May 2, 2019
Source: https://mereja.com/amharic/v2/113727

የአማራ ክልል ሰልፍ ፕሬዚደንቱ እንዲወርዱ የተጠየቀበት ነው
BBC Amharic
በአማራ ክልል ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ማርቆስ፣ መርዓዊና ሌሎችም ከተሞች ዛሬ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል።
ከሰልፉ አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት አቶ እንዳላማው ክንዴ ለቢቢሲ እንደገለፁት ሰልፈኞቹ በርካታ ጥያቄዎችን ሲያስተጋቡ አርፍደዋል።
አስተባባሪው እንዳሉን በሃገር አቀፍ ደረጃ ለውጥ አለ ተብሎ የሚወራው የአማራን ህዝብ የጠቀመ አይደለም፤ ይልቁንም ይበልጥ የተጎዳው ባለፉት ሁለት ዓመታት ነው፤ የአማራ ክልል መሪ ድርጅት (አዴፓ) ስሙን ከመለወጥ ውጭ ክልላዊም ሆነ ተቋማዊ ለውጥ አላመጣም፤ የህዝቡን ጥያቄ በተገቢው መንገድ አልመለሰም የሚሉ ሃሳቦች የተነሱ ሲሆን የክልሉ ፕሬዚደንት ስልጣናቸውን እንዲለቁም የተጠየቀበት ነው።
ሰልፈኞቹ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ላይ ፣ በአጣዬና ጎንደር በነበሩ ጥቃቶች በክልሉ ተወላጆች ላይ የተፈፀሙት ግድያዎችን በማውገዝም ድምፃቸውን ያሰሙ ሲሆን የክልሉን መንግስት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ ብቻ በማተኮር አፋጣኝ መፍትሔ አልሰጠም በማለትም ኮንነውታል ።
ሰልፉን ለማካሄድ ከክልሉ መንግስት ፈቃድ ያላገኙ ቢሆንም በራሳቸው ውሳኔና ተነሳሽነት ወጣቱ ኃላፊነቱን ወስዶ እንዳካሄዱም እንዳላማው አክለዋል።
ፎቶ፡ AMMAFiled in:Amharic