May 5, 2019
Source: https://mereja.com/amharic/v2/114395

በቋራ ወረዳ ተፈላጊ ተጠርጣሪዎችን ይዘው ለማሳለፍ የሞከሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በቁጥጥር ሥር ውለዋል፤ ምርመራም ተጀምሮባቸዋል፡፡
በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ ቁጥር አንድ በሚባለው አካባቢ የብሔር ግጭት በመፍጠር ወንጀል፣ ተጠርጥረው የሚፈለጉ አምሥት ግለሰቦችን በመኪናቸው ሸራ አልብሰው ወደ መተማ ወረዳ ለማሻገር የሞከሩ አራት የመከላከያ ሠራዊት አባላት በአካባቢው ኅብረተሰብ በቁጥጥር ሥር ውለው ለፖሊስ ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡
የምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ ተወካይ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ዓባይ አሻግሬ ለአብመድ እንዳስታወቁት በቁጥጥር ሥር የዋሉት የመከላከያ ሠራዊት አባላት በቋራ ወረዳ ቁጥር 4 ነፍስ ገበያ አካባቢ ሠላም በማስከበር ተግባር ላይ ለሚገኙ የኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ደመወዝ ለመክፈል ሄደው ከፍለው ሲመለሱ ነው፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የመከላከያ ሠራዊት አባላትም ኮሎኔል አንገሶም አርአያ የ33ኛ ክፍለ ጦር 2ኛ ብርጌድ 1ኛ ሻለቃ አዛዥ፣ መጋቤ ሃምሳ አለቃ አባድር አብራሽ ሾፌር፣ አስር አለቃ ደጀን ቡልቶ የሒሳብ ባለሙያ እና ወታደር ሳምራዊት ገብረእግዚአብሔር የሒሳብ ባለሙያ መሆናቸውን ዋና ኢንስፔክተር ዓባይ ገልጸዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ሌሎች አምሥት በብሔር ግጭት ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ሁለት ክላሽ፣ 322 ጥይት፣ 157 ሺህ 900 ብር፣ ዘጠኝ የክላሽ ካዝና፣ ሁለት የወገብ ትጥቅ እንደያዙ ለሥራ በሚገለገሉበት ተሽከርካሪ ደብቀው ወደ መተማ ወረዳ ጉባይ ቀበሌ ሲያጓጉዙ ነው ሚያዝያ 25 ቀን 2011ዓ.ም ከቀኑ 11፡00 አካባቢ ሁሉም በኅብረተሰቡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት፡፡
ኅብረተሰቡ በተደራጀና ሥነ-ምግባር በተሞላበት አግባብ በሕግ ማስከበር ተግባር የተሠማሩ ሰዎች ሕግን ሲተላለፉ ሕግን ለማስከበር ያደረገው ተግባር የሚመሠገን መሆኑን የገለጹት ተወካይ