May 5, 2019

Source: https://mereja.com/amharic/v2/114325

ደጃዝማች ዑመር ሰመተር!! …..የኦጋዴኑ የበረሀው መብረቅ
ተገዳይ እወልወል እጠረፉ ዳር፤
የመትረየሱ ሼክ የለበን መምህር፤
ሞት ጠራህ አንተንም ዑመር ስመጥር!!! ጣልያንን ከአፈር የደባለቀ ጀግና

Image may contain: 1 person, meme and text

ደጃዝማች ዑመር ሰመተርበኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ለአገራቸው ነጻነት ሲሉ በፍጹም አገራዊ ፍቅር መተኪያ የሌለው ህይወታቸውን የከፈሉ አካላቸውን ያጎደሉ በርካቶች ናቸው፡፡ የቀደሙትን የእነዚሕን አባቶች ውለታ አቅም በፈቀደ በምናስታውስበት በዚ ገጽ ዛሬ ዕድል ቀናንና ታለቁን ኢትዮጵያዊ ጀግና ደጃዝማች ዑመር ሰመትረን ልንዘክር ተገናኘን…..እነሆ ሰውየው!!!

አዲስ አበባ ከተማ ከሚገኘው ከታላቁ አንዋር መስኪድ አጠገብ ‘’ዑመር ሰመትረ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት’’ የሚል መጠሪያ የተሰጠውን ት/ቤት ሲያስቡ ከታሪኩ በስተጀርባ መታሰቢያ የቆመላቸው እኝህ ሰው ማን ናቸው ብለው መጠየቅዎ ወይም በሌላ ሰው መጠየቅዎ አይቀርም…… የዛሬው ባለታሪካችን የተወለዱት በኦጋዴን አካባቢ ካልካዩ በተባለ ሥፍራ ሲሆን ዓመቱም 1871 ዓ.ም ነው፡፡ በልጅነታቸው የተለያዩ ሀይማኖታዊ ትምህርቶችን ባህላዊ ሥርዓቶችን እየተማሩ ያደጉት እኝህ ሰው የአስተዳደር ሰው ለመሆን በነበራቸው ፍላጎት የመሪነት ክህሎታቸውን ሊያሳኩ የሚችሉ የተለያዩ ጥረቶችን እየመኮሩና ከአካባቢው የጎሳ መሪዎች አሰራርና ተሞክሮን እየቀሰሙ ማደጋቸው ይነገራል፡፡ ለአካለ መጠን ሲደርሱም በአካባቢ አስተዳደር ስራ በመሰማራት አገራቸውን ያገለገሉ ሲሆን በቅድሚያ በባላባትነት ማዕረግ በመቀጠልም የሱልጣን ዓሊ የሱፍ እንደረሴ ሆነው በናኢባነት እንደዚሑም የኤል-ቡር ገዢ በመሆን ለ23 ዓመታት አገራቸውን በፍጹም ቅንነት አገልግለዋል፡፡

የታሪክ ጠላታችን ፋሺት ኢጣልያ የአድዋ ሽንፈቱዋን ለመበቀል ሴራ መጠንሰሱዋን አሀዱ ያለችው በወልወሉ ግጭት ነበር……የወልወል ግጭት መሠረቱ እንዲህ ነው…የእንግሊዝና የኢትዮጵያ መንግስት በሶማሊያ በኩል ባለው የግዛታቸው ወሰን በደንብ ለመከለል ስምምነት አድርገው ስለነበር ቀን ተቆርጦ ወደስራ ሲገባ ሥራውን እንዲያከናውኑ ከእንግሊዝ ኮሎኔል ክሊፎርድ ከኢትዮጵያ ወገን ደግሞ ፊታውራሪ ተሠማ ባንቴ በተሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት የወሰን ክልሉን ለማጥናት በተንቀሳቀሱበት ወቅት ካፒቴን ሺማትሩ የተባለ የኢጣልያ ተወላጅ ቀደም ሲል ከደረሰበት የወሰን ስምምነት መቶ ኪሎ ሜትር የሚያህል አልፎ እንደጠብ አጫሪነት መተላለፊያ ከለከለ…..በዚህ ነገር ግራ የተጋቡት የኢትዮጵያ ተወካዮች በሰውየው አድራጎት ላይ ማብራሪያ ለመስማት እንኩዋን ባላስቻለ ፍጥነት ጦሩን አዝምቶ በአየርና በምድር ጦርነት በመክፈት ያለውተዘጋጁትን የኛን ወገኖች አጠቃቸው……በዚሕ ጦርነት ፊት አውራሪ አለማየሁን ጨምሮ ቁጥራቸው 107 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በክብር ሲወደቁ 75 ያላነሱ የፋሽስት ወታደሮች ሞቱ……

ደጃዝማች ዑመር ሰመተርየአጣልያ ጦር በወልወል የጫረው እሳት በሰሜን ተያይዞ በነበረበት በዛ ቀውጢ ቀን አገር በጣልያን እንዳትወረር በዱር በገደሉ ሲጠባበቁ በነበረበት ወቅት በምስራቁ ኢትዮጵያ ክፍል ከደጃች አፈወርቅ ወልደሰማያት ጋር በመሆን ዑመር ሰመትር የትግሉን ጎራ ተቀላቀሉ፡፡ በዚሕም ወቅት ከአቻ ወንድሞቹ ጋር በተለያዩ የጦር አውደ ግንባሮች የተሰለፈው የሶማሌ ጦር ጠላትን መውጫ መግቢያ አሳጥቶ የእግር እሳት ሲሆንበት በተለይም ደግሞ በዑመር ሰመትረ የሚመራው ጦር ጎርበሌ ላይ መሽጎ እየወረወረ የጠላት ጦርን መድረሻ አሳጣው በመሪው በኡመር ሰመትር ኢትዮጵያውያን በድል ጎዳና ተራመዱ……አይቀጡ ቅጣት የተቀጣው የጠላት ጦር ሊመሽበት እንደሆነ ተረዳና ከሱው ብሶ ስሞታ ለዓለም መንግስት አሰማ……በዚሕ ስሞታው ካሳ እንዲከፈለው ብቻ አልጠየቀም ጀግናው ዑመር ሰመትር እንዲሰጠው ጭምር እንጂ…….በተለያዩ የጦር አውደ ግንባሮች ድልን መጎናጸፍ የጀመረው የዑመር ጦር ኤል ቡር ላይ ፋሺስት ቦታውን በስድስት ባታሊዮን ጦር ተከበበ….እውነታው የገባቸው የጦር አበጋዙ ለጊዜውም ቢሆን ማፈግፈጉን መረጡ…ፋሽስት ድል ያገኘ መሰለው..ይሁንና ለ5 ወራት ያሕል ጦራቸውን በማደራጀት የቆዩት ዑመር በ1930 ዓ.ም ሌሌት በጠላት ጦር ላይ ያልታሰበ አደጋ ጣሉ ያንን የተፈራ ባለ ብዙ ባታልዮን ጦር ከጥቅም ውጭ አደረጉት ….በድል እየዘመሩ ለሌላ ጥቃት ሽላቦ ላይ ሰፈሩ…..አሁንም ፋሺስት ሽላቦ ድረስ እየመጣ አላስቀምጥ አላቸው …እደገና ገጥመው ድል አደረጉት….በቆራሄም ጠላት አፈረ ከጠላት ምሽግ የጨበጣ ውጊያ በማካሄድ ታላቅ ጀበዱ ፈጸሙ…….የጠላት ጦር ኃይሉ እየከበደ ሲመጣ በጉርለጉቤው ጦርነት ዑመር በጠላት ጥይቶች ተመቱ……ደጃች ዑመር ሰውነታቸው በስድስት ጥይቶች በመቁሰሉ በጦርነት ለመሳተፍ ከማችሉበት ደረጃ ደረሱ…….በዚሁ ምክንያት ለህክምና በቅድሚያ ሀርጌሳ ከዛም በኬንያ በኩል ተጉዘው ወደ ሎንደን ተላኩ……….. እስከጦርነቱ ማብቂያ በሎንዶን የቆዩት ዑመር ሰመትር ነጻነት ሲመለስ ባንዲራ ሲሰቀል አርበኛው ሁሉ እየፈኮረና እያቅራራ ግዳጅ ሲጥል የድል አጥቢ አርበኛውም ለጀግንነቱ ምስክር ሲገዛ ፊታውራሪ ዑመር(በሁዋላ ደጅ አዝማች) በኦጋዴን ከጦርነቱ የተረፉትን አርበኞች አክብረው የሚገባቸውን ሸለሙዋቸው!!!………..ታላቁ ጀግናችን ዑመር ሰመትረ የተጣባቸው የጠላት ጥይት ጤና እየነሳቸው ቁስሉም እየመረቀዘ ስላስቸገራቸው በሀረር ከተማ ሀኪሞች ባሉበት ቦታ ሁሉ እየተዘዋወሩ ቢታከሙም ለመዳን ግን ሳይችሉ ቀረ በተወለዱ በ61 ዓመታቸው መጋቢት 10 ቀን 1936 ዓ.ም ከዚሕ ዓለም በሞት ተለዩ!!!…..ሐረር ከተማ በሚገኘው በአብደል መካነ መቃብር ልዑል መኮንን መኩዋንቶቻቸውን አስከትለው ክርስቲያንና እና እስላሙ በነቂስ ወጥቶ ለጀግና በሚሆን በሙሉ ወታደራዊ ክብር ተሸኙ!!! …..

በዚሕ የቀብር ስነ ስርዓት አብዶ ሀይድ የተባሉ የትግል ጉዋዳቸው ይህንን አንጀት የሚበላ ቅኔ ተቀኙላቸው…..

ተገዳይ እወልወል እጠረፉ ዳር፤
ተጋዳይ አፍዱግ ላይ እጠረፉ ዳር፤
ተጋዳይ ቆራሄ እጠረፉ ዳር፤
ተጋዳይ ሀነሌ እጠረፉ ላይ፤
የመትረየሱ ሼክ የለበን መምህር፤
ሞት ጠራህ አንተንም ዑመር ስመጥር!!!
……//…..
ክብር ለነጻነት ላበቁን አባቶቻችን!!
#MinilikSalsawi
ምንጭ፡
• የኢትዮጵያ ታሪክ – ተክለ ጻድቅ መኩሪያ
• ያልተዘመረላቸው – በፍጹም ወ/ማርያም
► መረጃ ፎረም – JOIN US