ምንጫ – ኢትዮ ኦንላይን

2019-03-14

Author: በቀለች ቶላ (ደራሲ)


– ለጡት፣ ለቆዳ እና ለአጥንት ነቀርሳ (ካንሰር)

መቅድም፡-

በኢትዮጵያ ሀገር በቀል ዕውቀት (የባሕል ሕክምና) ረዘም ያለ ተሞክሮ ያለው ነው፡፡ በጽሑፍ የተመዘገበው እንዳለ ሆኖ፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል ሲወርድ- ሲወራርድ የመጣም ጥቂት አለ፡፡ ወደ ትውልድ ሳይተላለፍ የቀረም ብዙ አለ፡፡ በዚህ ዘመን በተግባር በሀገር በቀል ዕውቀት (የባህል ሕክምና) አገልግሎት የሚሰጡት የኢትዮጵያ የባሕል ሐኪሞች ዕውቀት ያልተሰበሰበ አዝመራ ሆኗል የሚሉ አጥኚዎች አሉ፡፡ ለዛሬ ከዚህ ካልተሰበሰበው ሀገር በቀል ዕውቀት ውስጥ እጅግ ጥቂቱን፤ ማለትም ለጡት፣ ለቆዳ እና ለአጥንት ነቀርሳ (ካንሰር) የሚደረገውን የኢትዮጵያ የባህል ሐኪሞች ሕክምና ዘዴ በአጭር እንቃኛለን፡፡

ማጣቀሻ፡-

በሀገር በቀል ዕውቀት (የባሕል ሕክምና) አገልግሎት የሚሰጥበት ቤት በተደጋጋሚ ሄጄ መመልከቴ እና ታክመው የዳኑ ሰዎችንም ፊት ለፊት ለማነጋገር መቻሌ ገፊ ምክንያቴ ነው፡፡

መግቢያ፡-

ነቀርሳ ማለት ምን ማለት ነው?

ነቀርሳ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ‹‹ካንሰር›› ማለት ሲሆን፤ ከነርስ መዝገበ ቃላት የተገኘው ትርጉም “ነቀርሳ /ካንሰር/፣ አደገኛ እብጠት፣ ዕጢ፣ እሱም ወራሪ ወይም የሚስፋፋ ሆኖ፤ ቀድሞ ከነበረበት ራቅ ወደ አለ የሰው አካል ውስጥ በደም አማካይነት የሚዘዋወር፣ ወይም በውስጡ ነጭ የደም ሴል ባለው ፈሳሽ ህብረህዋስ አማካይነት የሚዘዋወር ነው፡፡” ይልና ቀጥሎም

“የነቀርሳ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምልክቶች

• ማንኛውም አንኳር (ዕበጥ) ነገር፣ የደነደነ እና ጠጣር የሆነ፣ በተለይም በጡት ላይ፣ በከንፈር ወይም በምላስ ላይ ሲታይ፣
• ማንኛውም ያልተጠበቀ ወይም ምክንያቱ ሊገለጽ የማይችል የደም ፍሰት፤
• ያልተጠበቀ ደም በሽንት ውስጥ፣ ወይም በሰገራ ላይ መገኘት፣
• ደም ወይም ደም መሳይ ፈሳሽ ከጡት ጫፍ ወይም ከማንኛውም ክፍት የሰውነት አካል ወደ ውጪ ሲፈስ፣
• ሴቶች የወር አበባ ካቆሙ በኋላ ያልተለመደ መድማት ሲከሰትባቸው፣
• በተለይም በአፍ፣ በምላስ ወይም በከንፈር አካባቢ ወይም በቆዳ ላይ የማይድን ቁስል መኖር፤
• ቀድሞ በዚያ ሰው ላይ በነበረ ኪንታሮት ወይም ጠቆር ያለ ቦታ (ማርያም የሳመች የሚባለው) ላይ በግልፅ የሚታይ የቀለም ወይም የመጠን ለውጥ ሲከሰት፤
• የምግብ ፍላጎት መቀነስ ወይም የምግብ ሆድ ውስጥ አለመፈጨት፤
• የማያቋረጥ የድምጽ መሻከር፣ ሳል፣ ምግብ ለመዋጥ መቸገር፤
• ለብዙ ጊዜ የቆየ ከተለመደው የተለየ የሰገራ ማስወገድ /መጸዳዳት/ ችግር፤” ማጣቀሻ 1

ነቀርሳ መነሻው ምንድነው?

ዶክተር ዴቪድ ዋርነር፣ ዶክተር በሌለበት የተባለው መጽሐፍ ላይ እንደሚለው፣ ‹‹ነቀርሳ ተላላፊ በሽታ ሳይሆን በማንኛውም የሰውነት ክፍል ላይ ጤናማ ያልሆነ እድገት ወይም እብጠት ነው፡፡ የነቀርሳ እብጠት በመጨረሻ ለሞት እስኪያበቃ ድረስ እያደገ የሚሄድ ነው፡፡ … በማንኛውም የአካል ክፍል ላይ ጠንካራ፣ ህመም የሌለው፣ ቀስ ብሎ የሚያድግ እብጠት ነቀርሳ ሊሆን ይችላል፡፡››
ይላል፡፡ ማጣቀሻ 2

ከ8ዐ ዓመታት በፊት በአሜሪካን አገር ውስጥ በተፈጥሮ እፅዋት እና የአመጋገብ ትምህረት በመስጠት የነቀርሳ በሽተኞችን ሲያክም የኖረው ጀትሮ ክሎስ፤ (በ1939 እ.ኤ.አ) ባሳተመው ባክ ቱ ኤደን፤ በሚባለው መጽሐፉ ላይ ደግሞ እንዲህ ይነግረናል፡፡

“የነቀርሳ በሽታ መነሻ ምክንያቱ ብዙ ነው፡፡ አጀማመሩ ሥር የሰደደ መመረዝ፣ መመርቀዝ፣ ድርቀት፣ የሰውነት ጽዳት አባለ-አካላት የሆኑት ሳንባ፣ ጉበት፣ ኩላሊት፣ ቆዳ እና የሰገራ ማስወገጃ አካባቢ መዳከም ብሎም የእነዚህ ሥርዓት መመረዝ እና የመርዙም በእነዚህ በተዳከሙ አባል አካል ዙርያ መጠራቀም፣ ወይም ሰውነት በመመታት፣ በመውደቅ መነረት፣ መጐዳት፣ የተነሳ ሊሆን ይችላል፡፡ ማጣቀሻ 3

የነቀርሳ በሽታ ዓይነቶች?

የነቀርሳ በሽታ ዓይነቶች በብዙ ሁኔታ ሲተነተኑ ዓይነታቸው እና ስማቸው ብቻ እንኳ ሰፊ ነው፡፡ በ1981 ዓ.ም በታተመው ዕፀ ደብዳቤ መጽሐፍ ላይ ዓይነታቸው፣ ከይሲ፣ ምንሽሮ፣ ከመንዝና፣ የውስጥ፣ የፌስቱላ፣የማህጸንና የፊንጢጣ በሚል የነቀርሳ ዓይነት ዝርዝር ይነበባል፡፡ ማጣቀሻ 4
እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ገለፃ፤ በዓለም ላይ በብዛት በሰው ላይ ከሚከሰቱት አምስት ዋና ዋና የነቀርሳ ዓይነቶች ውስጥ፣ በወንዶች ላይ የሳንባ፣ የፕሮስቴት፣ የትልቁ አንጀት እስከ ፊንጢጣ ያለው (ኮሎ.ሬክታል)፣ የጨጓራ እና የጉበት ሲሆኑ ፤በሴቶች ላይ የጡት፣ የትልቁ አንጀት እስከ ፊንጢጣ ያለው (ኮሎ.ሬክታል)፣ የሳንባ፣ የማህፀን ጫፍ እና የጨጓራ ነቀርሳ ናቸው፡፡ ማጣቀሻ5

ለጡት፣ ለቆዳ እና ለአጥንት ነቀርሳ የሀገር በቀል ዕውቀት ሐኪሞች ምን ያደርጋሉ?

በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች እና ገጠር ለነቀርሳ በሽታ የተለያየ የባሕል መድኃኒት የሚሰጡ እና የሚያክሙ የባሕል ሐኪሞች አሉ፡፡ ዘዴውም እንደ በሽታው ዓይነት፣ እንደ ባሕል ሐኪሙ ልምድ፣ እንደሚያዘጋጀው የመድኃኒት ዓይነት የተለያየ ነው፡፡

በሽታውን ስለመለየት፡-

እያንዳንዳቸው የባሕል ሐኪሞች የነቀርሳ ሕመሙን ዓይነት፣ የጉዳቱን መጠን፣ ያለበትን ደረጃ የሚለዩበት ዘዴ አላቸው፡፡ በማየት፣ በመዳሰስ፣ ደጋግሞ በመጠየቅ ይለዩታል፡፡ ከለዩት በኋላ ስለበሽታው ይዘትና ዓይነት በዝግታ ያስረዳሉ፡፡ አንዳንድ የባሕል ሐኪሞች ደግሞ ታማሚው የተመረመረበትን የላብራቶር የምርመራ ወረቀት እንዲያቀርብ ይጠይቁታል፡፡

ለታማሚው የሚሰጡት ምክር፡-

ታማሚው እንዳይፈራ፣ እንዳይጨነቅ፣ ተስፋ እንዳይቆርጥ፣ በሕክምናው እንዲተማመን ይመክሩታል፡፡ የሚሰጡት መድኃኒት እንዴት እንደሚሰጠው፣ እንደምን እንደሚያሽለው፣ ስንት ጊዜ እንደሚወስደው፣ ምን ምን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ያስረዱታል፡፡ ይህን የመለየት እና የማስረዳት ጊዜ ታማሚው ከሐኪሙ ዘንድ ከቀረበበት ጊዜ እና እስኪያስረዱት ድረስ ቢበዛ 3ዐ ደቂቃ ቢሆን ነው፡፡ ከቀደመው ታማሚ ቀጥሎ ሌላ ተረኛ ታማሚ ከሌለ እና ታማሚው ብዙ ውይይት ከፈለገ፣ ጥያቄዎችን እያነሳ ብዙ ምክር ሊነግሩት ይችላሉ፡፡ ክስተቶችን እየጠቀሱ፣ ስለ ተመሳሳይ ሕመም የቀድሞ ታካሚዎች እያነሱ በምሳሌ ሊያስረዱት ይችላሉ፡፡ ይህም ሆኖ

• ታማሚው ሕክምናውን እጅግ ከፈራ፣ ወይም ካልፈለገው አያስገድዱትም፡፡ ሳይታከም መሄድ ይችላል፡፡ ወይም
• የነቀርሳው የበሽታ ሁኔታ ሊታከም ከሚችልበት ደረጃ በላይ ከሆነ ምክር ሰጥተው ይሸኙታል፡፡

የባሕል ሕክምናው ዓይነት፡-

ሁሉም የባሕል ሐኪሞች ሁሉንም ዓይነት ሕመም አያክሙም፡፡ የነቀርሳ በሽታን የሚያክሙ የባሕል ሐኪሞች እራሳቸው አንድ ዓይነት ዘዴ ወይም ተመሳሳይ የተፈጥሮ መድኃኒት አይጠቀሙም፡፡ የየራሳቸው የተፈጥሮ መድኃኒት ዓይነት እና የአሰጣጥ ዘዴ አላቸው፡፡ በአገሪቱ ካለው ሰፊ የባሕል ሕክምና ዓይነት ጥቂቱን እንደምሳሌ እንመልከት፡-

ቀብቶ በማሸግ ወይም በማጀል ማከም፡-

የሚቀባው መድኃኒት በጣም ትንሽ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ የአንድ ፍሬ ምስር ዱቄት የሚያክል ሊሆን ይችላል፡፡ ትንሽ መድኃኒት ቀብቶ የሚታሸግ ከሆነ፣ ቀብቶ ማሸግ ይበላል፡፡ በዛ ብሎ ወፈር ያለ መድኃኒት ተደርጎ የሚታሸግ ከሆነ ቀብቶ ማጀል ይባላል፡፡

• ትንሽ መዳኃኒት ቀብቶ ማሸግ ወይም በብዙ መድኃኒት ማጀል ብዙ ጊዜ በውጪ የሰውነት ክፍል ላይ፣ አብጦ ለወጣ የነቀርሳ ዓይነት ነው፡፡ መድኃኒትን ቀብቶ በማሸግ ወይም በማጀል፤ የሚገኘው ውጤት ሰንኮፉ ወደ አንድ ቦታ ተሰብስቦ በሽታው እንዲወጣ ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ የባሕል ሐኪሞች የጡት ነቀርሳን፣ የቆዳ እና የአጥንት ነቀርሳን በዚህ ዓይነት ዘዴ ያክሙታል፡፡ ነቀርሳው ያለበትን /የደረሰበትን/ ደረጃ ያጠኑታል፡፡ በዚያ መሠረት አሁኑኑ “ቢቀባ ወይም ቢታጀል እና በተከታታይ ቢታከም ይድናል” ብለው ያመኑበትን በመቀባት እና በማጀል ማከም ይጀምራሉ፡፡

• ተቀብቶ ወይም ታጅሎ ከመታሸጉ በፊት ታካሚው ሌሎች የሚነገሩት ምክሮች ካሉም ይነገረዋል፡፡ እናም ቀጠሮ ሊሰጠው ይችላል፡፡ እስከ ቀጠሮው ድረስ እንደተነገረው ምክር እያደረገ ይቆያል፡፡

የሚቀቡት ወይም የሚታጀልባቸው ባሕላዊ መድኃኒት ለዚህ ጉዳይ የተመረጡ ማዕድናት፣ እፅዋት፣ ወይም የእንስሳት ውጤት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የሚቀባው ወይም የሚታጀለው በየጊዜው ይቀየራል፤ ለምሳሌ በየቀኑ፤ በየሁለት ቀኑ ወይም በየ ሶስት ቀኑ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደዚህ ሲሆን ከውስጥ መግል እና ሰንኮፍ ነገሮች ተሰብስበው ወደ አንድ ቦታ ይመጣሉ፡፡ የባሕል ሐኪሙ በየጊዜው የታሸገበትን እያነሳ፣ መግሉን እያፀዳ፣ መድኃኒቱን እየቀባ ሲያሽግ ይቆያል፡፡ በጡት፣ በቆዳ፣ ወይም ከአጥንት ላይ በቁስሉ አፍ በኩል ወደ ጫፍ የሚመጣው ሰንኮፍ ቀኑ ሲደርስ በራሱ ይለቃል፡፡ ይህ ማለት የነቀርሳ ሴሎቹ በአንድ ቦታ ተጠራቀሙ ማለት ነው፡፡ ይህ ጥርቅም እና ጠንካራ ነገር ነው- ሰንኮፍ የሚባለው፡፡

• ሰንኮፉ በሚወጣበት ጊዜ ጠንካራ ነገር ነው፡፡
• ቀለሙ በወቅቱ ነጣ ያለ ነው፡፡ ሲቆይ ሊጠቁር ይችላል፡ (አንዳንድ ሰዎች “ለጉዱ” ብለው ያስቀምጡታል )
• ደበልበል ያለ ወይም ጠፍጠፍ ያለ ቅርጽ ሊኖርው ይችላል፡፡
• መጠኑ ለምሳሌ አንድ የኢትዮጵያ የብር ሣንቲም ያህላል፤ ወይም
• አንድ ቆርኪ ያህል ይሆናል፤ ወይም ከዚያ ትንሽ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል፡፡

የመጀመሪያው ዙር ከታሸገበት /ከታጀለበት/ ቀን አንስቶ ሰንኮፉ እስከሚወጣ ድረስ ከ9 እስከ 12 ቀናት ሊቆይ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው ዙር ሲወጣ ተለቅ ያለ ሰንኮፍ ይወጣል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ፣
ሀ) በአንድ ጊዜ ሰንኮፉ ተጠርጎ ሊወጣ ይችላል፡፡ ወይም
ለ) ተጠርጎ ያልተጠናቀቀ እንደሆን ሌላ ጊዜ በተደጋጋሚ
መቀባትና መሸግ ያስፈልጋል፡፡

በተደጋጋሚ የሚታሸግ ከሆነ፤ ሁኔታውን እያዩት ታካሚው እረፍት ያደርጋል፡፡ ሳይታሸግ /ሳይታጀል/ ይቆያል ማለት ነው፡፡ ከሁለት ወይም ከሶስት ሳምንት በኋላ ሁለተኛ ዙር ይቀጥላል፡፡ ይቀባና ወይም ይታጀልና ይታሸጋል፡፡ በየቀኑ፣ በየሁለት ቀኑ ወይም በየሶስተ ቀኑ ይቀየራል፡፡ ሰንኮፉ ይወጣል፡፡ ከመጀመሪያው ዙር ቀጥሎ ባሉት ዙሮች የሚወጣው የሰንኮፉ መጠን እየቀነሰ እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ በዚያውም የታካሚው የሕመሙ ጫና እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ በመጨረሻም ተቀብቶ ታሽጎ ሲፈተሽ ምንም የሚወጣ ሰንኮፍ የለም፡፡ አሁን ዳነ፣ አበቃ ማለት ነው፡፡

ምን ጊዜም ሰንኮፉ የወጣበት ቦታ ላይ በወቅቱ ክፍት ቁስል ይሆናል፡፡ ከዚያም የቁስሉን ቦታ በየቀኑ እያፀዱ ያጥቡታል፡፣ የቁስል ማድረቂያ የባሕል መድኃኒት ይቀቡታል፣ መልሰውም ሊያሽጉት ይችላሉ፡፡ የቆሰለውም ቦታ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ይድናል፤ ሰፊ የነበረው የቁስል ቦታም ይሰበሰባል፡፡

በእንደዚህ ዓይነት ህክምናው ጫና ሳይኖረው ለጥቂት ወራት ይቀጥልና ያበቃል፡፡ የነቀርሳ እብጠት፣ ቁስለት እና ሰንኮፍ ሲወጣበት የነበረው ቦታም ይድናል፡፡ ከዳነ በኋላ በቦታው በሰውነት ላይ የሚታይ ነገር ቢኖር የቆዳ መሸብሸብ ወይም አነስ ያለ ጠባሳ ሊሆን ይችላል፡፡

ሕክምናው ለጡት ነቀርሳ ሲሆን፤ በጡት አንድ ጎን ላይ አነስ ያለ ጠባሳ ይኖራል፡፡ የቀረው ሙሉ ጡት ጤነኛ እና ምንም ጉድለት የሌለው ይሆናል፡፡

የባሕል ሐኪሙ እንዲመገቡ ወይም እንዳይመገቡ የሚነግራቸው ምክሮች አሉ፡፡ ሌሎችም የሚከለከሉ እና የሚፈቀዱ ነገሮች አሉ፡፡ በተጨማሪ በየጊዜው የሚበሉ፣ የሚጠጡ ወይም የሚቀቡ ተፈጥሯዊ መድኃኒት ይሰጣሉ፡፡

የሚገርመኝ የነቀርሳ ሕመሙ በጡታቸው ላይ በወጣትነት ደርሶባቸው፤ እንደዚህ ታክመው ድነው፣ ልጅ ወልደው አጥብተው ያሳደጉ ሴቶች መኖራቸው ነው፡፡ ሌላም በቅርብ 2 ዓመታት ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ሕክምና ወስዳ ከዳነች በኋላ አሁን በረሐ ለበረሐ እየሄደች የንግድ ሥራ የምታከናውን ሴት በዚህ ምልከታዬ ወቅት አጋጥማኛለች፡፡

በሚጠጣ ፈሳሽ የባሕል መድኃኒት ማከም፡-

የነቀርሳውን የሕመም ደረጃ የመለየት ሥራ እና ስለሚሰጠው ምክር ከላይ እንደተገለፀው ነው፡፡ ይኸኛው የሕክምና ዘዴ ማሸግ ወይም ማጀልን አይጨምርም፡፡ የባሕል ሐኪሙ የነቀርሳውን የበሽታ ደረጃ ከለየው በኋላ፤ “በሚጠጣው የባሕል መድኃኒት የሚድንበት ደረጃ ላይ ነው” ብሎ ካመነ መድኃኒቱን ያስጀምራል፡፡ መድኃኒቱ የሚዘጋጀው ሊጠጣ በሚችል ዓይነት ከተመረጡ የዕፀዋት ቅጠል፣ ሥር፣ ቅርፊት፣ ሙጫ ወይም ማዕድን ተቀምሞ ነው፡፡ የነቀርሳ ሕመሙ በሰውነት የውጪ ክፍል በጡት ላይ፣ በቆዳ ላይ ወይም በአጥንት ላይ ቢገኝ፤ በሽታውን ለመፈወስ በማጠጣት ብቻ ያክሙታል፡፡ ይህ የሚጠጣው መድኃኒት የሚዘጋጀው በዳበረ እውቀት ነው፡፡ ይህን መድኃኒት ታካሚው እዚያው የባሕል ሐኪም ዘንድ ቆይቶ ወይም ወደ ቤቱ ወስዶ ተመጥኖ በተነገረው መሠረት ሊጠጣው ይችላል፡፡ ይህም ከአንድ እስከ ሁለት ወር ጊዜ ሊቆይ ይችላል፡፡ የመድኃኒቱ ጣዕም፣
ሀ) ምሬት የሌለው ሊሆን ይችላል፤
ለ) መጠነኛ ምሬት ይኖረው ይሆናል፤
ሐ) በጣም ሊመር ይችላል፤

ታካሚው ምሬቱን ወይም ያልለመደውን ጣዕም ተቋቁሞ በራሱ ፍላጎት የሚጠጣ ከሆነ ይቀጥላል፡፡ ታካሚው መጠጣት አቅቶት እርዳታ ካስፈለገው ምሬቱን ወይም ጣዕሙን እንዲቋቋም ዘዴ ያበጁለት እና ያጠጡታል፡፡

ይህ የተጠጣው የተፈጥሮ የባሕል መድኃኒት፤ ለምሳሌ፣
ሀ) በተቅማጥ፣
ለ) በትውከት፣
ሐ) በተቅማጥ እና በትውከት፣ ወይም
መ) ምንም ነገር ሳያስከትሉ፣
የበሽታው ተውሳክ ከሰውነት እንዲወገድ የሚያደርጉ እና የነቀርሳ ሕመሙን የሚፈውሱ ናቸው፡፡

ይህ ለመጠጥ የተዘጋጀው መድኃኒት፣ በተጨማሪም ለነቀርሳ እብጠት ወይም ቁስል ማጠቢያም የሚውልበት ጊዜ አለ፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን የሚከለከሉ እና የሚፈቀዱ ምግቦች እና መጠጦች አሉ፡፡

የባሕል መድኃኒቱን በሚዋጥ መልክ መስጠት፡-

የነቀርሳውን የሕመም ደረጃ የመለየት ሥራ እና ስለሚሰጠው ምክር ከላይ እንደተገለፀው ሆኖ፤ የባሕል ሐኪሙ የነቀርሳውን የበሽታ ደረጃ ከለየው በኋላ፤ “በእነዚህ በሚዋጡ የባሕል መድኃኒቶች የሚድንበት ደረጃ ላይ ነው” ብሎ ካመነ የሚዋጠውን መድኃኒት ያስጀምራል፡፡

የባሕል ሐኪሞች ከዕፀዋት ወይም ከማዕድናት ቀምመው አዘጋጅተው በትንንሽ መጠን ሊውጡት በሚመች ሁኔታ ያዘጋጁታል፡፡ ለታካሚው የሚወስድበትን መጠን፣ ጊዜ፣ የሚያስፈልገውን ጥንቃቄ ሁሉ የባሕል ሐኪሙ ይነግረዋል፡፡ ተለወሰኑ ሳምንታት ሲወድ ይቆይና፤ የተወሰኑ ቀናት እረፍት ያደርጋል፡፡ በዚሁ ዓይነት እንደ በሽታው ጉዳት ከአንድ እስከ አራት ወራት ወይም ከዚያም በላይ መድኃኒቱን እየወሰደ፣ በመሐል እረፍት እያደረገ ይቆያል፡፡ የነቀርሳው ህመም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻለ ይሄዳል፡፡ እብጠቱም ሆነ የቁስሉ ንዝናዜ ይቀንሳል፡፡

በማዋጥ ዓይነት የተሰጠው መድኃኒት፣ እንደሚጠጣው ዓይነት፣ የሚያስከትላቸው ነገሮች፤

ሀ) በተቅማጥ፣
ለ) በትውከት፣
ሐ) በተቅማጥ እና በትውከት፣ ወይም
መ) ምንም ነገር ሳያስከትሉ፣

ታካሚው ከበሽታው ይድናል፡፡ በዋናነት በሚዋጥ ዓይነት የሚሰጥ ቢሆንም በተጨማሪ የሚቀባ፣ መታጠቢያ እና በመሳሰሉት መልክ የሚሰጡ መድኃኒቶች ይኖራሉ፡፡

የተለያዩ ዘዴዎችን አጣምሮ መስጠት፡-

እንደ ባሕል ሐኪሙ የሕክምና ብልሃት የተለያዩ ዘዴዎችን፣ (ከላይ የተጠቀሱትም ሆኑ ሌሎች ዘዴዎችን) በማጣመር የሚያክሙ አሉ፡፡ ታካሚው በተነገረው ምክር መሠረት እራሱን መርዳት ይጠበቅበታል፡፡ ወይም የታካሚው ቤተሰቦች እና አስታማሚዎች የተሰጠውን መድኃኒት በአግባቡ መስጠት እና የተነገረውን ምክር መተግበር ይኖርባቸዋል፡፡

ምስጋና ይገባችኋል!

የሀገር በቀል ዕውቀት አዋቂዎች (የባሕል ሐኪሞች) ለዘመናት ለህዝቡ ባበረከታችሁት አገልግሎት ከፍተኛ ምስጋና ይገባችኋል፡፡ በተለይ ነቀርሳን በቀላል ዘዴ፣ በአነስተኛ ክፍያ፣ በአጭር ጊዜ በማከም ህዝብን እና ቤተሰብን እንዴት እንደደገፋችሁ ቢፃፍ ብዙ መጽሐፍት ይወጣዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ነቀርሳ ዘመናዊ ሕክምናውን እንዴት እንደተፈታተነው ግልጽ ነው፡፡ በዘመናዊ ሕክምና ውስብስብ ችግር ውስጥ የገባው የማከሚያ ስልት፤ በባሕል ሕክምናው በቀላሉ የሚጠናቀቅ የማከሚያ ስልት ነውና፡፡ ነቀርሳን በቀላል ዘዴ፣ በአነስተኛ ክፍያ፣ በአጭር ጊዜ በማከም ህዝብን እና ቤተሰብን እያገለገላችሁ ስለሆነ ምሥጋና ይገባችኋል፡፡

አሳዛኙ ጉዳይ፡-

የሚያሳዝነው ትልቁ ጉዳይ፤ በእንደዚህ ዓይነት ለብዙ ዘመናት ሕክምና ሲሰጡ የቆዩ የባሕል ሐኪሞች አብዛኞቹ ሥራቸውን በጽሑፍ አለማስቀመጣቸው ነው፡፡ የታከሙ ሰዎችን ዛሬ ለማስረጃ ወይም ለጥናት ብንፈልግ በቀላል ልናገኛቸው አንችልም፡፡ ታካሚዎቹ ታክመው ወደየመጡበት ይመለሳሉ፡፡ ነገር ግን የታካሚዎችን፣ ስማቸውን፡ አድራሻቸውን፣ ስልክ ቁጥራቸውን፡ ስለ ህመማቸው ዓይነት፣ ስለወሰዱት የህክምና ዘዴ፣ ስለዳኑበት የመድኃኒት ዓይነት ወዘተ፣ በመዝገብ አስፍረው ቢሆን በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ለተለያየ ጥናት ቢፈለግ ለዚህ ዘመን ትልቅ መረጃ ይሆን ነበር፡፡

ለወደፊት የሚበጀን፡-
በአሁኑ ዘመን በአገራችን ለነቀርሳ በሽታ የባሕል ሕክምና አገልግሎት እየሰጡ ያሉትን፤ በሥራ ቦታቸው ሄዶ መጎብኘት፣ ማወያየት፣ ሥራቸውን በተሻለ ደረጃ እንዲሠሩ መደገፋ እና መርዳት፣ የፈለገ ወገን ቢኖር፣ ጉዳዩ የአገር እንጂ የግለሰቦቹ ብቻ አይደለምና፡፡

መደምደሚያ፡-

የነቀርሳ ሕመም በዚህ ዘመን እየበዛ ሄዷል፡፡ በሽታው ከጀመረ እየተባባሰ ይሄዳል፡፡ ያባባሱት ነገሮች የሕክምናው ውስብስብነት፤ በሽታው በቀላል ዘመናዊ ህክምና አለመዳን፤ በሽታውን የሚያባብሱ ምግቦች እና መጠጦች ተለይተው አለመነገር እና የመሳሰሉት ችግሮች ናቸው፡፡ በተለይ በእኛ አገር ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው የሕክምና ዘርፍ ዘመናዊ /የአውሮፓ ሕክምና/ ዘዴ ነው፡፡

በሌሎች የዓለም አገራት፤ ሌሎች አማራጭ የሕክምና ዘዴዎች በተግባር ላይ ውለዋል፡፡ ሰፊ ድጋፍ አላቸው፣ ብዙ ዓይነት ምርምር ይደረግባቸዋል፡፡ ነገር ግን በእኛ አገር ያለው የባሕል ሕክምና ዘዴ ትኩረት ያልተሰጠው እና በጥናት ያልተደገፈ ነው፡፡ ውጤታማ የሕክምና አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም፤ በመደበኛነት አልተካተቱም፡፡ ኢ-መደበኛም ቢሆኑ ወደፊት ትኩረት ሊሰጥባቸው ያስፈልጋል፡፡ ሥራቸውን በተሻለ ደረጃ እንዲሰሩ የሁላችንም ትብብርና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡

በሚቀጥለው ዝግጅት ለነቀርሳ ህመም የተሻሉ የተፈጥሮ መድኃኒቶች፣ የአመጋገብ ዘዴን እና ነቀርሳን እንዳይባባስ ስለሚደረጉ ጥንቃቄዎች በአጭሩ እንቃኛለን፡፡ ቸር ሰንብቱ፡፡

ማጣቀሻዎች
1. UN PANDA, 2005, Jaypee’s Nurses’ Dictionary, 2nd Edition, Jaypee Brothers Medical Publishers (p) Ltd. New Delhi, INDIA.
2. DAVID WERNER with CAROL THUMAN and JANE MAXWELL. (2002). WHERE THERE IS NO DOCTOR, A village health care handbook New Revised Edition, United States of America,

3. JETHRO KLOSS, BACK TO EDEN, THE CLASSIC GUIDE TO HERBAL MEDICINE, NATURAL FOODS AND HOME REMEDIES, SINCE 1939, THE AUTHENTIC KLOSS FAMILY ®, 2009, LOTUS PRESS, U.S.A

4. ገለሁን አባተ፣ 1981 .ም፣ ዕፀ ደብዳቤ፣ ከጥንት እስከ ዛሬ፣ ሥነ ሕይወት ክፍል ሳይንስ ፋኩሊቲ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ አዲስ አበባ፣
5. የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ 2ዐ12 ሪፖርት Related news