1 May 2019

ዮሐንስ አንበርብር

ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ለማዘዋወር መንግሥት በወሰነው መሠረት የተቋሙን አጠቃላይ ሀብቱን ኦዲት በማደረግ የሀብት መጠኑን ለማወቅ፣ ፕራይስ ወተር ሃውስ ኩፐር (PWC) የተሰኘ የእንግሊዝ አማካሪ ኩባንያ ተቀጥሮ ሥራ መጀመሩ ታወቀ።

ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ኩባንያ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የቀደመ የሥራ ግንኙነት እንዳለው የገለጹት የሪፖርተር ምንጮች፣ ተቋሙን በጥልቀት የማወቅ ዕድል ቀድሞ ነበረው ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት  በዓለም አቀፍ ደረጃ አሉ ከተባሉት ዕውቅና ያተረፉ አማካሪ ኩባንያዎች መካከል አንዱ በመሆኑ፣  የሀብት ግመታ ግኝቱ ተቀባይነት እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልጸዋል።

ይህ ኩባንያ ከጥቂት ዓመታት በፊት የኢትዮ ቴሌኮምን የፋይናንስ አስተዳደርና ዘመናዊ የሒሳብ አያያዝ ሥርዓት ማደራጀቱንም አክለዋል።

ግዙፍ የመንግሥት ተቋማትን ሙሉ በሙሉና በከፊል ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር በተወሰነው መሠረት፣ አፈጻጸሙን የሚከታተል ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙ ይታወቃል፡፡ ይህ ኮሚቴ ሚያዚያ 14 ቀን 2011 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተሰብስቦ ከዚህ ቀደም የተደረሰበትን የፕራይቬታይዜሽን ውሳኔ ወደ ተግባር ለመለወጥ እየተደረገ ያለውን ዝግጅት የተመለከተ ሪፖርት ቀርቦ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ግምገማ መካሄዱን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የፕራይቬታይዜሽን ሒደት ዝግጅቶችንና አፈጻጸም እንዲመራ በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር የተቋቋመው ንዑስ ኮሚቴ አባል የሆኑት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ እየተደረጉ ያሉትን ዝግጅቶች የተመለከተ አጠቃላይ ሪፖርት አቅርበዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በወቅቱ ባቀረቡት ሪፖርትም የኢትዮ ቴሌኮምን አጠቃላይ ሀብት ለመገመት፣ የውጭ አማካሪ ድርጅት ተቀጥሮ ሥራው መጀመሩን አረጋግጠዋል።

የሀብት ግመታ ሥራውም ከሁለት እስከ ስድስት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አስረድተዋል።

ከዚህ ኩባንያ በተጨማሪ ዲሊዮት የተባለ ሌላ የእንግሊዝ ኩባንያና ኧርነስት ኤንድ ያንግ የተባለ የአሜሪካ ኩባንያ ደግሞ የሀብት ግመታው መጠናቀቅን ተከትሎ የሚከናወነውን የአክሲዮን አወቃቀርና ሽያጭ በተመለከተ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን ለማማከር መቀጠራቸውን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በተጨማሪም ሜከንዚ የተባለ ሌላ የአሜሪካ አማካሪ ድርጅት ደግሞ እንደ አዲስ የሚዋቀረውን የቴሌኮም ገበያ ለመቆጣጠር የሚያስፈልገውን ዝግጅትና መፈጠር ያለበትን ተቋማዊ ሥርዓት በተመለከተ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን የማማከር ኃላፊነት መውሰዱን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የተቀጠሩትን የውጭ አማካሪ ድርጅቶች አጠቃላይ ወጪ የዓለም ባንክና ሌሎች የምዕራብ አገሮች መንግሥታት እንደሚሸፍኑም ለማወቅ ተችሏል።

በኢትዮጵያ በመንግሥት ባለቤትነት በብቸኝነት ተይዞ የቆየውን የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ዘርፍ ለውድድር ክፍት የሚያደርግ፣ ማናቸውም የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ የግል ከባንያዎች ፈቃድ አውጥቶ በቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎቶች ውስጥ በጤናማ የውድድር መርህ መሳተፍ እንዲችሉ የሚፈቅድ ሕግ ተረቆ፣ በአሁኑ ወቅት በፓርላማው በዝርዝር በመታየት ላይ የሚገኝ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

ይህ ረቂቅ ሕግ የቴሌኮም ገበያውን እንደገና እንደ አዲስ የሚያዋቅር፣ ፈቃድ የሚሰጥና የቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፍን የሚቆጣጠር የኢትዮጵያ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኤጀንሲን የሚያቋቋም ይሆናል።

በመሆኑም መንግሥት ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ለመሸጥ ከጀመረው ዝግጅት በተጨማሪ፣ ሌሎች የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ የግል ኩባንያዎች የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎቶችን በማቅረብ በሚፈጠረው ገበያ እንዲወዳደሩ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ፣ ፓርላማው በዝርዝር እየተመለከተ የሚገኘው ረቂቅ ሕግ ማሳያ ነው።