May 3, 2019
Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 25 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በውጭ ሃገር ያላትን ወታደራዊ ማዘዣ ቁጥር ልታሳድግ መሆኑን የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት አስታወቀ።
ቤጂንግ የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሸቲቩን ሂደት አስተማማኝ ለማድረግ በውጭ ሃገራት ያሏትን ወታደራዊ የጦር ማዘዣዎች ልታሳድግ እንደምትችል ከፔንታገን የወጡ መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ አልጀዚራ ዘግቧል።
ፔንታገን ለኮንግረሱ ባቀረበው አመታዊ ሪፖርቱ ላይ ይህ የቤጂንግ እቅድ፥ ወዳጅ በትምላቸውና የውጭ ሃገር ጦርን በማስተናገድ የተሻለ ልምድ ባላቸው ሃገራት ተግባራዊ ይሆናልም ነው ያለው።
ለዚህ ደግሞ ምናልባትም ፓኪስታን አንደኛዋ ሃገር ትሆናለችም ብሏል በሪፖርቱ።
መካከለኛው ምስራቅ፣ የደቡብ እስያ ሃገራት እና የምዕራባዊ ፓሲፊክ ሃገራትም ቻይና ወታደራዊ የጦር ማዘዣዋን ለመገንባት ያሰበቻቸው አካባቢዎች መሆናቸውም በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
አመታዊ ሪፖርቱ በፈረንጆቹ 2022 የቻይና ወታደራዊ በጀት 260 ቢሊየን ዶላር ሊሆን እንደሚችልም ግምቱን አስቀምጧል።
ቻይና ከሃገሯ ውጭ በጂቡቲ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ እንዳላት ይታወቃል።
የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ቤጂንግን በሁሉም መስክ ጠንካራ የማድረግ አላማ እንዳላቸው መግለጻቸው ይታወሳል።
ይህም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሃገሪቱን ተሰሚነት ከፍ ማድረግ፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባትና ዘመናዊ የቴክኖሎጅ ባለቤት መሆንን ባካተተ መልኩ የሚተገበር ነው።
በተጨማሪም የሃገሪቱን ጦር በሁሉም መስኩ ማዘመንና ተፅዕኖ ፈጣሪነቱን ማሳደግም የእቅዱ አንድ አካል ነው።
ምንጭ፦ አልጀዚራ