May 1, 2019

የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና

የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

  በሀገራችን ለረዥም ዘመናት በቆየው ሥርዓት የተነሣ – የፖለቲካ ባሕላችን ሥልጣንን የኹሉ ነገር መነሻና መዳረሻ ብሎም ማዕከሉን ያደረገና የሚያደርግ በመኾኑ  ሀሳባዊነትን መሠረት ካደረገ ፖለቲካ ይልቅ ኃይልን አድርጎ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

  ኃይል የኹሉ ነገር ምንጭና መሠልጠኛ ኾኗል፡፡ በረዥሙ የሀገራችን ታሪክ ውስጥ ለሥልጣንና ስለሥልጣን ብዙ ነገር ተደርጓል፡፡ ተፈጽሟል፡፡ ዘመኑ እንደያዘው አስተሳሰብና አመለካከት ተሸክሞት ኖሯል፡፡ የዛ ተጽዕኖ ዛሬም ድረስ ጎልቶ የሚታይባቸው የታሪክ አሻራዎች በርካታ ናቸው፡፡

 ፓርቲና የፓርቲ ፖለቲካ በሀገራችን የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው፡፡ እምብዛም ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ባልዘለቀው የፖለቲካ ፓርቲ ታሪክ ውስጥ እልፍ አላፍ ለቁጥር የሚያታክቱ ፓርቲዎች ተመስርተዋል፡፡ ተመስርቷልም ተብለው መግለጫ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲ ታሪክ ሰላማዊን ብቻ ሳይኾን ትጥቃዊ ትግል ለማድረግ በተደራጀ መንገድ የተንቀሳቀሱትንም ጭምር የሚይዝ ነው፡፡

 የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋና ማዕከላቸውና መዘውራቸውን ፖለቲካዊ በማድረግ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የመሰባሰቢያ አንድ ጥላ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ሥልጣን የጥላው የወደፊት ፍላጎት መገለጫና ማሳለጫ በመኾን ግለሰቦችና ቡድኖች ለተመሳሳይ የጋራ ግብና ዓላማ የሚተጉበት መሣሪያ በመኾንም ያገለግላል፡፡

 ፓርቲ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ብሎም የፓርቲ ፖለቲካ ባሕል የሚሉ ጽንሰ ሀሳባዊ ጉዳዮችን ከነባራዊ ወቅታዊ ኹኔታ አንጻር መቃኘት እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ቢኾንም ከተግባራዊ እንቅሰቃሴያቸው አንጻር ነጠላ አብነት እየሰጡ “እከሌ” – “እከሌ” ብሎ ማስቀመጥ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን በመኾኑ በማዕቀፍ ደረጃ ስለነዚህ ጉዳዮች መመልከቱ አስፈላጊ ይኾናል፡፡

  በሀገራችን ከ109 በላይ “ፓርቲዎች” እንዳሉ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ ይህም በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ በነጠላ፣ በጥቂት ስብስብና በበበርካታ ስብስቦች ፓርቲያዊ መሰል እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ኃይሎችን አይጨምርም፡፡ ይህም በአንድ ባክል ባሕሉ ያልዳበረና ያልተጠናከረ በመኾኑ የሂደቱ ውጤት ቢኾንም በሌላ በኩል ዘመኑ ከደረሰበትና ከሚፈልገው ኹለንተናዊ አቅም አንጻር ደግሞ የኃላ ቀርነት መገለጫ ተደርጎም ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡

 ጠንካራና የሠለጠነ የፖለቲካ ፓርቲ ባሕልን ባዳበሩ ሀገራት እጅግ ውስን ፓርቲዎች ሲኖራቸው የሚቆሙለት ማሕበረሰብም የተለየና በወጉ ተለይቶም የተቀመጠ ነው፡፡ እኛ ጋር ምን አይነት ፓርቲዎች እንዳሉን ታሪካችንም ኾነ አኗኗራችን የሚያሳየን አንዳንዶች በግለሰቦች ላይ እጅጉን የተጣበቁ – በግለሰቡና በፓርቲው መሐከል ልነቱ ጎልቶ የማይታይበት፤ ብዙዎች የጠራ ፕሮግራም፣ ስትራቴጂ፣ ስልት፣ መርህ፣ ርዕዮተ ዓለምና ርዕዮተ ሀገርን ከመያዝ አንጻር እጅጉን የተዝረከረኩ፤ ብዙዎች ከጋዜጣዊ መግለጫና ከስብሰባ ተሳታፊነት የዘለለ ትርጉም ያለው እንቅስቃሴ የማያደርጉ፤ ብዙዎቹ ፓርቲዎች በትርፍ ጊዜያቸው በሚንቀሳቀሱ አመራሮችና አባሎች የሚንቀሳቀሱ፤ ብዙዎች ከምስረታ እስከ እንቅስቃሴያቸው ድረስ በጥቂቶች ስለጥቂቶች በጥቂቶች በሰፊው ሕዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ ስለመኾናቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡

 ይህንንም ከታሪካችንና ባሕላችን፣ ከኹለንተናዊ ድህነታችን፣ ከገዥዎች ጫና፣ ከግለሰቦች ኢ – ሥነ ምግባራዊ ድርጊት፣ ከሕብረተሰቡ የንቃተ ህሊና ደረጃ፣ ከድጋፍ ማጣት፣ ከነባራዊ ኹኔታ መለዋወጥ፣ ምሁራን ከፖለቲካ ተሳትፎ ጋር ያላቸው መራራቅ፣ ከምሕዳር መጥበብ፣ ከፋይናንስ ምንጭ ማጣት፣ ከባለሀብቶች ድጋፍ መራቅ፣ ከረዥም ይልቅ በጊዜያዊ ነገሮች ላይ መጠመድ – – – ወዘተ የሚሉ አንድ ሺ አንድ ምክንያቶችን ብንደረድርም እውነታው ግን ከዚህ የተለየ እንዳልኾነ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡

  ምክንያቶቹን ውስጣዊም ይኹኑ ውጫዊ፤ ወቅታዊም ይኹኑ ታሪካዊ ነገሩን ለመረዳትና በቀጣይ መደረግ ስላለበት ነገር ለማሰብና ለመወያየት ይጠቀሙ ይኾናል እንጂ እውነቱን (Truth) እና እውነታውን (Reality) ሊቀይር ከቶ አይችልም፡፡

  ለመኾኑ አንድ የሚያድግ ፓርቲ መገለጫዎቹ ምን ይመስላሉ?

አንደኛ፡- የሚያድግ ፓርቲ ለምን? እንዴት? በማን እንደተመሰረተ? ግልጽና የማያሻማ መነሻን የሚይዝ ነው፤

ሁለተኛ፡- የተመሰረተበትን ኹለንተናዊ ፍላጎት ከማዕቀፍ አንጻር ሊገልጽ የሚችል ትርጉም ያለው ፓርቲያዊ ፕሮግራም፣ ማኒፌስቶ (ርዕዮተ ዓለምና ርዕዮተ ሀገር)፣ ዓላማ፣ ግብ፣ ርዕይ፣ መርሕ ሊኖረው ይገባል፡፡

ሶስተኛ፡- ከፕሮግራሙና ማኒፌስቶው የሚቀዳ ኹለንተናዊ ዓላማዎችና ግቡን ሊያሳካበት የሚያስችል አደረጃጀትና ሕጋዊ ሰውነት፤

አራተኛ፡- አደረጃጀቱን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል በጋራ ሀሳብና ዕሳቤ ላይ የተሰባሰቡ አባላትና አመራሮች፤

አምስተኛ፡- አንድ ፓርቲ እንደፓርቲ ከተቋቋመበትና ከቆመለት ዓላማ በመነሣት አመራር፣ አባል፣ ደጋፊና ተፎካካሪ ብሎም ተቃዋሚውን በግልጽ ለመለየት የሚችልበት ሀሳባዊና ዕሳቢያዊ መስመር ሊኖረው ይገባል፤

ስድስተኛ፡- እንቅስቃሴውን ትርጉም ባለው መንገድ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ኹለንተናዊ አቅምን ከሰው ኃይል (ከአባላት ማፍራት፣ ከአመራር ማብቃት፣ ከደጋፊ ማብዛት፣ ከተፎካካሪ ጋር በትብብር ከመስራትና ተቃዋሚን ከማዳከም)፣ ከፋይናንሳዊ አቅምና ከሀሳብ ልዕልና አንጻር የሚገነባበት ስልት፣ ስትራቴጂና ዕቀድ መያዝ፤

ሰባተኛ፡- ፓርቲና ፓርቲያዊ እንቅስቃሴ ሂደት ነው፡፡ ሂደቱን በየጊዜው ከሚፈጠሩ ኹለንተናዊ ኹነቶች ጋር በማቀናጀት ለማስጓዝ የሚያስችል ኹለንተናዊ ትጋት ማድረግን ይጠይቃል፡፡

  ዕውን በሀገራችን ከነዚህ ሰባት ነጥቦች አንጻር ስንመለከታቸው የማያድጉ ፓርቲዎች አይበዙምን?

 በሀገራችን ያሉ ብዙዎቹ ፓርቲዎች ከሚያድጉ ይልቅ የማያድጉ አይደሉምን? ብዙዎቹ ተመስርተናል ብለው መግለጫ ሰጥተው – ብዙም ሳይቆዩ ተጣላን  – አለፍ ሲልም ተለያየንና ፈረስን የሚሉ አይደሉምን? በመግለጫ ተመስርተው – በመግለጫ የፈረሱስ በርካቶች አይደሉምን? ሳይግባቡ ተጣምረው – ያለመግባባት ሥራ የሰሩ ብዙዎች አይደሉምን? “የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ” እንደሚባለው ለብዙ ዓመታት ተመሳሳይ ነገርን – በተመሳሳይ መንገድ በማለትና በመስራት የሚታወቁ –  ተመሳሳይ ውጤት ያላቸውስ አይደሉምን?

ዕውን ብዙዎቹ ፓርቲዎቻችን ከአንድ ዕድር ጋር የሚነጻጸር ፋይናንሳዊ አቅም አላቸውን? የአንዳንድ ዕድሮች ፋይናሳዊ አቅም ምን እንደኾነ ለመረዳት ዞር ዞር ማለት ይጠይቃል፡፡ ዕድሮች እንኳ በአመራርና አባል መሐከል የተለየና የታወቀ መስመር ኖሯቸው – ተቋማዊ ሕልውናቸውን አስጠብቀው ለብዙ ዓመታት መሻገር ሲችሉ – ብዙ ፓርቲዎች ግን በብዙ ውጥንቅጥ ውስጥ ስለመኖራቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡

 ስንቶች ናቸው – ፓርቲያዊ ሕገ ደንብ ተከብሯል – አልተከበረም ተባብለው ሲጨቃጨቁና ፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት ሲንጓተቱ የነበሩ? ፓርቲያዊ ዓላማ ላይ የጋራ ነገርን ከመያዝ አንጻር እኛን ይወክላል  – አይወክልም እሰጣ ገባ እረፍት አልነሳንምን?

 የፓርቲ ፕሮግራም ላይ ከተደረጉ ለውጦች ይልቅ ስያሜ፣ አርማና አካሄድ ላይ የባከኑ ጊዜዎች፣ ጉልበቶችና ገንዘቦች ገና ከምስረታ ላይ ሊያልቁ ሲገባቸው ሳያልቁ ተመስርተውና ተመስርተናል በማለታቸው ያለማለቅ ዝቅጠት የታየባቸው አይደሉምን?

 ፓርቲ ያለ ዕሴት፣ ዲሲፕሊንና ያለ መርህ በቁሙ የሞተ አይደለምን? ስንቶች ናቸው  – ጥብቅ ፓርቲያዊ ዲሲፕሊን፣ ዕሴትና መርሃቸውን ጠብቀው እየተጓዙ ያሉት?

 ዕውን የትኛው የሀገራችን ፓርቲ ነው – በግልጽ በአመራር፣ በአባል፣ ደጋፊው፣ ተፎካካሪውና ተቃዋሚውን ቀይ መስመር አስምሮ በአስተምህሮት፣ በዕሳቤ፣ በርዕዮት፣ ከዓላማና ከግቡ አንጻር እየተንቀሳቀሰ ያለው? ዕውን የትኛው ፓርቲ ነው – የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅዱን ትርጉም ባለው መንገድ በግልጽ አስፍሮ ሕዝብን የማንቃት፣ የማደራጀትና የመምራት ሥራ እየሰራ ያለው?

 ዕውን የትኛው ፓርቲ ነው – በሀገራችን ከዕሳቤውና ከርዕዮቱ በመነሣት ተቋማዊ ሂደቱን ጠብቆ እንደግለሰብ፣ እንደቡድንና እንደፓርቲ – በእምነት (በአስተሳሰብና በአመለካከት)፣ በዕውቀት (በስልት፣ ስትራቴጂና ዕቅድ) እና በድርጊት (በተግባር) ደረጃ በኹለንተናዊ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሀገራዊና ሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ከጥቃቅንና አነስተኛ ጉዳዮች ወጥቶ በትላልቅ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ?

  ሀገራችን ካለችበት እጅግ አስጨናቂ፣ አስፈሪና አስጊ ነባራዊ ኹለንተናዊ ኹኔታ አብነት እየሰጡ ነገሩን መተንተን የሚቻል ቢኾንም ካለው ነባራዊ ኹኔታ አንጻር በዚህ መንገድ ማስቀመጡና በዚህ ላይ ውይይት ማድረጉ ጠቃሚ ይኾናል፡፡

 ፓርቲና ፓርቲያዊ ባሕል የኹለንተናዊ ነገሮች ውህድ ውጤት እንጂ በአንድ ነጠላ አካል ብቻ የሚከናወን ፈጽሞ አይደለም፡፡ ይህም የፓርቲ ተዋንያንን ብቻ ሳይኾን ከዛ ውጭ ያለውንም አካል በሙሉ የሚመለከት – አይመለከተኝም ቢል እንኳ የሚነካው ነው፡፡ ይህም ባሕል ይዳብር ዘንድ ኹለንተናዊ ትጋት ይጠይቃል፡፡

  በአንድ ሀገር ውስጥ የማያድጉ ፓርቲዎች ለሀገርና ለሕዝብ ሸክሞች ሲኾኖ በአንጻሩ የሚያድጉ ፓርቲዎች ሸክም አቅላዮች ናቸው፡፡ የማያድጉ ፓርቲዎች የሀገርና የሕዝብ መዥገሮች ሲኾኑ የሚያድጉ ፓርቲዎች የሀገርና የሕዝብ አለኝታና መከታ ብሎም የትውልዶች መኩሪያ ናቸው፡፡

የሚያድጉ እንጂ የማያድጉ ፓርቲዎች ፈጽሞ ኹለንተናዊ መሠረታዊ ለውጥ አያመጡም፡፡ የሚያድጉ ፓርቲዎች በሚያድጉ አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎች፣ ተፎካካሪዎችና ተቃዋሚዎች ኹለንተናዊ ትጋትና ኹለንተናዊ መስዋዕትነት የሚገነቡ – ታሪካዊ ኃላፊነትን በብቃት መወጣት የቻሉና የሚችሉ ናቸው፡፡ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!