‹‹ወጣቶች አማላይ ተስፋን ለመስማት አይደለም የሚታገሉት፡፡››

‹‹ፋኖ  ከእኔ በላይ ለሀገር እና ለህዝብ ብሎ ያለፈ ትውልድ ነው፤ እኛም የምንናፍቀው እና የምንደግፈው ይህንኑ ነው፡፡›› ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌ

‹‹ወጣቶች አማላይ ተስፋን ለመስማት አይደለም የሚታገሉት፡፡›› ረዳት ፕሮፌሰር ሰብስብ ሐዲስ (በወሎ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር ትምህርት ክፍል መምህር)

Image may contain: text

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድን ወደ መሪነት መምጣት ተከትሎ በሀገሪቱ የለውጥ ጉዞ ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ መንግስት የት ገባ? እስከሚያስብል ድረስ የመንጋ እና የደቦ ፍርድ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተስተውሏል፡፡ ቡድኖች ትዕዛዝ ሲያስተላለፉ፣ እርምጃ ሲወስዱና ፈራጅ ሲሆኑም ታይቷል፡፡

የሰላም ሀዋሪያ በጎ አድራጎት የፀጥታ አስከባሪዎች ማህበር ሊቀመንበር አበጀ ገበየሁ ማህበራቸው ለውጡን ለመደገፍ በ2010 ዓ.ም እንደተቋቋመ ይናገራል፡፡

‹‹የጅምላ ፍርድ እንዳይኖር እናስተምራለን፣ ግብረ ገብነት እንዲጎለብት እና ባህላችን እንዲመለስ እንሰራለን›› ያለው ወጣት አበጀ በውይይትና በመግባባት ችግሮችን መፍታት እየተቻለ በአሉባልታ ወሬዎች ችግር መፍጠርም ሆነ አደጋ ላይ መውደቅ እንደማይገባ ነው የሚናገረው፡፡ ወጣቱ የፀጥታ መደፍረስ የሚስተዋለው መንግስት እርምጃ ከመውሰድ ስለተቆጠበ ነው  ብሎ ያምናል፤ ህግ የማስከበር ክፍተት መኖሩንም እንደታዘበ ነው የነገረን፡፡  ወጣቱ የሰላም ባለቤት  መሆን እንዳለበትም ነው የተናገረው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን  ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እየመሯት ያሉት የተማሩ የሚባሉ ግለሰቦች፣ ንቁ የማህበራዊና ፓለቲካዊ ጉዳይ ተሳታፊና መሪዎች ናቸው፤ ማንም ሀገሩን የሚወድ ሀገሩን የሚያበላሽ ታሪክ መስራት የለበትም፤ ለሀገር ምን ሰርቼ ልለፍ ማለት እንጂ አፍራሽ ተግባር መፈጸም ነገ ተጠያቂ ያደርጋል›› ነው ያለው አበጀ፡፡

በሰከነ መንፈስ በማሰብ ኢትዮጵያን የበጎ አስተሳሰብ ባለቤት ለማድረግ ቂም በቀል እና ቁርሾ መቀረፍ እንዳለበት ይላል፡፡

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ሰብስብ ሐዲስ እንደተናገሩት ደግሞ አሁን የሚታየው የወጣቶች እንቅስቃሴ ነገን እኔን በሚመቸኝ እና በሚጠቅም መልኩ መስራት አለብኝ ከሚል ጥያቄና ፍላጎት የመነጨ ነው፡፡ በሀገራችን ታሪክ ወጣቶች ለውጥ እንዲመጣ ጥረት ሲያደርጉ፣ ሲታገሉ፣ በመጨረሻ ግን ለውጡ ተቀልብሶ ሲቀሙ ነው የምናስተውለው ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰሩ፡፡ ለዚህም የ1960ዎቹን እና የ1997 ዓ.ም የለውጥ እንቅስቃሴዎችን በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡
 

‹‹በእነዚህ ጊዜያት የወጣቶች ጥያቄ ሲመለስ ሳይሆን ሲቀማ ወይም ለሌላ ጥቅም ሲውል ያየንበት ነው፤ የዚህ ትውልድም የትግል ዉጤት የቀድሞው ታሪክ እንዳይደገምበት ስጋት ላይ ወድቋል፤ ስጋቱን ለመቅረፍም ወጣቱ በቀጥታ የራሱን እርምጃ ሲወስድ ይታያል፤ ውሳኔውንም ይሰጣል››ነዉ የሚሉት ምሁሩ፡፡
 ጥያቄው እንዲመለስለት ግን ወጣቱ በስርዓትና በአግባቡ እንዲታገል ማድረግ ይገባል፤  የወጣቶችን ትግል ትናንት፣ ዛሬ እና ወደፊትም በሚያበሩ በማይጠልቁ ከዋክብቶች የመሰሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ  ጨለማ ለመግፈፍ የሚደረጉ ትግሎች የሚያስከትሉትን ተጽዕኖ መመርመር ላይ ውስንነት እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡

እርምጃ መውሰድ እንጂ ከጉዳዩ በስተጀርባ ያለውን ነገር መረዳትና ማስተዋል ይጎድላል፤ በመሆኑም ወጣቱ የፖሊስን፣ የፍርድ ቤትን ወይም የሌላውን ህግ አስከባሪ ተቋም ተግባር ተክቶ መስራቱ  ውጤቱ ግጭት እና ጥፋት ስለሚሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
 

እናም ያልተመለሱ የስራ አጥነት፣ በሙስና የተዘፈቁ አመራሮች ይውረዱልንም ሆነ ሌሎች ጥያቄዎች ከኃይል ይልቅ በሰለጠነ አግባብ በሚደረግ ግፊት ሊመለሱ ይገባል ነው ያሉት፡፡ ለጫናው ደግሞ የሚያታግሏቸውን ተቋማት መምረጥ፣ ወይም መደራጀት ይስፈልጋል፡፡ የወጣቶች ማህበራትን በማደራጀትና በማደርጀት  ወጣቶቹ የሚጠይቋቸውን ጥያቄዎች ተቋማዊ ቅርፅ ማስያዝንም እንደመፍትሄ አቅርበዋል፡፡ በተበታተነ መልኩ ማቅረቡ ግን ተመልሶ ችግር ከመፍጠር ያለፈ ፋይዳ እንደሌለውም ነው የጠቆሙት፡፡

 

በመሆኑም የወጣቶችን አደረጃጀት ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት ጥያቄያቸው ምንድን ነው? አላማውስ? እቅድ አላቸው? ለጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ለተግራዊነቱ በተጨባጭ ይሰራሉ? የሚሉትን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
 

ወጣቱ ፍላጎቱን ለማስፈፀም የጉልበት አማራጭን የሚወስድ ከሆነ ግን ጥያቄው ተንጠልጥሎ ይቀራል፤ በኋላ ላይም ይቀለበሳል፡፡ ወጣቶች የሚታገሉት በህይወታቸው ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ እንጂ አማላይ ተስፋን ለመስማት አለመሆኑንም ተናግረዋል ረዳት ፕሮፌሰሩ ሰብስብ፡፡ በመሆኑም ወጣቶች ስራ አጥነት እንዲቀረፍ፣ የሃብት ፍትሃዊ ክፍፍል እንዲኖር፣ ከአደንዛዥ ሱስ የሚገላግሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አውታሮች እንዲነቃቁ ይሻሉ፡፡ ‹‹በወጣቶች ትግል የመጣው ፓለቲካዊ እፎይታ የአሸናፊነት ስሜትን አጎናፅፏል፤ ይህንን ወደ ተቋማትና ወደ ሀገር ግንባታ ማምጣት አስፈላጊ ነው፤ ድሉን ይዞ በተቃራኒ ጎራ የተሰለፈ ቡድንን ወይም አካልን ለመጎሸምና ለመኮርኮም የምንገለገልበት ከሆነ ግን ኢትዮጵያን ተጎጂ ያደርጋል›› ነው ያሉት ምሁሩ፡፡

በሀገሪቱ የፖለቲካ ቁንጮ ላይ ያሉ ግለሰቦች፣ የተማሩት እና ብዙኃን መገናኛ ደግሞ መሪ በመሆን ለወጣቶች ፈር ማሳየት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
 

የአማራ ክልል ሰላምና ሕዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌ ደግሞ  የመንጋ (የደቦ) ፍርድ እንደሚስተዋልና ይህም ወደ ጥፋት የሚወስድ መንገድ እንጂ፤ እንደማያዛልቅ ነው የተናገሩት፡፡ የደቦ ውሳኔዎች የመጓጓዣ እንቅስቃሴውን እያስተጓጎሉት መሆኑንም በማሳያነት አንስተዋል፡፡ ‹‹ወጣቶች በተለያየ መንገድ ተነሳስተው ስሜታቸውን ሊገልፁ ይችላሉ፤ ለውጡ የመጣውም በእነሱ ትግል ነው፡፡ ሆኖም ወደፊት አርቀው ማየትና ማሰብ መቻል አለባቸው›› ብለዋል ብርጋዴር ጀነራሉ፡፡  ‹‹ወጣቶች ብቻ ሳይሆን ድርጅቶችም አሁን ያለንበትን ሁኔታ ከልብና ከራስ በላይ ማሰብና መረዳት ይኖርባቸዋል›› ነው የሚሉት፡፡
 

 ‹‹ምናልባት ፋኖዎች ይህንን ያደርጋሉ የሚባል ከሆነ የፋኖዎች መገለጫ ይህ ተግባር አይደለም፡፡ ፋኖ የተከበረና የሀገር አደራ የተቀበለ ከ1928 ዓ.ም የጣሊያን ወረራ በኋላ ሀገርን ነፃ ያወጣ የጀግኖች መጠሪያ ነው፡፡ ከእኔ በላይ ለሀገር ለህዝብ ብሎ ያለፈ ትውልድ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ፋኖ ነው የምንናፍቀውም  የምንደግፈውም›› ነው ያሉት፡፡ ምክንያቱም ፋኖ ለሕዝቡ ቀድሞ መሰዋትነትን የሚከፍል፣ ሰብዓዊ ርህራሄ የተሞላ፣ ህብረተሰቡ ችግር ከሚያጋጥመው ይልቅ በእሱ ላይ እንቅፋት ተከስቶ ለመፍታት የሚታትርና የሚመኝ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

     ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ                         Image