ፍርድ ቤት እስከ ፖሊስ፣ ልዩ ሃይል ወዘተ የተባሉ ህግ አስከባሪ አካላት በዘር ተመልምለው እስከተመደቡ ድረስ ከእነሱ ዘር ያልሆነ ሰው በሰላም ይኖራል ማለት ዘበት ነው፡፡እነዚህ የዘር ህግ አስከባሪዎች ሌላውን ሰው ከዘራቸው እኩል አይተው ከለላ ይሆናሉ ማለትም የሞኝነት ምልክት ነው፡፡በመተከል እየሆነ ያለው እጅግ አሳዛኝ ሁነት የዚህ አካሄድ ውጤት ነው፡፡

መተከል በተነሳው ግጭት አስራ ሰባት ሰው መሞቱን እና ሃያ አምስት ቤት መቃጠሉን ራሳቸው የአካባቢው ሹማምንት እና የአማራ ክልል ባለስልጣናት ለቢቢሲ አማርኛው ዝግጅት ክፍል ተናግረዋል፡፡ነገሩ ቶሎ በቁጥጥር ስር ሊውል እንደማይችልም እለው ገልፀዋል፤ ምክንያታቸው ደግሞ ሰው ሰው ዘርዘር ብሎ ስለሚኖር በቆጣጠሩ ስለሚያስቸግራቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ዘር ለይቶ የሚደረገው እጅግ አሰቃቂ ግድያ ደግሞ የዘር ፖለቲካው አስቀያሚ ገፅታ ውጤት መሆኑ ቀርቶ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊት እንሆነ ነው ሹማምንቱ የሚናገሩት፡፡የዘር ፖለቲካ ራሱ ጎጅ ልማድ ነው እያሉ ይሁን ወይስ ስልጣን ላይ ቂብ ያረጋቸውን የዘር ፖለቲካ ላለማሳጣት ይሁን ዳርዳርታው ግልፅ አይደለም፡፡ምን ቢያሽሞነሙኑት የዘር ፖለቲካ እንደሁ ትርፉ ሬሳ ነው፡፡ይህን እውነት ለመደበቅ የሚጋጋጡት ካድሬዎች ራሳቸውን ያስገምታሉ እንጅ ትርፍ የለውም፡፡ከሁሉ አሳሳቢው ነገር ግን ይህ ሁሉ ጥፋት ሲደርስ ክልሉን የሚያስተዳደረው መንግስት ነገሩን በቁጥጥሩ ስር ለማዋል ያልቻለው የሃገራችን የፀጥታ አካላት ቀስት ከሚወረውሩት መጤ ጠል ሰዎች የተለየ እሳቤ የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡
የፀጥታ አካላት ቀርቶ ርዕሰ መስተዳድሮችን ጨምሮ የሃገራችን ክልሎች ቁንጮ ካድሬ ባለስልጣናት ራሳቸው መጤ ያለውን ሊገድል “ሆ!” ብሎ ከሚወጣው ዘር ያንዘረዘረው ጎረምሳ የተለየ እሳቤ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ሰው በዘሩ ምክንያት በአሰቃቂ ሁኔታ ከሞተ በኋላ ለቤተሰብ መፅናናትን ሊመኙ የሚመጡ እነዚህ ተመፃዳቂ ባለስልጣናት በኩራት በየቴሌቭዥኑ ሲመጡ ምንም ያጠፉ የማይመስላቸው መሆኑ እጅግ የሚያሳስብ ነገር ነው፡፡ከዘመነ መለስ ዜናዊ በፊት የጎጃም ምድር በነበረው የመተከል ግዛት መጤ ተብሎ በቀስት የሚፈጀው የአማራ ተወላጅ የመገፋቱ ብዛት የሚያመጣው ቁጣ ማብረጃው ከወዴት እንደሆነ ባለቀስቶቹ ያሰቡበት አይመስልም፡፡
ቀልበን ያሳደግነው የዘር ፖለቲካ የተባለ አውሬ የማይነክሰው አይኖርም…..! የዘር ፖለቲካ ከተባለ አውሬ ጋር ያዋደደን የፖለቲካ አባዜ የት እንሚያደርሰን ማንም አያውቅም ….