የሙስሊም ማህበረሰብ ስብሰባ

ባለፉት ዓመታት የሙስሊሙ ማኅበረሰብ በእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ላይ የተለያዩ ቅሬታዎችን ሲያሰማ ቆይቷል። መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የተቋቋመውም በዚሁ ምክንያት ነበር።

ይህንኑ ተከትሎ ትናንት ሚያዚያ 23/2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የተቋማዊ ለውጥና አንድነት አገር አቀፍ ስብሰባ በሸራተን አዲስ ተካሂዶ ነበር። በስብሰባው ላይም የተለያዩ ውሳኔዎች ተላልፈዋል።

የሙስሊም ህብረተሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ በዕለቱ የተደረሱ ስምምነቶችን ገልፀውልናል።

ኃላፊው ከዚህ በፊት በመጅሊስ አመራርነት የተቀመጡ ሰዎች ህዝበ ሙስሊሙን የሚወክል አይደሉም፤ በመሆኑም ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ሥልጣናቸውን ይልቀቁ የሚል ጥያቄ ሲቀርብ መቆየቱን ያስታውሳሉ።

አመራሮቹ በህጋዊ መንገድ ያልመጡና ሙስሊሙን ማኅበረሰቡን የማይወክሉ ናቸው የሚሉ ጥያቄዎችም ሲቀርቡ ቆይተዋል፤ የተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎችም ተካሂደዋል።

በመሆኑም ትናንት በተካሄደው ስብሰባ በዋነኝነት በሥልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ያረጋገጡበት መሆኑን ኡስታዝ ካሚል ይናገራሉ።

መሸፈን የተከለከለባቸውን የዓለም አገራት ያውቃሉ?

ምርጫ እስከሚካሄድም ድረስ ሙስሊሙን ሕዝብ የሚመራና መሠረታዊ ክንውኖችን የሚፈፅም ቴክኒካል ኮሚቴ መዋቀሩን ገልፀውልናል።

በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ መጅሊሱ በኃይማኖት አባቶች መመራት አለበት የሚል አቋም የነበር በመሆኑ 24 የሚሆኑ ኡለማዎች ( የኃይማኖት አባቶች) ተመርጠው ከነበረው ዘጠኝ ኮሚቴ ሥልጣኑን ተረክበዋል።

“ህዝበ ሙስሊሙ ከዚህ በኋላ ጎራ ለይቶ፤ ከዚህኛው ነኝ፤ ከዚያው ነኝ ማለት አያስፈልግም፤ ሁሉም በኃይማኖቱ ለሃገሩ ለመስራት ቃል ተገጋብተዋል” ብለዋል ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድም በስብሰባው ላይ ተገኝተው የነበረ ሲሆን “ጠንካራ የሙስሊም ማህበረሰብ ለሃገር አንድነት መሠረት ነው” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። የሰላም ሚንስተር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚልም ለተደረገው የመቀራረብ ሂደት የሰላም ቁርጠኝነት ለተሳታፊዎቹ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ወደፊት ምን ይጠበቃል?

ይህ ስብሰባ ለህዝበ ሙስሊሙ የዓመታት ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። ከስብሰባው ተሳታፊዎች አንዷ ሙኒር አብዱል መናን የምትጠብቃቸውን ለውጦች እንዲህ ትገልፃለች።

እርሷ እንደምትለው መጅሊስ ውስጥ የተንሰራፋውን የሙስና አሰራር በማፅዳት ትልቁን ድርሻ ይይዛል።

“መጅሊሱ የሚያገኛቸው ገቢዎች አሉት ከመስጊድ ሱቆች ኪራእ እንዲሁም ከሃጂ ገቢ ይገኛል ነገር ግን መስጂዶች አሁንም ከምዕመን ተለምኖ ነው የመብራትና ውሃ የሚከፈለው ይህ ብልሹ አሰራር ይስተካከላል ብዬ እጠብቃለሁ” ብላለች።

የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እንግልት በመካ

የመጅሊሱ አስተዳደሮች ተጠሪነታቸው ለሙስሊሙ ማህበረሰብ እንጂ ለመንግስት ወይም ለፖለቲካ ተጠቃሚነት መሆን እንደሌለብትም ገልፃለች።

በአዲሱ አወቃቀር የተለያዩ የተቋቋሙ የወጣቶችና የሴቶች ዳሬክተሮች መቋቋማቸውንና በተቻለ ፍጥነት እንሱን ወደ ስራ ማስገባት በትምህርትም በስነ ምግባርም ኃይማኖታዊ ስርዓትን ለማስተካከል ትልቅ እርምጃ ለማድረግ እንደሚረዳ ትገልፃለች።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈፀመ ጥቃት 17 ሰዎች ሞቱ

ተያያዥ ርዕሶች