May 3, 2019


Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 25፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች የሽግግር መንግሥት ምስረታውን ለማራዘም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለጸ፡፡

የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች የሽግግር መንግሥት ምስረታውን የማራዘም ውሳኔ ላይ የደረሱት ዛሬ በአዲስ አበባ ባካሄዱ ውይይት ላይ ነው።

የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች ባለፈው መስከረም ወር በአዲስ አበባ በደረሱት ስምምነት መሠረት በያዝነው ወር አጋማሽ የሽግግር መንግሥቱን በአዲስ መልክ ለማደራጀት መወሰናቸው ይታወሳል።

ሆኖም የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ባለመጠናቀቃቸው በመንግሥትና በተቃዋሚ ኃይሎች በኩል ይህንን በተመለከተ የተለያዩ አቋሞች ሲንጸባረቁ ቆይተዋል።

ኢጋድ ይህንን ክፍተት ለመሙላትና ስምምነቱ ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል የሰላም ስምምነቱ ፈራሚዎችን በአዲስ አበባ ጠርቶ እያወያየ ይገኛል።

ስብሰባውን የመሩት የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ ፓርቲዎቹ ልዩነታቸውን በማጥበብ ስምምነት ላይ አንዲደርሱ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት ሁሉም ኃይሎች የሽግግር መንግሥቱን ምስረታ በስድስት ወራት ለማራዘም ተስማምተዋል።

የደቡብ ሱዳን መንግሥት ለስምምነቱ ትግበራ አስፈላጊ የሆነውን ገንዘብ ለመመደብ ቃል መግባቱም ነው የተገለጸው።

ወይዘሮ ሂሩት ፓርቲዎቹ ስምምነት ላይ ለመድረስ ያሳዩትን ቁርጠኝነት በማድነቅ በተራዘመው ጊዜ ውስጥ የቀሩ ተግባራትን በማጠናቀቅ በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ቁርጠኝነት እንዲሳዩ መጠየቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።Filed in:Uncategorized