May 2, 2019

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ተከስቶ ከነበረው ግጭት ጋር ተያይዞ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለፍርድ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

በዚህ መሰረትም ግጭቱን በማነሳሳትና በማባባስ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ቁጥርም 33 መድረሱን ኮሚሽኑ አመላክቷል።

ከተጠርጣሪዎች መካከልም አንዱ የክልሉ ፖሊስ አባል መሆኑ ነው የተገለፀው።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር መሐመድ ሃመደኒል እንደተናገሩት በዳንጉር ወረዳ ተከስቶ በነበረው ግጭት የተፈጸመውን ወንጀል ከክልል እና ከፌደራል ፖሊስ የተውጣጣ ቡድን ምርመራ እያደረገ ነው፡፡

የምርመራ ቡድኑ 100 የሚጠጉ የቀስት ደጋን ከነመወርወሪያው እንዲሁም 100 መጥረቢያ እና ገጀራ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ገልጸዋል፡፡

የምርመራ ቡድኑ በአጭር ጊዜ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በማቅረብ የግጭቱ ተጎጂዎች ፍትህ እንዲያገኙ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ግጭቱ ከተከሰተበት ሚያዚያ 17 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ አካባቢው በፌደራልና በክልሉ የጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር በመዋሉ የአካባቢው ጸጥታ ከቀን ወደ ቀን መሻሻል ማሳየቱን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ከጸጥታ ሃይሉ አቅም በላይ ሆኖ ጥቃት የሚያደርስ አካል ባለመኖሩ ህብረተሰቡ እንዲረጋጋም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በማምቡክ ከተማ እና አካባቢው በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች የተጀመረው ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

ምንጭ ፦ኢዜአ
► መረጃ ፎረም – JOIN US