2019-04-09

SourceURL:https://ethio-online.com/archives/2204 ፪ የጡት ነቀርሳን ችላ አንበለው! – Ethio Online

ሀገራዊ መድኃኒት

Author: በቀለች ቶላ (ደራሲ)

፪ የጡት ነቀርሳን ችላ አንበለው!

መነሻ፡-

ከዚህ በቀደመው ጽሑፍ፣ ለጡት፣ ለቆዳ እና ለአጥንት ነቀርሳ፣ የኢትዮጵያ የባሕል ሐኪሞች የሕክምና ዘዴን በሚመለከት፣ በአጭሩ ለመግለጽ ሞክሬ ነበር፡፡ የዛሬው ከዚያ የቀጠለ የጡት ነቀርሳን የሚመለከት ነው፡፡

መግቢያ፡-

የጡት ነቀርሳ በድሮ ጊዜ በአገራችን እንዲህ እንደዛሬው አልተስፋፋም ወይም የለም ማለት ይቻላል፡፡ማስረጃ ለመጥቀስ “መጽሐፈ መድኃኒት” የተሰኘው በአማርኛ ከተተረጎመ የ2ዐዐ አመት እድሜ አለው፡፡ ይህ መጽሐፍ ቀድሞ በብራና ላይ የተፃፈ ነበር፡፡ ይህ በብራና ላይ ተዘጋጅቶ የነበረው እንግሊዝ አገር ተወስዶ በእነሱ ቤተ መጽሐፍት ይገኛል፡፡ ከእዚያ ላይ አገር ወዳድ የሆኑት አቶ ሐዲስ ገብረ መስቀል  ገልብጠው በ198ዐ ዓ.ም አሳትመው ነበር፡፡ የዚህ ቅጂ በብሔራዊ ቤተመዛግብት እና ቤተ መጽሐፍት ድርጅት ይገኛል፡፡ ማጣቀሻ 1  በተጨማሪም የዚሁ መጽሐፍ ግልባጭ (ከብራና ወደ ወረቀት የተገለበጠ) በአሁኑ ዘመን በቁም እጅ ጽሑፍ በወረቀት ላይ የተጻፈው በአንዳንድ አረጋውያን እጅ ጎንደር እና ጎጃም ውስጥ ይገኛል፡፡ የዚህን የእጅ ጽሑፍ ትሩፋት በሌላ ርዕስ አዘጋጅተውት እዝያው ለብሔራዊ ቤተመዛግብት የተሰጠ አለ፡፡ “የኢትዮጵያ የሀገር ባህል የዕፀዋት መድኃኒቶች ዝርዝር” በሚል ዋና ርዕስ እንዲሁም “፩ኛ ዕፅ ደብዳቤ እና ፪ኛ ዕፅ ደብዳቤ” በሚል ሁለት ዋና ክፍሎች ተለይቶ በ1975 ዓም በአቶ ልዑል ወ/ሩ ፋኤል የተዘጋጀ ነው። ማጣቀሻ 2

በእነዚህ ጥንታዊ ጽሑፍ ላይ የጡት ነቀርሳ በሽታ አልተጠቀሰም፡፡ የተጠቀሱት የነቀርሳ ዓይነቶች በቆዳ ላይ የሚከሰቱ እንደ ከይሲ፣ ምንሽሮ፣ ከመንዝና፣ ከማንአንሼ ያሉት እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ታድያ ድሮ ያልነበረ በአሁን ዘመን የጡት ነቀርሳን እንደዚህ ያስፋፋው በተለይ ምንድነው?   አዲስ የአኗኗር ዘይቤ በመከተላችን ይሆን እንዴ?  አንዳች ያለ ዕውቀት የተቀየረ ክስተት ይኖር ይሆን እንዴ?   ምግባችን፣ መጠጣችን ወይም ሕክምናችን  ይሆን?  ብዙ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህንን ለአጥኚዎች መተው ነው፤ (ብዙ ምርምር የሚጠይቅ ሥራ ስለሆነ)

  1. በአገሪቱ የጡት ነቀርሳ በሽታ ስፋት

የነቀርሳ ቁጥጥር እስትራተጂክ የሚባል ከ 3 አመት በፊት የተዘጋጀው አገራዊ የነቀርሳ እቅድ ሰነድ አለ፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የነቀርሳ ቁጥጥር እስትራተጂክ እቅድ  (2ዐ16 እስከ 2ዐ2ዐ እ.ኤ.አ) ይባላል፡፡ ማጣቀሻ 3

ሰነዱ እንደሚገልፀው፣ “ነቀርሳ ጤናማ ያልሆኑ የሰውነት ሴሎች ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ ማደግ እና መራባት ሲጀምሩ፣ ለመግለጽ የሚያገለግል አጠቃላይ ቃል ነው፡፡ ቀጥሎም እነዚህ ጤነኛ ያልሆኑ  ሴሎች፣ ጤነኞቹን ቲሹ አባል አካላትን ጨምሮ ይወራሉም ያጠፋሉም፡፡ ነቀርሳ አንዳንድ ጊዜ ፣ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ከመስፋፋቱ (ከመሰራጨቱ) በፊት በአንድ የሰውነት ክፍል ውስጥ ይጀምራል፡፡  ዋና መገለጫው ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ ጤናማ ያልሆኑ ሴሎች ማደግ እና መሰራጨት ቢሆንም ነቀርሳ የሚለው ከ1ዐዐ በላይ የተለያዩ በሽታዎችን ያጠቃልላል” ይላል፡፡

የበሽታው ጠንቅ አስቀድሞ በሚጀምርበት የሰውነት አካል መሠረት ተለይቶ ሲታይ እንዲህ ነው፡፡

እንደ ብሔራዊ ነቀርሳ ቁጥጥር የ2ዐ14 እ.ኤ.አ መረጃ መሠረት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ  ከጠቅላላው በአመት ውስጥ ከሚከሰት ሞት በነቀርሳ የሚከሰት ሞት 5.8 ከመቶ ይሆናል፡፡ ምንም እንኳን ከአዲስ አበባ በስተቀር፣  ህዝቡን በሙሉ መሠረት ያደረገ አገራዊ መረጃ ባይኖርም፣ በአንድ አመት በአገሪቱ ውስጥ 6ዐ96ዐ የነቀርሳ ታማሚ እና 44 ዐዐዐ ሞት በነቀርሳ በሽታ ይከሰታል ተብሎ ይገመታል፡፡

ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ሞት ውስጥ ከ 8ዐ በመቶ በላይ የሚሆኑት 4ቱ ዋና ዋና በሽታዎች ከልብ ጋር ተያያዥ ሕመም፣ ነቀርሳ፣ የስኳር በሽታ እና ሥር የሰደደ የሳንባ ሕመም ናቸው፡፡

በአገር ደረጃ ያለው ስርጭት፣ በ ግሎባኮን በተደረገ ጥናት የተገኘ

በአገሪቱ ከጠቅላላው አዋቂዎች የነቀርሳ በሽታ፣  ቀዳሚዎቹ የጡት ነቀርሳ 3ዐ ከመቶ፣ የማሕፀን ጫፍ ነቀርሳ 13 ከመቶ፣ እና የትልቁ አንጀት ነቀርሳ 7.5 ከመቶ ነው፡፡ በአመት ውስጥ በነቀርሳ ከሚከሰት ሞት  2/3ኛው  የሴቶች ሞት ነው፡፡ ከላይ የሚታየው መረጃ ይህንኑ ያመለክታል፡፡

ይህ ቁጥር ተራ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህን ሁሉ የበሽታ ጫና በሴቶች ላይ ያመጣብን ምንድነው? ይህ የተነገረው ቁጥር ለጊዜው ያሰደነግጣል፣ በጥልቀት ስናስበው ግን ያልተቆጠረውስ ምን ያህል ይሆን ማለታችን አይቀርም፡፡ ሁሉንም ቤት ይቁጠረው፣ ቤት መቸም የማይችለው ጉድ የለም፡፡

  1. የበሽታው ደረጃ እና ምልክቶች፣

ለመሆኑ ይህ በሽታ አጀማመሩ ምን ይመስላል? በአገረ እንግሊዝ ከተዘጋጀ ብረስት ካንሰር ናዎ ላይ የተወሰደ መረጃን በአጭር እንመልከት፡፡ የጡት ነቀርሳን አስቀድሞ በእርከን እና በደረጃ ለይተው ይነግራሉ፡፡ ማጣቀሻ 4

የጡት ነቀርሳ የበሽታው ደረጃ ወይም እርከን

“የጡት ነቀርሳን በደረጃ ወይም በእርከን መለየት ያስፈለገው የዕጢእብጠቱን መጠን ለማጥናት ሲባል ነው፡፡ ተሰራጨቶ እንደሆን፣ እና ምን ያህል እንደተሰራጨ ለማወቅ፡፡ የጡት ነቀርሳውን ያለበት እርከን መረዳት የሕክምና ዶክተሩን የሚሆነውን ሁኔታ ለመገምገም እና የሕክምናውን ዘዴ ለእያንዳንዱ በሽተኛ ለማቀድ ይረዳዋል፡፡

የጡት ነቀርሳ እርከኑን (ደረጃውን) ለመግለጽ ዋናው ዘዴ ቲ. ኤን. ኤም TNM (tumour, nodes, metastasis) ይባላል፡፡ ይህ ማለት አቻ ትርጉሙ ትንሽ ዕጢእብጠትትልቅ ዕባጭ፣ ቀድሞ ከጀመረበት፡ ወደ ሩቅ የሰው አካል የተዘዋወረ በሽታ የመለየት ሥርዓት ነው፡ ፡ በዚህ በተባለውም ሥርዓት ብዙ ጊዜ  በሁለት ደረጃ እና በ4 እርከን ይከፈላል፡፡”

1ኛ ደረጃ የጡት ነቀርሳ ምንድነው?

በዚህ 1ኛ ደረጃ እያለ የተለያዩ እርከኖች አሉት፡፡

እርከን  1፣ ብዙውን ጊዜ እርከን አንድ ማለት ነቀርሳው በአንፃራዊነት ትንሽ እብጠት እና በጡት

ውስጥ  ያለ ነው፡፡

እርከን 2፣ ብዙውን ጊዜ እርከን ሁለት ማለት፣ ወደ አካባቢው ቲሹ መሰራጨት ያልጀመረ፣

ነገር ግን ዕጢእብጠቱ ከእርከን 1 ከፍ ያለ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እርከን 2 ማለት እንያ የነቀርሳ ሴሎች ወደ ላምፒ ኖድ ተሰራጭተው  ዕጢእብጠት  ወደ መሆን ይቃረባሉ፡፡

እርከን 3፣ ብዙውን ጊዜ እርከን ሶስት ማለት ነቀርሳው ትልቅ ነው፡፡ ወደ አካባቢው ቲሹ መሰራጨት

ጀምረው ይሆናል፡፡ የነቀርሳ ሴሎች በአካባቢው ባሉ ላምፒ ኖድ ውስጥ ይሆናሉ፡፡

እርከን 4፣ እርከን 4 ማለት ነቀርሳው ቀድሞ ከጀመረበት ወደ ሌሎች አባል አካል ተሰራጭቷል፡፡

ይህም  2ኛ ደረጃ ወይም ሜታስታቲክ ነቀርሳ ሆነ ማለት ነው፡፡

1ኛ ደረጃ እያለ የጡት ነቀርሳ ምልክቶች

ዴቪድ ዋርነር ደግሞ  በ1ኛ ደረጃ እያለ የጡት ነቀርሳ ምልክቶች ዋናዎቹ እንደሚከተለው ናቸው ይላል፡፡ ማጣቀሻ 5

በድረገጽ መረጃ መረብ ላይ ኤቭሪዴይ ሔልዝ የጡት ነቀርሳ ደረጃን በፎቶ እንደሚከተለው አስቀምጦታል፡፡ ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ቀጥሎ ያለውን ተመልከቱ፡፡ ማጣቀሻ 6

Everyday Health   Breast Cancer Stages

2ኛ ደረጃ የጡት ነቀርሳ  ምንድነው?

ብረስት ካንሰር ናዎ ሲቀጥሉም እንዲህ ይላሉ፣  “ይህ ሁለተኛ ደረጃ የጡት ነቀርሳው ከጡት ወይም ከብብት ሥር ተነስቶ ወደ ሌሎች የሰውነት አካል ተሰራጭቷል ማለት ነው፡፡  እንዲሁም በሌላ ስያሜ ሜታስታቲክ የጡት ነቀርሳ (secondary or metastatic cancer.)  ወይም ከባድ የጡት ነቀርሳ ይባላል፡፡ ማጣቀሻ 7

የ2ኛ ደረጃ የጡት ነቀርሳ የሚያድገው እንዴት ነው

“2ኛ ደረጃ የጡት ነቀርሳ የሚከሰተው የነቀርሳ ሴሎች በደም ዥረት (ጀረት )  ውስጥ፣ በሊምፍ ስርዓት ውስጥ ወይም በአካል እንቅስቃሴ አማካይነት ወደ ሌላ የሰውነት አካል ሲጓዙ ነው፡፡  በዚያም  በደረሱበት አዲስ ቦታ፣ ለምሳሌ ወደ ሳንባ ደርሰው ቢሆን ሌላ ዕጢእብጠት (tumour) ይፈጥራሉ፡፡

ይህ ሁለተኛ ዕጢእብጠት ወይም በቀላሉ 2ኛ ደረጃ ነቀርሳ ይባላል፡፡ እንዲሁም ሜታስታቲክ ዕጢእብጠት ይባላል፡፡ ይህ ዕጢእብጠት የተፈጠረው ከቀደመው ከጡት ነቀርሳ ሴሎች ነው፡፡

የ2ኛ ደረጃ የጡት ነቀርሳ ሌላ ቦታ የት ያድጋል

የተለመደው ወይም ብዙውን ጊዜ የ2ኛ ደረጃ  የጡት ነቀርሳ ሴሎች፣ ውስጥ ለውስጥ ተጉዘው  በሌላ አባልአካል  ውስጥ ድጋሚ የሚያድጉት በአጥንት፣ በጉበት፣ በሳንባ፣ በጭንቅላት (አንጎል) ውስጥ እንዲሁም በደንዳኔ (bowel)፣ አድሪናል ዕጢ (adrenal glands)፣ በቆዳ፣ እንቁላል ዕጢ (ovary) እና ሌሎችም አባልአካል  (other organs) ውስጥ ነው፡፡

የ2ኛ ደረጃ የጡት ነቀርሳ ምልክቶች፣

“የ2ኛ ደረጃ የጡት ነቀርሳ ምልክቶቹ ሄደው (ተጉዘው)እንዳደጉበት (ዕጢእብጠት እንደሆኑበት) የሰው አካል ይለያያሉ፡፡ ሆኖም የሚከተሉትን ምልክቶች ያሳያሉ፡

እነዚህ የበሽታ ምልክቶች ሁልጊዜም በዚህ በ2ኛ ደረጃ የጡት ነቀርሳ በሽታ ብቻ ይከሰታሉ ማለት አይደለም እና ሐኪምን ማማከር አስፈላጊ ይሆናል፡፡

የ2ኛ ደረጃ የጡት ነቀርሳ ይድናል ወይ?

“በዚህ ዘመን 2ኛ ደረጃ የጡት ነቀርሳ ማዳኛ የለውም፡፡ ነገር ግን አዲስ የተሻሻሉ የሕክምና አሠራሮች በዘመናዊ ሕክምና ውስጥ እየመጡ ናቸው፤ በዚህ የሕክምና ዘዴ የ2ኛ ደረጃ ነቀርሳ እድገትን ባለበት መቆጣጠር ይቻላል፡፡

ልብ በሉ፣ የእያዳንዱ ሰው የነቀርሳ እድገት ወይም መስፋፋት (እንዲህ እና እንዲህ ብቻ ነው) ብሎ መተንበይ አስቸጋሪ ነው፡፡ የሚያክመው ቡድን ሊነግር የሚችለው ግምታዊ ነገርን ነው፡፡”

  1. የምርመራ ዘዴ

3.1    የእራስን ጡት በየጊዜው መፈተሽ፣

ዴቪድ ዋርነር፣ አንዲት ሴት የራስዋን ጡት  እንዴት መፈተሽ  እንደምትችል የሚከተለውን ምክር ይነግራል፣

ልብ በሉ፣ ይላል ዴቪድ ዋርነር፣ የምታጠባ እናት ሆና ትኩሳት ያለው አስጨናቂ ህመም በጡቷ ውስጥ ሲኖር መግል የቋጠር እባጭ (እንፌክሽን) ሊሆን ይችላል፡፡ እንጂ ነቀርሳ ላይሆን ይችላል፡፡

በሽታው ከጀመር በኋላ በሁሉም ሴቶች ላይ በአንድ ዓይነት ፍጥነት አይባዛም፡፡ እንደየሰዉ ይለያያል፡፡ ለምሳሌ 1ኛ ደረጃ ውስጥ ከአንደኛው እርከን እስከ ሶስተኛው እርከን የሚደርሰው ምናልባትም፣

3.2   ምርመራ  በዘመናዊ ሕክምና  

የላብራቶሪ ቴክኖሎጂ ተመራማሪ የሆነው አቶ ማርቆስ ስለሺ “የህክምና ምርመራዎች ምንነትና አስፈላጊነት” ባለው መጽሐፉ ላይ እንደገለፀው  አንደኛው የምርመራ ዘዴ ማሞግራፊና ዜሮግራፊ ይባላል፡፡ የምርመራው ዓላማ የጡት ላይ እብጠትን ወይም ዕጢን ለመመርመር ነው፡፡

የምርመራው መነሻ፣ ጡት ላይ የተፈጠረ ጤናማ ያልሆነ የጡት ክፍል/ቲሹ ለምሳሌ ዕጢ ወይም ውሃ የቋጠረ እብጠት ካለ ለማመልከት የሚጠቅሙ ልዩ የሆነ ኤክስሬይ ናቸው፡፡  ማጣቀሻ 8

  1. በወቅቱ መታከም

ማንኛውም ዓይነት የነቀርሳ በሽታ ወይም በምንም ደረጃ ወይም እርከን ላይ የሚገኝ የጡት ነቀርሳን በሽታው እንደታየ ወድያው በተቻለ ፍጥነት ምርመራ አድርጎ ሕክምና መጀመር ይበጃል፡፡

የተለያዩ የመታከሚያ ዘዴዎች አሉ፡፡  በዋናነት

  1. በዘመናዊ ሕክምና ዘዴ መታከም
  2. የባሕል ሐኪሞች ዘንድ መታከም፡፡ (ባለፈው ጽሑፍ ላይ እንደተብራራው)

የባሕል ሐኪሞች ዘንድ የተለያዩ አማራጮች አሉ፡፡

አስተውሉ፣  የባሕል ሐኪሞች እንደተጠቀሰው ማከም የሚችሉት፣ የነቀርሳው በሽታ በ1ኛ ደረጃ ላይ በተለያየ እርከን ላይ እያለ ነው፡፡ 2ኛ ደረጃ ለደረሰው በሽታ በተለይም ወደ ውስጥ አባል አካል ለምሳሌ ቀድሞ በሽታው ከነበረበት ከጡት ተነስቶ ወደ ሳምባ፣ ጉበት፣ ሆድ፣ ድረስ ለተስፋፋ አጥጋቢ ሕክምና አያደርጉም፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከጡት ተነስቶ ወደ ሌላ ቦታ በቆዳ ላይ፣ በእጅ ላይ ቢከሰት በተቻለ መጠን ሊያክሙ ይችላሉ፡፡

አንዳንድ ታማሚዎች እንዲያውም ሁለቱንም የሕክምና ዘዴ ፈርተው ሳይታከሙ የሚቀሩም አሉ፡፡ ሁለቱንም ዘዴ መፍራት ብቻ ሳይሆን የበሽታውን አደጋ አስቀድመው በመፍራት ሕመሙን ከቤተሰብ ጭምር ደብቀው በላያቸው እንዲስፋፋ የሚያደርጉም ብዙዎች ናቸው፡፡  በምንም ምክንያት በሽታውን መደበቅ አያስፈልግም፡፡ ቢያንስ ለቤተሰብ፣ ለጎረቤት፣ ለባሕል ሐኪም፣ በቅርብ ለሚገኝ ሐኪም፣ መንገር ያስፈልጋል፡፡  ከላይ እንደተነገረው በሽታው ከትንሽ እብጠት ተነስቶ፣ ወደ ሌሎች የአካል ክፍሎች ተዛምቶ ጉዳት ያደርሳል፡፡

የበሽታው አደገኛነት አስቀድሞ ሲጀምር ከፍተኛ ሕመም የለውም፡፡ አጣዳፊ አይደለም፡፡  ቀስ እያለ፣ ያዝ ለቀቅ እያረገ ሥር ይሰዳል፡፡ ምንም ዓይነት ሕክምና ሳያደርጉ፣ በአመጋገብ እና በአኗኗር መሻሻል ሳያደርጉ፣በአንደኛ ደረጃ ውስጥ ከአንድ እስከ ሶስት እርከን ይደርሳል፣ ብሎም ወደ 2ኛ ደረጃ ይቀየራል፣ ይስፋፋል፡፡

ሁለተኛ  ደረጃ ደርሶ መስፋፋት ከጀመረ ማን ይችለዋል? አንድ ቦታ ተገኘ ብለው በቀዶ ጥገና ሲያክሙት ወይም በሌላ ዘዴ ቢያክሙት ያ የታከመው ቦታ የዳነ ይመስላል፤ ለካስ ቀድሞ  ወደ ሌላ ቦታ ደርሶ ጥቃት ጀምሮ ኖሯል እዚያ አዲስ በተከሰተበት ቦታ በሽታው እንደገና ይፀናል፡፡ ከዚያም የታማሚው የሕመም ሲቃይ ከባድ ይሆናል፣ አብሮ የሚጨነቀው ቤተሰብ ብዙ መከራ ውስጥ ይገባል፡፡  በዚህ ደረጃ ለደረሰ በሽታ ሕክምናው በጣም ውስብስብ ይሆናል፡፡

  1. አመጋገብን ስለ ማስተካከል

በየትኛውም ዘዴ እየታከሙ ቢሆን የአመጋገብ እና የአኗኗር ዘይቤን ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ለነቀርሳ ታካሚ የተሻሉ እና የተከለከሉ ምግቦች እና መጠጦች ከህክምና በቤታችን ላይ የተገኘ መረጃ ነው፡፡ ማጣቀሻ 9

የተሻሉ ምግቦች እና መጠጦች የሰውነትን የበሽታ መከላከል አቅም የሚያጎለብቱ፣ የነቀርሳ ሴሎችን የሚያዳክሙ ናቸው፤

የሚከለከሉ ምግቦች እና መጠጦች የሰውነትን በሽታ የመዋጋት አቅም አዳክመው፣ ለነቀርሳ ሴሎች አበረታች ሆነው በሽታው እንዳይባባስ ነው፡፡

ይህም ሆኖ አንዳንድ ሰው አለርጂክ የሚሆኑበትን  ምግብና መጠጥ ለይቶ ማወቅ አለበት፡፡

ለነቀርሳ ታካሚ የተሻሉ ምግቦችና መጠጦች

የነቀርሳ ታማሚ ወይም በሕክምና ላይ ያሉ ሴቶች መመገብ  ያለባቸው፣

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ከተጠቀሱት የዕፀዋት አይነት ውስጥ ጥቂት  ምስሎች

ለነቀርሳ ታካሚ/ታማሚ የተከለከሉ ምግቦችና መጠጦች

የምግብ አበሳሰል ጥንቃቄ፣

6   ሌሎች ሊረዱ የሚችሉ የዕፀዋት መድኃኒት

ሀ/  የተቀመመ የቤት ውስጥ መድኃኒት

የነቀርሳ ታካሚ ይህን ከሕክምና በቤታችን መጽሐፍ የተወሰደ፤  በቀላል የሚዘጋጅ ቅመም አዘጋጅቶ፣ ከሌላ ሕክምና ጋር አስማምቶ ቢጠቀም ጥሩ ነው፡፡ ……..

ግማሽ ኪሎ ነጭ ሽንኩርት የተፈጨ፣ ግማሽ ኪሎ ጥቁር አዝሙድ የተፈጨ፣ አንድ ኪሎ ማርና  አንድ ብርጭቆ ኮምጣጤ   (አቼቶ) በአንድነት ለውሶ ማዘጋጀት፡፡ ከዚህ ላይ ጧት እና ማታ አንድ የሾርባ ማንኪያ መዋጥ ነው፡፡ ይህንንም እስኪያልቅ መውሰድ እና ሲያልቅ እንደገና አዘጋጅቶ መጠቀም ነው፡፡ ይህንን እየተጠቀሙ ሌሎችንም የሕክምና ዓይነት በወቅቱ መከታተል እና የአመጋገብ መመሪያውን መከተል ነው፡፡

ለ/ እርድ፣ ነጭ ሽንኩርት እና ዝንጅብል

እርድ፣ ነጭ ሽንኩርት እና ዝንጅብል በእኩል መጠን አንድ ላይ ተወቅጦ፣ ደርቆ በዱቄት መልክ ይዘጋጃል፤ ከዚህ ላይ አንድ ሻይ ማንኪያ በሚጠጣ ውሃ ላይ በማድረግ መጠጣት፤

ሐ/  የተልባ ዘይት በዓይብ

በሙቀት ሳይጎዳ የተጨመቀ የተልባ ዘይት አንድ የሾርባ ማንኪያ፣ በአንድ ጭልፋ የቤት     ዓይብ አንድ ላይ ማሸት እና ለእንጀራ ማባያ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ምግብ በጀርመን ሳይንቲስቶች ለነቀርሳ ታካሚ እንደሚረዳ የተጠና እና የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡

መ/  በየሁለት ሳምንት ወይም በየወሩ የሰለመኪ ቅጠል ሻይ መጠጣት፡፡ ይህ ሻይ ለግማሽ ቀን

ያስቀምጣል፡፡ በሒደቱም ብዙ ጉዳ ጉድ ከሆድ ውስጥ ያፀዳል፡፡ በዚያውም ከሆድ ውስጥ

ጥገኛ ተውሳኮች ይወገዳሉ፡፡ ይህ ለሰውነት ድጋፍ ማድረግ ነው፣  ብርታት ይሰጣል፡፡

ሰውነት በሽታን እንዲዋጋ ይረዳል፡፡

ሠ/ በአሜሪካ አገር ጥቂት የታወቁ  ፀረ ነቀርሳ ዕፀዋት

ጀትሮ ክሎስ ከ 8ዐ ዓመታት በፊት በአሜሪካን አገር ነቀርሳን ለማከም ይገለገልባቸው የነበሩ  የመድኃኒት ዕፀዋት ስም በመጽሐፉ ላይ  ዘርዝሯቸው ነበር፡፡ የእነዚህ የመድኃኒት ተክሎች ውጤት በዚህ ዘመን በአሜሪካን አገር በፋብሪካ ደረጃ ተመርተው የቀረቡም ይገኛሉ፡፡   ማጣቀሻ  1ዐ

እንግሊዘኛ መጠሪያየአማርኛ አቻ ስምእንግሊዘኛ መጠሪያየአማርኛ አቻ ስም
Red clover blossomsቀይ ክሎቨር ቡጥ አበባ፡blue flagብሉ ፍላግ
burdock rootቡርዶክ ሥርgravel rootግራቭል ሩት
yellow dock rootቱልት፡ መቅመቆ፣bloodrootብለድ ሩት
blue violetሰማያዊ ቫዮለትdandelion rootዳንዳሊዮን ሥር
golden seal rootጎልደን ሲል ሥርchickweedቺክዊድ
gum myrrh6ከርቤrock roseሮክ ሮዝ
Echinaceaኤክኔሽያagrimonyአግሪሞኒ
aloesእሬትOregon grapeኦሪጎን ግሬፕ

እነዚህ የመድኃኒት ዕፀዋት ለምሳሌ ከእዚህ ዝርዝር ውስጥ መቅመቆ፣ ከርቤ እና  እሬት፣  በአገራችንም በባሕል ሐኪሞች ወይም ለቤት ውስጥ ሕክምና ሰፊ ግልጋሎት በመስጠት ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ሌሎቹም እንደ ቀይ ክሎቨር እና ኤክኔሽያ ያሉት ተክሎች በአገራችን ለምተው ይገኛሉ፡፡ ዳንዳሊዮን በብዛት ዱር በቀል ነው፡፡ በእውቀት ቢያለሙት ብዙ ጥቅም ይገኝበታል፡፡  ሌሎቹ እንደ ቡርዶክ፣ ቫዮለት፣ ጎልደን ሲል፣ ብሉ ፍላግ እና ሌሎችም  በእኛ አገር የሌሉ ናቸው፡፡ ጥቅሙን የተረዳ አምጥቶ ቢያለማ ወርቃማ ሥራ ነው፡፡

ሁልዳ ሬገር ክላርክ በዋናነት ምርጥ የካንሰር መድኃኒት ዕፀዋት የምትለው፤ 1) የጥቁር ዋልነት ቅርፊቱ በልዩ ብቃት የተጨመቀ፡ 2) በካብሱል መልክ የተዘጋጀ አርቲሚሲያ ዱቄት፣ እና 3) ቅርንፉድ ሲሆኑ፡ ስለዚህ ጉዳይ እና የሷ ልዩ የምርምር ግኝት ሁሉ በመጽሐፏ ላይ በሰፊው ተብራርቶ ይገኛል፡፡ ማጣቀሻ 11

በአገረ አሜሪካ የጀትሮ ክሎስ እና የሁልዳ ሬገር ክላርክ የተሻሻሉ መድኃኒት በፍብሪካ ደረጃ ለዚሁ ተብሎ የተዘጋጀ ይገኛል፡፡ ማስፈለግ ወይም ማጥናት ይቻላል፡፡

ቸር ሰንብቱ

ማጣቀሻዎች

ማጣቀሻ 1  ሐዲስ ገብረ መስቀል. በ198ዐ ዓ.ም. መጽሐፈ መድኃኒት. ብሔራዊ ቤተመዛግብት

እና ቤተ መጽሐፍት ድርጅት

ማጣቀሻ 2   ልዑል ወ/ሩፋኤል በ1975 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሀገር ባህል የዕፀዋት መድኃኒቶች ዝርዝር፤ 1ኛ ዕፀ ደብዳቤ እና 2ኛ ዕፀ ደብዳቤ፣ በብሔራዊ ቤተመዛግብት እና ቤተመጽሐፍት ድርጅት፡

ማጣቀሻ 3.   Federal Ministry of Health Ethiopia,2015, The National Cancer Control Plan

of Ethiopia 2016-2020

ማጣቀሻ 4 እና 7  © 2019 Breast Cancer Now is a limited by guarantee in England

ማጣቀሻ 5David Werner with Carol Thuman and Jane Maxwell. (2002). WHERE THERE IS

NO  DOCTOR, A   village health care handbook New Revised Edition, U.S.A,

ማጣቀሻ 6 Everyday Health   Breast Cancer Stages: By Tara Haelle Medically Reviewed by

Krystal Cascetta, MD

ማጣቀሻ 8 ማርቆስ ስለሺ አሊ፣ 2ዐዐ ዓ.ም የህክምና ምርመራዎች ምንነትና አስፈላጊነት

መጽሐፍ አንድ፣ Printed by  Branna P.E  Addis Ababa Ethiopia.

ማጣቀሻ 9 በቀለች ቶላ፤2ዐዐ9 ዓ.ም፣ ሕክምና በቤታችን፤ የቤት ውስጥ ባሕላዊ ሕክምና በተፈጥሮ

መድኃኒት፤  5ኛ እትም፡ አልፋ አታሚዎች፣ አዲስ አበባ፤

ማጣቀሻ 1ዐ JETHRO KLOSS, Back to Eden, The Classic Guide to Herbal Medicine,

Natural Foods and Home Remedies, since 1939, The Authentic

Kloss Family ®, 2009, Lotus Press, U.S.A

ማጣቀሻ11 Hulda Reger Clark, 2002,  The cure for all Diseases, With many exclusive case history,

Health Harmony, Patpar Ganj, Delhi-INDIA