2019 May 05

Zaggolenews. የዛጎል ዜና

የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ሶለን ሚያዚያ 19 ቀን 2011 ዓ.ም በድንገት ዜና ዕረፍታቸውን ሰማን። ነጋሶ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ለሰባት ዓመታት አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት አገልግለው በራሳቸው ፈቃድ «በቃኝ» ብለው ሥልጣናቸውን ለቀዋል። ከሥልጣናቸው ከመነሳታቸው በፊት አይነኬውን የወቅቱን ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ፊት ለፊት የሞገቱ ብርቱ ሰው ነበሩ። በ1993 ዓ.ም የህወሓት ክፍፍልን ተከትሎ በተነሳው የፖለቲካ ጡዘት ነጋሶን ከባድ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። በወቅቱ ነጋሶ «አሁንስ መንግሥቱ ኃይለማርያምን መሰልከኝ» በሚል አነጋገር መለስን በአንድ ስብሰባ ላይ መሸንቆጣቸው የብዙዎችን አግራሞት አጭሯል።

ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ከሥልጣን በፈቃዳቸው የመልቀቃቸው ጉዳይ በእነአቶ መለስ ዘንድ በበጎ አልታየም። የሃሳብ ልዩነቱ የበቀል በትር አሳረፈባቸው። በሕግ የተፈቀደላቸው ጥቅማጥቅም በሕገወጥ መንገድ እንደ ጸደቀ በብዙዎች ዘንድ በሚታመን አዋጅ ተነጠቁ። አንድ የሚንቀሳቀሱበት መኪና እንኳን አጥተው የአገር ፕሬዚዳንት እግረኛ ሆነው በአደባባይ ታዩ። አንዳንዴ ታክሲ ተጋፍተው ሲሳፈሩ ያያቸው የአዲስ አበባ ሕዝብ ራራላቸው፣ አከበራቸው። ክብሩንም፣ ፍቅሩንም ለመግለጽ የታክሲ ሒሳብ ለመክፈል የሚሽቀዳደመው ሰው ብዙ ነበር። ነጋሶ ግን ስለሁኔታቸው ተጠይቀው «ሕዝቡ ይህን የሚያደርገው ለእኔ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ መሆኑ ይገባኛል። ይህም ሆኖ ነጻነት አይሰማኝም» ማለታቸው ይታወሳል።

ነጋሶ ብርቱና ተስፋ የማይቆርጡ ሰው ናቸው። መብታቸውን ለማስመለስ ብዙ ውጣ ውረዶችን አይተዋል። ለወቅቱ ፕሬዚዳንት እና ለፓርላማ አፈጉባዔ «በሕግ አምላክ» ሲሉ ተከታታይ የተማጽኖ ደብዳቤዎችን ጽፈዋል። ከቢሮ ቢሮ ተንከራተዋል። የኦህዴድ/ኦዴፓ የትግል አጋሮቻቸው በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ይህንን ሁሉ ግፍ እያዩ፣ እየሰሙ ከጎናቸው ሊቆሙ አልቻሉም። እንዲያውም በተቃራኒው አንዳንዶቹ በጨዋ ደንብ «እባክህ አትድረስብን» አሏቸው፣ አገለሏቸው። ቢቸግራቸው ዶሴ አንጠልጥለው መንግሥትን ፍርድ ቤት ገተሩ። ወጡ፣ ወረዱ። ድካም ብቻ ተረፋቸው።

«እልህ ድንጋይ ያስውጣል» እንዲሉ ነጋሶ በ1997 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ በደንቢዶሎ ተወዳድረው በማሸነፍ ፓርላማ ገብተው አገልግለዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት ለቁምነገር መጽሔት በሰጡት ቃለምልልስ እንዲህ አሉ። «አሁን ካለሁበት ቤት ውጣ ተብዬ ሁለት ጊዜ ደብዳቤ ጽፈዋል። ለቤት ውስጥና ለኑሮ የማጠፋው ገንዘብ ተከልክያለሁ። የምኖረው በ 1 ሺ 700 ብር የፓርላማ ገንዘብ ነው። መኪናም ተቀምቻለሁ። የቤት ሠራተኛ ባለቤቴ ናት የቀጠረችው። ጥበቃም በትንሽ ገንዘብ ቀጥሬ ነው። ለሕክምና የባለቤቴ ጓደኞች መድሃኒት ገዝተው ባይልኩልኝ ከባድ ይሆን ነበር። ጠዋትና ማታ አምስት ኪኒኖችን እወስዳለሁ። የደም ስሮቼ ይዘጋጋሉ። ለመመርመርና ውድ መድኃኒት ለመግዛት ገንዘብ የለኝም። ባለፈው ሳምንት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ፕሬዚዳንቱ ጋር በታክሲ ነው የሄድኩት። የአገሪቱ አቅም በሚፈቅደው ክብር እና ጥቅም ይገባኝ ነበር። ይህ ለእኔ ተከልክሏል።…»

ይህ ሁሉ ግፍ የተሸከሙት ነጋሶ ጊዳዳ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ገደማ የኦህዴድ/ኦዴፓ ማዕከላዊ ኮምቴ ተሰብስቦ ጥቅማጥቅም እንዲሰጣቸው ውሳኔ ማሳለፉ ተሰማ። ድጋፉ አንድ የቤት መኪና፣ የውጭ አገር ነጻ ሕክምና ይጨምራል ተባለ። የአንድ ዘመናዊ የተሽከርካሪ ስጦታ ሲሰጥም በቴሌቪዥን መስኮት አየን። ይህ የኦዴፓ እርምጃ እሳቸውን በቅርብ ርቀት የሚያውቁ ወገኖችን ሁሉ አስደሰተ።

ይህም ሆኖ ውሳኔው በተባለው መልኩ ተግባራዊ አለመሆኑን ለአዲስ አበባ አስተዳደር ልሳን ለሆነው አዲስ ልሳን ጋዜጣ ከመሞታቸው ቀደም ብሎ በሰጡት ቃለ ምልልስ ሹክ አሉ። «የኦሮሚያ ምክር ቤት ጽ/ ቤት መኪና ትርፍ ስላለ ለጊዜው በዚህ ተጠቀም ሌላ ይገዛልሃል ተብዬ ነበር። እስካሁን አልተገዛም። አሁንም በውሰት መኪና ነው እየተገለገልኩኝ ያለሁት። በአገር ውስጥና በውጭ አገር የማደርገውም ሕክምና በራሴ እንጂ በተገባልኝ ቃል መሠረት እየተሸፈነልኝ አይደለም» ብለዋል።

በታሪክ ትምህርት ሶስተኛ ዲግሪያቸውን የያዙት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በተለይ የኦሮሞ ባህል፣ ታሪክና እሴት የሚያጠናክሩ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድም ይታወቃሉ።

የነጋሶ ስንብት

ወዳጄ ጋዜጠኛ ኤልያስ መሠረት የነጋሶን የቅርብ ሰው ጠቅሶ እንደጻፈው ከሳምንታት በፊት የጤና ምርመራ ለማድረግ ወደ ጀርመን አገር መሄዳቸውን፣ አንዳንድ መድኃኒቶች ይወስዱ ከመሆኑ በስተቀር አጣዳፊ ሕመም እንዳልነበረባቸው፣ እዚያው በጀርመን አገር እግራቸው ላይ አነስተኛ ቀዶ ሕክምና አድርገው ነበር።

ነጋሶ ሆቴላቸው ውስጥ ሆነው በመጨረሻው ሰዓታት ከባለቤታቸው ጋር በኢንተርኔት መልዕክት እየተለዋወጡ ነበር። በድንገት መልዕክት መላላኩ ተቋረጠ። በአካባቢው የነበረችው ልጃቸው ወደክፍላቸው ስትገባ አባቷ ራሳቸውን ስተው አገኘቻቸው። ከዚያም ወደሆስፒታል ተወስደው ለሁለት ቀናት በሕክምና ሲረዱ ከቆዩ በኋላ እስከዘላለሙ አሸለቡ።

«ዳንዲ የነጋሶ መንገድ» በተሰኘና በዳንኤል ተፈራ የተዘጋጀ የግለታሪክ መጽሐፋቸው ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ለንባብ በቅቷል። መጽሐፉን አስመልክቶ የዚህ ጹሑፍ አቅራቢ በወቅቱ የሰጠው የተመጠነ ዳሰሳ እነሆ ቀርቧል። የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ግለታሪክ (Biography) በመጽሐፍ መልክ ታትሞ ገበያ ላይ መዋሉን የሰማሁት በጋዜጦች አማካይነት ነው። የነጋሶ ግለታሪክ በሁለት ምክንያት ማንበብ እንዳለብኝ በውስጤ ስለተሰማኝ ወዲያውኑ መጽሐፉን በእጄ አስገባሁት። አንዱና ዋንኛው ምክንያት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው በመሥራታቸው እና በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት ከኢህአዴግ ጋር መቆራረጣቸው ስለሚታወቅ ስለሁኔታው የተሻለና አዲስ መረጃ አገኛለሁ የሚል ተስፋ በውስጤ በማደሩ ነው። ሁለተኛው ምክንያቴ በጋዜጠኝነት ሙያዬ ዶክተር ነጋሶን በቅርብ ርቀትም ቢሆን የማወቅ፣ ቃለመጠይቅ የማድረግ እድሉን አግኝቼ ስለነበር የዋኸና ቀጥተኛ የሆኑ ፖለቲከኛ መሆናቸውን ለመረዳት ችዬ ነበር። እናም ይኽ ባህሪያቸው ያለፉትን የሕይወት ውጣ ውረዶች በግልፅ ለመንገር የሚያስችሉ በመሆናቸው ከሳቸው ግለታሪክ የምቀስመው ይኖረኛል የሚል ተስፋን በመሰነቄ ነው።

መጽሐፉን እጄ በገባ በሁለተኛው ቀን ፉት አልኩት። እንደገናም ዋና ዋና ጉዳዮችን ለመለየት ይረዳኝ ዘንድ መለስ ብዬ በወፍ በረር ቃኘሁት። የተሰማኝን እነሆ ለማለት ብዕሬን አነሳሁ።

አዎንታዊ ጎኖች

መጽሐፉ በስድስት ክፍሎች (ምዕራፎች) የተዋቀረ ነው። ስለነጋሶ ውልደት፣ አስተዳደግ፣ የሕይወት ውጣውረድ፣ የፖለቲካ ሀሁ በአንደኛውና በሁለተኛ ክፍል ተካትቷል። ከክፍል ሦስት ጀምሮ ነጋሶ ከኢህአዴግ ጋር ጋብቻ ፈጽመው በትዳር የቆዩበትን ዓመታት ያስቃኘናል። ስለህወሓት ክፍል፣ ስለቅንጅት ወዘተ ቀጣዩን ምዕራፎች ይዘዋል።

ዶክተር ነጋሶ ለመጽሐፉ ፀሐፊ ወይም ለእኛ ለአንባቢያን ሳይሰስቱ የሚያውቁትን፣ የሚያምኑትን፣ የሚሰማቸውን ነግረውናል። የልጅነት አስቸጋሪ የሕይወት ፈተናዎች ለመጋፈጥ የሰው ቤት ሳህን እስከማጠብ የደረሱበትን እንግልት በግልፅ የተናገሩበት መንገድ እጅግ ልብ የሚነካ ነው። ይኽ ሁኔታም ትናንትን ረስተው በዛሬ ማንነታቸው ለሚኮፈሱ ሰዎች ሁሉ ጥሩ ትምህርት የሚሰጥ ነው ብዬ አስባለሁ።

በአጠቃላይ በህወሓት ክፍፍል ወቅት የነበረውን ሁኔታ፣ የኤርትራን ሪፈረንደም ሂደት በገለልተኝነት ስሜት ሊነግሩን ሞክረዋል። ይኸም የሚያስመሰግናቸውና ጥሩ ችሎታ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

የሕገመንግሥቱ ጉዳይ

ሕገመንግሥቱ ሲረቀቅ በአርቃቂ ኮሚሽን ውስጥ ከተሳተፉ ሰዎች አንዱና ግንባር ቀደሙ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ መሆናቸውን የምናስታውሰው ነው። ዶክተሩ አወዛጋቢ የሆነውን የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 39 ማለትም «ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ ነው» የሚለውን አንቀጽ እንደሚደግፉ ይገልፃሉ።

ሕገመንግሥቱ በሚረቀቅበት ወቅት ስለተካሄደው ክርክር እንዲህ ይላሉ «… በተለይ አንቀጽ 39ኝን በተመለከተ በመሬት ጉዳይ ላይ ክርክር ተካሂዷል። እኔና ዳዊት አንቀጽ 39 መኖር አለበት፣ መሬት መሸጥ የለበትም የሚል አቋም ይዘን ተከራክረናል። የብሔር ጥያቄን በተመለከተ የኦሮሞ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብቱ እስከመገንጠል መከበር አለበት የሚል ነበር አቋሜ። እዚህ ጋር ‘መገንጠል አለበት’ ማለትና ‘የመገንጠል መብቱ ይከበርለት’ ማለት ልዩነት እንዳለው ልብ ማለት ያሻል። አሁንም የሕዝቡ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቱ መከበር ትክክለኛ ነው፣ ዴሞክራሲያዊም ነው እላለሁ» ይላሉ። (ገፅ 191)

ዶክተር ነጋሶ አንድነት ፓርቲን በተቀላቀሉበት ሥነ- ሥርዓት ላይ ደግሞ በተቃራኒው መገንጠልን እንደሚቃወሙ ተናግረዋል። ለዚህም በሰጡት ማብራሪያ እንዲህ ይላል። «… የብሔር ብሔረሰብ ጥያቄ ላይ መገንጠልን አልደግፍም። መብት ይከበር ነው የምለው። መገንጠልን እንደምቃወም በግልፅ ተናግሬያለሁ» ይሉናል። (ገፅ 296)

ዶክተር ነጋሶ «መገንጠል አለበት» ማለትና «የመገንጠል መብቱ» ይከበርለት ማለት የተለያዩ ናቸው ነው የሚሉን። እኔ ግን ከልዩነታቸው ይልቅ አንድነታቸው ይበልጥ ጎልቶ ስለታየኝ የነጋሶ መከራከሪያ የሚያሳምን መስሎ አልታየኝም። ማንኛውም ብሔር ብሔረሰብ የመገንጠል መብቱ ተከብሮለት ግን መገንጠሉን እቃወማለሁ የሚሉበት ሥነ አመክንዮ ሚዛን የሚደፋ አይደለም።

መገንጠልን የሚቃወም ሰው ይህንን የሚመለከትና የሚደግፍ፣ የሚያበረታታ፣ የሕግ እውቅና የሚሰጥ አንቀጽ ያውም ሕገመንግሥት ያህል ሠነድ ውስጥ ሲገባ በግልፅ ድምፁን ማሰማት ነበረበት። ዶክተር ነጋሶ ይህን ስለማድረጋቸው በመጽሐፉ ውስጥ አላሳዩንም።

የርዕዮተ ዓለም ጉዳይ

ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በመጽሐፉ ውስጥ በኢህአዴግ ቅር ከተሰኙበት አንዱና (ጉዳዩ በመፅሐፉ ውስጥ ስለተደጋገመ ምናልባትም ዋናው ጉዳይ ሊሆን ይችላል) አቶ መለስ ድንገት ብድግ ብለው የምንከተለው ነጭ ካፒታሊዝም ነው የማለታቸው ጉዳይ ነው። ነጋሶ ከዚህ ቀደም የሚያውቁት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም መሳቢያ ውስጥ የተቆለፈበት መሆኑ የመታለል ስሜትን ፈጥሮባቸዋል። ይህንንም በአንድ ወቅት ለአቶ መለስ አንስተውላቸው «የ1987 ፕሮግራምን አንብቦ

አቅጣጫውን የካፒታሊስት ግንባታ መሆኑን ያልተረዳና ተታለልኩ የሚል ሰው ሁለትና ሁለት አራት መሆኑን መደመር የማይችልና መሀይም ነው» ሲሉ እንደዘለፏቸው ይጠቅሳሉ።

በሌላ በኩል ዶክተር ነጋሶ ተታለልኩ የሚሉበት አብዮታዊ ዴሞክራሲ የጠራ ግንዛቤ እንዳልነበራቸው በመጠቆም በአንድ ወቅት አቶ መለስን «ይሄ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባለው ርዕዮተዓለም ከየት ነው የመጣው? ምንድነው?» ብዬ ጠይቄዋለሁ ይሉናል። በተጨማሪም ስለዚሁ ጉዳይ ሰለሞን ጢሞን ጠይቀው የአቶ መለስ አይነት ማብራሪያ እንደሰጣቸው ይናገራሉ።

እንግዲህ ዶክተር ነጋሶ ቢያንስ ይኽን እስከጠየቁበት ጊዜ ድረስ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጉዳይ የጠራ አቋምና አመለካከት አልነበራቸውም። የጠራ ርዕዮተ ዓለም ያልያዙበትን ፓርቲ (ግንባር) ከፍተኛ አመራር ሆነው እያገለገሉም ነበር። እንደገና ድንገት ተነስተው ደግሞ አብዮታዊ ዴሞክራሲን መንገድ ላይ ጥለውብን ወደነጭ ካፒታሊዝም ተሸጋገሩ ሲሉ ለልዩነታቸው አንድ የመነሻ ነጥብ እንደሆነ ይነግሩናል።

«… በውስጥ እምነቴ ሶሻሊስት ነበርኩ። ከኢህአዴግም ስቀላቀል አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወደሶሻሊዝም ይሄዳል በሚል ነበር። የተለየሁትም አብዮታዊ ዴሞክራሲን ትቶ ወደ ነጭ ካፒታሊዝም ሲጓዝ ነው…» (ገፅ 304) ይሉንና እንደገና ይኽን ማለታቸውን ይዘነጉና የለየለት ነጭ ካፒታሊስት ሥርዓት የሚከተሉ አገራት ርዕዮተ ዓለም የሆነውን የሊበራል ሥርዓት (ዴሞክራሲ) ጥሩ ነው ይሉናል።

«… ሊብራል ዴሞክራቶች የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፍትሕ ሥርዓት የሚዳብርበትን ሁኔታ ሊፈጥሩ ይችላሉ። ለእኔ እንዲህ ያለው ሥርዓት ቢገነባ ደስ ይለኛል… (ገፅ 307)» በማለት ይገልፃሉ። ይኽ ሁኔታ የነጋሶ ርዕዮተ-ዓለም አሁንም ያልጠራ መሆኑን አስገንዝቦኛል።

ኦህዴድ/ኦዴፓን በተመለከተ

ዶክተር ነጋሶ ከህወሓት ትውውቅ የነበራቸው በጀርመን አገር በነበሩበት ወቅት ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑን ይገልፃሉ። ከሚኖሩበት ጀርመን በካርቱም በኩል አድርገው ወደ ኢትዮጵያ የመጡትም ልክ ኢህአዴግ አዲስ አበባን በተቆጣጠረበት ግንቦት 1983 ዓ.ም እንደነበር ይተርካሉ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የኢህአዴግ/ ኦህዴድ አባል በመሆን ከፍተኛ ካድሬዎችን ጭምር በማሰልጠን፣ በከፍተኛ የአመራር ኃላፊነት ማገልገላቸውን ይገልፁና ድንገት ተነስተው ደግሞ ከአመለካከታቸው ውጪ ኦህዴድን እንደተቀላቀሉ ይነግሩናል።

«… በሌላ በኩል በአጠቃላይ በብሔርተኝነት ላይ የተመሠረተ ርዕዮተ ዓለም ላይ ያለኝ አመለካከት ከኦነግ ከለቀቅኩኝ በኋላ ተቀይሯል። ኦህዴድንም ስቀላቀል የግድ በኦህዴድ በኩል ወደ ኢህአዴግ መሄድ ስላለብኝ ነበር እንጂ ያኔም ብሔርተኝነት ከውስጤ እየጠፋ ነበር። ‘ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት’ የሚለው የኦህዴድ/ ኢህአዴግ አቋም ተስማምቶኝ ነበር (ገፅ 299)» ይሉናል።

ዶክተር ነጋሶ ስለብሔረተኝነት ያላቸው ርዕዮተ ዓለም ከኦነግ ከለቀቁ በኋላ መቀየሩን እየነገሩን ያለው ኅብረብሔራዊውን አንድነት ፓርቲን እየተቀላቀሉ ባሉበት ወቅት መሆኑ የተአማኒነት ጥያቄን ማስነሳቱ አልቀረም።» (የጸሐፊው ማስታወሻ፡- ለዚህ መጣጥፍ ቅንብር፤ የቁምነገር መጽሔት፣ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ የሰንደቅ ጋዜጣ፣ የኤሊያስ መሠረት ታዬ ድረ ገጽ…ያገኘሁዋቸው ዜናና መረጃዎችን መጠቀሜ ይታወቅልኝ)

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝጣ 26/2011

በፍሬው አበበ