ፖለቲካ | May 01

መነሻ ገጽ
ኢሠማኮ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች የሠራተኞችን የሥራ ዋስትና ሥጋት ውስጥ እየከተቱ ነው አለ
የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ

ፖለቲካ

ኢሠማኮ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች የሠራተኞችን የሥራ ዋስትና ሥጋት ውስጥ እየከተቱ ነው አለ

1 May 2019 ዳዊት ታዬ

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተፈጠሩ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች የሠራተኞችን የሥራ ዋስትና ሥጋት ውስጥ በመክተት፣ ተዘዋውረውና ተረጋግተው እንዳይሠሩ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) አስታወቀ፡፡

ኢሠማኮ ረቡዕ ሚያዝያ 23 ቀን 2011 ዓ.ም. የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን በማስመልከት በሰጠው መግለጫ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ማሻሻያዎችን ለማድረግ እየሠራ ቢሆንም፣ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ሠራተኞች ሠርቶ ለመግባት፣ ተረጋግተው ለመሥራትና ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር ችግር እየገጠማቸው ነው ብሏል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ለአገር አንድነት፣ ለሠራተኛው መደራጀትና ሁለንተናዊ ዕድገት መሥራት የሚችለው ሰላም ሲፈጠር ብቻ መሆኑን አስታውቋል፡፡

መግለጫውን በተመለከተ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች በሥራ ላይ የነበሩ ድርጅቶችን እንቅስቃሴዎቻቸው እስከ መግታት በመድረሳቸው፣ የሠራተኞች የሥራ ዋስትና አደጋ ውስጥ ነው ብለዋል፡፡

አሁንም ሠራተኞችን የሚያሳስቡ ችግሮች ሙሉ ለሙሉ ያልተፈቱባቸው አካባቢዎች እንዳሉ፣ አቶ ካሳሁን በሰጡት ማብራሪያ አስረድተዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ባለሀብቶች ያለሙትን መሬት እንከፋፈላለን በማለት የተፈጠረ ችግር እንደነበር የጠቆሙት አቶ ካሳሁን፣ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ባለሀብቶች ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ ለማቅረብ የተፈተኑባቸውና የተዘረፉባቸው አጋጣሚዎች እንደነበሩም አስታውሰዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ችግሮች የሠራተኞችን ሠርቶ የመኖር መብት የሚፈታተኑ በመሆናቸው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ከመንግሥት ጋር በመነጋገር እንዳይደገሙ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የባለሀብቶችን መሬት ለመከፋፈል የተደረገውን ሙከራና በዚሁ ምክንያት ሥራቸው ተቋርጦባቸው የነበሩ ድርጅቶችን ጉዳይ፣ ከክልሎች ባለሥልጣናት ጋር በመመካከር ሊፈጠር ይችል የነበረውን አደጋ ለማርገብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ አሁንም እንዲህ ያለው አካሄድ እንዳይደገምና የሠራተኞች የሥራ ዋስትና አደጋ ላይ እንዳይወድቅ፣ ሁሉም ወገን የራሱን ኃላፊነት እንዲወጣ ማድረግ የግድ ነው ብለዋል፡፡ ይኼም በዘንድሮው ሜይ ዴይ ቀን ድምፃቸውን ከሚያሰሙባቸው ጉዳዮች አንዱ ይሆናል ተብሏል፡፡

የሠራተኞችን ህልውና ተፈታትነው ነበር የተባሉትና በተለይ የለሙ እርሻዎችን  ለመከፋፈል የተደረጉት ሙከራዎች በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ጎልተው መታየታቸውን አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡ የእርሻ መሬቶችን ለመከፋፈል በተደረገው እንቅስቃሴ ድርጅቶቹ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ሥራ እስከማቆም በመድረሳቸው፣ የሠራተኞች ማኅበራት ከክልሎች የሥራ ኃላፊዎችና ከነዋሪዎች ጋር በመነጋገር የተፈጠረውን ችግር ለማርገብ መቻላቸውን አቶ ካሳሁን ጠቁመዋል፡፡

በሦስቱ ክልሎች ተፈጸሙ የተባሉ አላስፈላጊ ድርጊቶች ሰለባ የሆኑ ድርጅቶች በስም ጭምር የተያዙ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ካሳሁን፣ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች ሊደገሙ የማይገባቸው ናቸው ብለዋል፡፡ ድርጅቶች ያመረቷቸውን ለማጓጓዝ ከተፈተኑባቸው ሥፍራዎች መሀል አንዱ በባህር ዳር አካባቢ ተፈጸመ ያሉት፣ በአንድ ኩባንያ ተጭኖ ሲጓዝ የነበረ 800 ኩንታል አኩሪ አተር በመንገድ ላይ መዘረፉን ነው፡፡

በደቡብ ክልል የአንድ የለማ እርሻ ልማትን በአንድ ለአምስት በተቧደኑ ግለሰቦች ለመከፋፈል የተደረገውን ሙከራ ያስታወሱት አቶ ካሳሁን፣ በዚህ ምክንያት የእርሻ ልማቱ ሥራ አቁሞ ነበር ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ደግሞ አንድ ፋብሪካ አያስፈልገንም ተብሎ እንዳይሠራ በመደረጉ የተፈጠረው መስተጓጎል የፈጠረው ውጥረት ለሠራተኞች ዋስትና ሥጋት ሆኖ ነበር ብለው፣ ከክልሉ ባለሥልጣናት ጋር በተደረገ ውይይት ከበርካታ ቀናት በኋላ ሥራ እንዲጀምር መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ የሠራተኞችን ሠርቶ የመኖር መብት የሚጋፉ ድርጊቶች በተከሰቱ ቁጥር ከክልሎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር ለማስቆም የተቻለ ቢሆንም፣ አሁንም ያልቆሙ ችግሮች መኖራቸውን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ስለዚህ በሠራተኞች ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ላይ ችግር ሊያስከትሉ የሚችሉ እንዲህ ያሉ ድርጊቶች እንዲቆሙ፣ ኢሠማኮ ከመንግሥትና ከሠራተኞች ጋር በመሆን እንደሚሠራ የገለጹት አቶ ካሳሁን፣ ይህም በሜይ ዴይ በዓል ይንፀባረቃል ብለዋል፡፡

ኮንፌዴሬሽኑ በሜይ ዴይ በዓል አጉልቶ ከሚያነሳቸውና ምላሽ ያስፈልጋቸዋል ያላቸውን ጥያቄዎችን በዕለቱ ለማስተላለፍ መዘጋጀቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ አሁንም የሠራተኞች የመደራጀት መብት አደጋ ላይ መሆኑን የሚያስገነዝበው አንዱ ነው፡፡

በተለይ የውጭ ኩባንያዎች ሠራተኞች እንዲደራጁ አለመፈለጋቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ ጎልቶ መታየቱን አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ሠራተኞችን ለማደራጀት አለመቻሉንም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት ዕርምጃ እንዲወስድ የሚሹ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ሌላው ጉዳይ ደግሞ የሠራተኞች የደመወዝ ሁኔታ ሲሆን፣ በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚከፈለው ደመወዝ ፈጽሞ ተገቢነት የሌለው ነው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚከፈለው አነስተኛው ደመወዝ 750 ብር ሲሆን፣ ትልቁ ክፍያ ደግሞ 860 ብር ነው፡፡ በዚህ ደመወዝ መኖር ከባድ ስለሚሆን በተለይ የመነሻ ደመወዝ ወለል መቀመጥ እንደሚኖርበት ኢሠማኮ የሠራተኞችን ድምፅ እንደሚያሰማ ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢሠማኮን እያሳሰበ ያለው ሌላው ጉዳይ ደግሞ በኤጀንሲዎች እየተፈጸመ ያለው በደል መሆኑ ተገልጿል፡፡ በሕጋዊ ስም ሕገወጥ ተግባራት የሚከናወኑበት አካሄድ ለማስቆም የተደረጉ ጥረቶች ባለመሳካታቸውና ድርጊቱ በመባባሱ፣ ጉዳዩ አሁንም በመንግሥት ትኩረት እንዲሰጠው ይፈለጋል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሠራተኞችን የወቅቱን አንገብጋቢ ጥያቄዎች ለመንግሥት ማቅረብ አስፈላጊ በመሆኑ፣ በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ የሚሠሩ ሠራተኞች የመደራጀትና የመደራደር መብት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረግ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው ኢሠማኮ ጠይቋል፡፡ በሕገ መንግሥቱና በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ዕውቅና የተሰጠው የመንግሥት ሠራተኞች የመደራጀትና የመደራደር መብት ተግባራዊ እንዲሆን፣ አገር አቀፍ የመነሻ ደመወዝ ወለል እንዲኖር፣ የሥራ ቦታዎች ከአደጋና ከበሽታ የፀዱ እንዲሆኑ የወጡ የሙያ ደኅንነትና ጤንነት አጠባበቅ ፖሊሲዎች፣ ሕጎች፣ ደንቦችና መመርያዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ለመንግሥት ጥሪ አስተላልፏል፡፡ ምንም ሳይሠሩ በሠራተኛ ላብ በሚነግዱ ኤጀንሲዎች ወይም ደላሎች ላይ አስፈላጊው ዕርምጃ እንዲወሰድ፣ በኢትዮጵያውያን ሊሸፈኑ በሚችሉ ዝቅተኛ የሥራ መደቦች በርካታ ሥራ አጦች እያሉ የውጭ ዜጎችን መቅጠር እንዲቆም አቋም እንደያዘ ከኢሠማኮ መግለጫ መገንዘብ ተችሏል፡፡ ከመንግሥት ወደ ግል በፕራይቬታይዜሽን የሚዘዋወሩ ድርጅቶች አቅም ለሌላቸው ባለሀብቶች በመሸጣቸው ምክንያትና በገቡት ውል መሠረት መሥራት ባለመቻላቸው ድርጅቶቹን በመዝጋታቸው፣ የሠራተኞች የሥራ ዋስትና አደጋ ላይ መውደቁንና ሌሎች መሰል የሠራተኞች ጥያቄዎች በሜይ ዴይ በዓል እንደሚስተጋቡ መግለጫው ያመለክታል፡፡