May 3, 2019
Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 25፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሁለተኛው የአፍሪካ- ቻይና የኦንላይን (ኢ-ኮሜርስ) ጉባኤ አዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ጉባኤውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከቻይና አለም አቀፍ የንግድ ድርጅት የኢ-ኮሜርስ ባለሙያዎች ኮሚቴ ጋር በመተባበር እንደሚያዘጋጁት ነው የተነገረው፡፡
ይህንን ጉባኤ ለማዘጋጀት የሚያስችለውን ስምምነትም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ ከቻይና የኢ-ኮሜርስ ባለሙያዎች ኮሚቴ ዳይሬክተር ሆ ዢጋንግ ጋር ተፈራመዋል፡፡
በቻይና መንግስት የሚደገፈው ይህ ጉባኤ ህዳር 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰኑን፥ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ጉባኤው በቻይናና አፍሪካ መካከል የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስርን ማጠናከርና አለም አቀፍ ትስስርን መፍጠር አላማው ያደረገ ነው ተብሏል፡፡
በአፍሪካ ውስጥ የወጪ እና የገቢ ንግድ አቅም ምን እንደሚመስል ማሳየት፣ የንግድ ድርጅቶችንና ግለሰቦች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግና የኦንላይን ግብይቱን እንዲቀላቀሉ ሁኔታወችን ማመቻቸትም የጉባኤው አካል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡