April 30, 2019

Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ፣ ሚያዚዸያ 22፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጰያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ ኃላፊነቱን ለማስረከብ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ።

ስራ አስፈጻሚዉ ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ ለሰላም እና ህዝበ ሙስሊሙ አጥብቆ ለሚሻዉ አንድነት ሲባል ነገ በሚካሄደዉ የኡለማዎች የምክክር መድረክ ላይ በሚቀመጠዉ አቅጣጫ መሰረት ሀላፊነቴን አስረክባለሁ ብሏል።

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼህ መሀመድ አሚን ጀማል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት ሁሉም የስራ አስፈጻሚ አባላት ኃላፊነታቸውን ለማስረከብና ለአንድነት የተጀመረዉን ለዉጥ ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ትላንት የምክር ቤቱ 15ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዶ በአቋም መግለጫው እንደተገለጸዉ ሁሉ፤ ኡለማዎች በሚያስቀምጡት አቅጣጫ በየትኛዉም ሰዓት ለማስረከብ ስራ አስፈጻሚው ከስምምነት ላይ መድረሱን እና በምክክር መድረኩ ላይ ለሚነሱ የመፍትሄ ሃሳቦች እና ለሚቀመጠዉ አቅጣጫ ተገዥ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ አንድነት የጋራ ኮሚቴ ባቀረበዉ ምክረ ሀሳብ ነገ ለሚካሄደዉ የምክክር መድረክም ከወዲሁ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን እና ለበርካታ ኡለማዎች ጥሪ መደረጉንም ተናግረዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸዉ ኡለማዎችም የነገዉ መድረክ ለሙስሊሙ አንድንትን ለማምጣት የሚጠቅም መሆኑን ተናግረዋል።

ነገ በሸራተን አዲስ የሚካሄደዉ የኡለማዎች የምክክር መድረክ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አቀራራቢነት ለተቋማዊ ለዉጥ እና አንድነት የተቋቋመዉ ኮሚቴ ባቀረበዉ ምክረ ሀሳብ የሚካሄድ ነዉ።

በመድረኩም ከ300 በላይ ኡለማዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ፣ለሰላም እና ለሙስሊሙ አንድነት የታገሉ ግለሰቦች ይሳተፋሉ።

በሀብታሙ ተክለስላሴ