት የወሰን አስተዳደርን እንደ ሽፋን በመጠቀም በፈጠሩት ብጥብጥና ሁከት በሁለቱም ወገን ለሰው ህይወት መጥፋት፣ለንብረት ውድመትና ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት መሆኑን ሃላፊው አስታውሰዋል።
የክልሎቹ የለውጥ አካላትና የፌዴራል መንግሥት ተባብረው በመስራት ችግሮቻቸውን ማስወገዳቸውንም ነው አቶ አድማሱ የተናገሩት።
በአሁኑ ወቅት በአዋሳኝ አካባባቢዎች ችግሮቹን ሙሉ በሙሉ መፈታታቸውን በመግለጽ ኮንፈረንሱ ህዝቦቹ በልማትና መልካም አስተዳደር ለማስተሳሰር ሚና እንዳለው ነው ተናገሩት።
መድረኩ ከሁለቱም ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቄያቸው ለመመለስና አስተማማኝ ሰላም ያሰፍናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል ብለዋል።
በልማት፣በፍትህና መልካም አሰተዳደር ህዝቡን ለመካስ የሚያስችል የጋራ መሠረት የሚጣልበትና እርቀ ሰላም የሚወርድበት መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።
በኮንፈረንሱ ለመሳተፍ ከሶማሌ ክልል ወደ አዳማ የሚመጡ እንግዶችን ከነገ ጀምሮ በሐረር፣ በባሌና በቦረና ላይ አቀባበል እንደሚደረግላቸው አስታውቀዋል።
በኮንፈረንሱ ላይ የሁለቱን ህዝቦች እንድነት የሚያጠናክሩ፣ የጋራ ታሪካቸውን የሚዳስሱና በሀገር አንድነት ግንባታ ውስጥ በነበራቸው ሚና ላይ የሚያተኩሩ ጽሑፎች በምሁራን እንደሚቀርቡ አስረድተዋል።
በባህል፣ በቋንቋና በሌሎች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥናታዊ ጽሑፎች የውይይቱ አካል መሆናቸውንም አቶ አድማሱ አብራርተዋል።
በኮንፈረንሱ ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዑጋዞች፣ አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ምንጭ ፡- ኢ ዜ አ