May 6, 2019
Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አንድ ሚሊየን የሚደርሱ እጽዋትና እንስሳት የመጥፋት አደጋ እንዳዠበባቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።
ድርጅቱ ይህንን ያስታወቀው በፈረንሳይ ፓሪስ በብዝሃ ህይወት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ስብሰባ ባደረጉበት ወቅት ነው ተብሏል።
ከአንድ ሺህ በላይ ገጾችን በያዘው በዚህ ሪፖርት ከ15 ሺህ በላይ ጥናቶች የተፈተሸ ሲሆን 450 ተመራማሪዎች ተካተውበታል።
የሪፖርቱ ማጠቃለያም በ109 ሀገራት ተወካዮች እንደጸደቀም ድርጅቱ ገልጿል።
ሪፖርቱ ውስጥ ከአውሮፓውኑ 1970 ወዲህ የህዝብ ብዛት በዕጥፍ መጨመሩን ያሳየ ሲሆን፥ የዓለም ኢኮኖሚ ደግሞ በአራት እጥፍ ተመንድጓል።
በአንጻሩ ከ1980 እስከ 2000 ባለው ዓመት ደግሞ 100 ሚሊየን ሄክታር ደን ወድሟል ይህም የተፈጥሮ ቀውስ ካስከተሉ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ነው ተብሏል።
ከ1992 ወዲህ ደግሞ የከተሞች መስፋፋት በእጥፍ ሲጨምር የፕላስቲክ ብክለት ደግሞ ከ1980 ወዲህ በአስር እጥፍ አድጓል።
እንዲሁም ሪፖርቱ የመሬት መሸርሸር ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን አሳይቷል ይህም 23 በመቶ የሚሆነው የመሬት ምርታማነት እንዲቀንስ ምክንያት ስለመሆኑም ዘርዝሯል።
40 ገጾችን በያዘው የሪፖርቱ ማጠቃለያ የሰው ልጆች በተለይም ባለፉት 50 ዓመታት ለእጸዋቱና ለእንስሳቱ መጥፋት ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሷል።
ባለሙያዎች ታዲያ ችግሩን ለመከላከል እንደመፍትሔ ካስቀመጧቸው ጉዳዮች መካከል ምግብን በተመለከተ በኢንዱስትሪ የሚመረቱ የስጋ ውጤቶችንና የእንስሳ ተዋፅዖዎችን የምናማትርበት ጊዜ ላይ ነን ብለዋል።
ተመራማሪዎቹ መንግስታት ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወስዱ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርትን እንደዕድገት መለኪያ ከመመልከት ይልቅ ሁሉንም አካታች የሆነ ዘላቂ ዕድገት ላይ እንዲያተኩሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ምንጭ፦ቢቢሲFiled in:Uncategorized