May 1, 2019
Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 23 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) ሙስሊሙ ህብረተሰብ አጥብቆ የሚፈልገውንና የአስተምህሮው ማእከል የሆነውን ሰላም ለማምጣት እየተካሄደ የሚገኘው ጉባኤ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ።
በሸራተን አዲስ “የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ እና የአንድነት ሀገር አቀፍ ስብሰባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በዚህ የኡለማዎች ጉባኤ ላይ በመገኘትም ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው በሙስሊሙ መካከል የሌለውን አንድነትና ሰላም በሀገሪቱ ላይ ልናገኝ አንችልም፤ ስለሆነም ለአንድነት ወሳኙን መድረክ መጠቀም ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
እምነት ሰላምን ቢያስተምርም አንዳንዶች የጥፋት መሳሪያ ሊያደርጉት እንደሚችሉ በማንሳት፥ የትኛውም አስተሳሰብ ሌላውን ሳይገፋ ነፃ ሆኖ ተከታዬቹን ወደ አንድነት መጥራት አለበት ብለዋል።
ህዝበ ሙስሊሙ የሚያነሳቸው ችግሮች ለዘመናት የተጠራቀሙ በመሆናቸው በአንድ ቀን ሁሉም ነገር ሊቀየር እንደማይችል በማመን ሰፊና ተሻጋሪ መሰረት ለመጣል መንቀሳቀስ ይገባልም ነው ያሉት።
ችግሮቹም በቅደም ተከተል ይፈቱ ዘንድ አቅጣጫ እንዲቀመጥም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጥሪ አቅርበዋል።
በእስካሁን ሂደት ያጠፉ፤ ያሳዘኑ ሊኖሩ ይችላሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በእምነቱ እንደተቀመጠው ሁሉ ይቅር ተባብሎ የአንድነት ጉዞን መጀመር ይገባል ብለዋል።
በትንንሽ ጉዳዬች በመጠላለፍም ታላቁን እምነት እና ተከታዬቹን ከማሳነስ እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ አንድነት የጋራ ሰብሳቢ የሆኑት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ኡመር ኢድሪስ ባደረጉት ንግግርም ቀኑ ለህዝበ ሙስሊሙ አንድነት ወሳኝ በመሆኑ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።Filed in:Uncategorized