ምንጭ – ኢትዮ ኦንላይን

2019-05-07 Author: ጌታቸው ወርቁ

የጎዳና ልጆች መከራ – ‹‹ታዳጊ-ወጣት ጥፋተኞች›› – አሃደ (፩)

(በዳሰሳ ጥናታዊ ምልከታ)

አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ፡-
ከኒው ዮርክ እና ከጄኔቫ ከተሞች በመቀጠል በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መናኸሪያነት የምትታወቀው አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ፣ በእንግዳ ዓይን ለሚመለከታት የአገሩን የዲፕሎማሲ ሥራ ሊከውን የተመደበ የውጭ አገር ዲፕሎማትም ሆነ፣ በዓለም አቀፍ ሥራ የተሰማራ የሌላ አገር ሰው፣ አሊያም ደግሞ ለደርሶ ተመላሽ አገር ጎብኚ እንግዳ (ቱሪስት)፣ ሰብዓዊ ምልከታ የሚጎረብጥ የዘወትር የጎዳና ላይ ትዕይንት አላት፡፡ በጎዳና ላይ የተጣሉ የጎዳና ልጆች (ስትሪት ቦይስ/ገርልስ) እና ባለቤት አልባ የጎዳና ውሾች በማኅበረሰብ የተገፋ አሳዛኝና ሰቅጣጭ የአደባባይ የጎዳና ላይ ኑሮ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የጎዳና ውሾችን የሚቆጣጠርበት ዘዴ አለው፤ በምሽትና በለሊት ውሾቹን በመርዝ የተለወሰ ስጋ በመመገብ ከገደለ በኋላ፣ አስከሬናቸውን ሰብስቦ በማቃጠል ቁጥራቸው ከመጠን በላይ ሆኖ የከተማ ነዋሪውን ህይወት እንዳያውክ ይሰራል፡፡

ሆኖም ግን፣ በተለያዩ ምክንያቶች ከወላጆቻቸው፣ ከቤተሰቦቻቸው፣ ከማኅበረሰባቸው ተለይተውና ርቀው በጎዳና ሰቅጣጭ ህይወት ላይ የተገፉ ታዳጊ-ወጣቶችን (ጁኒየር ዩዝ) ህይወት የሚታደግበት አሰራር የለውም፡፡ (በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ /ኢንጂነር/ በማኅበረሰቡና በመንግሥት ወደ ጎዳና የተወረወሩ ልጆችን ለመሰብሰብ ሙከራ አድርገዋል፤ ሆኖም፣ ከማኅበራዊ ፋይዳው ፖለቲካዊ ጠቀሜታው እጅግ ጎነና የታለመለትን ግብ አልመታም፡፡ ልጆቹ አሁንም ጎዳና ላይ ናቸው፡፡)

ስለዚህ፣ በእግርዎ ሲጓዙም ሆነ፣ በመኪና ሲንቀሳቀሱ ከፊት-ከኋላ፣ ከግራ-ቀኝ እጅዎትን ይዘው አሊያም ደግሞ የመኪናዎትን መስኮት ቆርቁረው አንዳች ልግስና የሚማጸንኦትን በተለያዩ ሱስ አስያዥ ንጥረ ነገሮች የደነዘዙ ከሲታ የጎዳና ልጆች ሰቅጣጭ የጎዳና ህይወት እያዩ ማለፍ እጅግ አሳዛኝ መሆኑን የተመለከተ ሁሉ ያውቀዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት የጎዳና ህይወት የቀን ተቀን ትርዒት፣ ከመዲናዋ አዲስ አበባ ከተማ ባሻገር ባሉ በየክልሎች ዋና ከተሞች ሀዋሳ፣ ናዝሬት/አዳማ፣ ሻሸመኔ፣ ባህር ዳር፣ ደብረ ብርሃን፣ ድሬዳዋ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች ሁሉ በየጎዳናው ዘወትር ይታያል፡፡ ‹‹የጎዳና ልጆች!›› ማኅበረሰቡ የሰጣቸው ሥያሜ ነው፡፡ እነርሱ ግን ቀረብ ብሎ ላናገራቸው ሰው የእከሌ እና የእከሊት ልጅ ነኝ ነው የሚሉት፡፡

ዳዊት አበራ (ሥሙ የተቀየረ) በአዲስ አበባ ስታዲየም ዙሪያ በሚገኙ ጎዳናዎች ላይ ህይወቱን የመሠረተ የ13 ዓመት ታዳጊ ወጣት ነው፡፡ በመዲናዋ ከሚገኘው ‹‹በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው የተገኙ ህፃናት ማቆያና ተሀድሶ ተቋም›› በተለምዶ (ጸባይ ማረሚያ) ተብሎ የሚጠራውን ተቋም፣ ነሐሴ 28 ቀን 2010 ዓ.ም ከለሊቱ 5፡30 ሰዓት ላይ አምልጠው ከወጡ ሃያ አምስት (25) ‹‹ታራሚ›› ልጆች መካከል አንዱ ነው፡፡

ቀይ የልጅ ፊቱ በጎዳና ጸሐይ ሀሩር ጥቁርቁር ብሏል፤ ጸጉሩ ካለመታጠብና ከቅባት እጥረት እርስ በእርሱ ተፈታትሎና ተያይዞ በተባይ ቀጭሟል፤ ከንፈሩ በሲጋራ ጢስ በልዞ- ደርቋል፤ አንገቱ በጭቅቅት ጠቁሮ፣ የሌላ ሰው ገላ መስሏል፤ ለግላጋ ታዳጊ ቁመቱ ከኮሰመነ ገላው ጋር ተዳምሮ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳለበት ያሳብቅበታል፤ የለበሰው አዳፋ የተቦጫጨቀና የነተበ ቲሸርት እና እግርጌው የተቆራረጠ ያለቀ ጂንስ ሱሪ (ስለሰፋው በቀበቶ ፈንታ በገመድ አስሮታል) ባለመታጠባቸው በቆሻሻ ግግር ደድረዋል፤ እግሮቹ ሁለት የተለያየ ነጠላ ጫማ ቢጫሙም፣ የተረከዙ ንቃቃትና የጣቶቹ መገረት ጎልቶ ይታያል፤ በዚህ ላይ ጫፉ በተቆረጠ የውሃ ላስቲክ ውስጥ ይዞ የሚስበው ‹‹ማስቲሽ›› (አንዳንዶች ቤንዚን ያራሰውን ጨርቅም ይስባሉ/ያሸታሉ) ቃና፣ የአካባቢውን አየር ይበክላል፤ ይህ ሁሉ ተዳምሮ አጠገቡ ቆሞ ለሚያናግረው ሰው ከሰውነቱና ከልብሱ የሚወጣው ጠረን ጋር ተቀላቅሎ ለአፍንጫ ስለሚቀረና ወደዱም ጠሉ ልክ እንደዚህ ተራኪ ያስነጥስዎታል፡፡ እጅግ መረር ያለ ተደጋጋሚ ማስነጠስ፤ አጢሹ! ሆኖም ይህ ለእርሱ ምኑም አይደለም፤ የዘወትር ኑሮው እና ህይወቱ ነውና፡፡

ዳዊት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጎዳና ህይወት ሊወጣ የቻለው በወላጅ አባቱ እና ወላጅ እናቱ ትዳር መፍረስ ምክንያት በ11 ዓመቱ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የላዳ ታክሲ ሾፌር የሆነው አባቱ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባል የሆነችው እናቱ፣ እርሱ ባልተረዳውና በማያውቀው ሁኔታ ትዳራቸው ፈርሶ፣ የቤት ዕቃ ተከፋፈሉና አባት ጉለሌ ክፍለ ከተማ ከሚገኘው የመኖሪያ ቤታቸው ውልቅ ብሎ ወጣ ሲል ለዘጋቢያችን ያስረዳል፡፡ እናት ልጇዋን ይዛ አባቱ በወር ለልጁ በሚያደርግላት ተቆራጭ እና በወር ገቢዋ ታግዛ ለተወሰነ ጊዜ ኑሯቸውን እንደ ቀድሞው ቀጥለው ነበር፡፡ ሆኖም፣ በሂደት እናቴ ሌላ የወንድ ጓደኛ ያዘች ይላል- ልጅ ዳዊት፡፡

በመጨረሻም ይህ ሰው በተለምዶ (ባህላዊ መንገድ) ለእናቴ ሁለተኛ ቧሏ ሆኖ ወደ ቤታችን ሲቀላቀል፣ ከእኔ ጋር አልተመቻቸንምና እኔን ከአስኮ ራቅ ብሎ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚገኝ የገጠር መንደር አያቶቼ (የእናቱ አባትና እናት) ጋር ቀላቀለችኝ ይላል፡፡

አያቶቼ እና አክስት-አጎቶቼ ለጊዜው በፈገግታ ቢቀበሉኝም፣ እየቆየ ከትምህርቴ ይልቅ በቀን ተቀን የግብርና ህይወታቸው ላይ ዋና አጋዥ እንድሆን አደረጉኝ ይላል፡፡

በማላውቀው ምክንያትም ደግሞ (ምናልባት ቁርጥ አባቴን ስለምመስል ይሆናል) ወንድ አያቴ ጥምድ አድርጎ ያዘኝ፡፡ ወንድ አያቴ ከአባቴ ጋር ጸብ ነበራቸው፤ አይግባቡም ነበር፤ ምናልባት የፍቺው አንዱ ነገር እሱ ይሆናል፡፡ ለእኔ ርህራሄ የነበራቸው ሴት አያቴና ትንሷ አክስቴ ናቸው፡፡ እነርሱ ግን የአያቶቼ ጎጆ ውስጥ ብዙም የወሳኝነት ቦታ አልነበራቸውም፡፡

በዚህ ላይ አጎቶቼና ትልቆቹ አክስቶቼ ዘወትር በእረኝነት ከብት እንድጠብቅና በግብርና ሥራ እንዳግዛቸው ብቻ ነው የሚፈልጉት፡፡ የእኔን ወደ ትምህርት ቤት መሄድ አይፈቅዱም፤ ብዙ ጊዜ እንድቀር ስለሚያደርጉኝ በትምህርቴም ተዳከምኩ፡፡ ሲብስብኝ ይህንን ሁኔታ ለአባቴ ደውዬ ባሳውቀውም፣ ምንም ሊያደርግልኝ አልቻለም፡፡

ነገሮች ሲከፉብኝ ሳላስበው በትምህርት ቤትም ሆነ በአካባቢዬ ተናዳጅ፣ አመጸኛና ተደባዳቢ ሆንኩ፤ እናም በመምህራኖቼ ‹‹ወላጅ አምጣ›› ሲደጋገምብኝ ወንድ አያቴ ትምህርቴን እንዳቋርጥ አደረጉኝና በእረኝነት ሥራ ላይ አሰማሩኝ፡፡

አንድ ቀን በዓመት በዓል ማግስት እናቴ ቤተሰቦቿን ለመጠየቅ ዳቦ አስጋግራ እና ነጭ ዐረቄ ይዛ መጥታ፣ ቡና ተፈልቶ ከሴት አያቴና ከአክስቶቼ ጋር ሲያወሩ፣ አባቴ ከሌላ ሴት ጋር ግንኙነት እንደጀመረ፣ ለእኔ ተቆራጭ ማድረግ ማቆሙን በቁጭት ስትናገር ሰማሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ለእርሱ ደውዬለት አላውቅም፡፡

ቀኑን ሙሉ ከብት የመጠበቅ የእረኝነት ኑሮ ሲከብደኝና በረባ ባልረባው ስህተት ዘወትር ከወንድ አያቴና አጎቶቼ የሚደርስብኝ የቀን ዱላ፣ ከትልልቆቹ አክስቶቼ የሚገጥመኝ የምሽት የታፋ ላይ ቁንጥጫና ግልምጫ ሲመረኝ ከዚህ ህይወት ለመውጣት ወሰንኩ፡፡

አንድ ቀን የዘመን መለወጫ በዓል ቀን ሲቃረብ፣ የአያቴን አንድ ሙክት በግ እና የአንዷን አክስቴን ሁለት ዶሮዎች ይዤ ወደ አስኮ ገብርኤል አካባቢ በመምጣት ከአንድ ከምግባባው ትልቅ ልጅ ጋር ተሻርከን ሸጥንና ምሳ ጋብዞኝ ሰባት መቶ ሃያ አምስት ብር አካፈለኝ፤ በጊዜው እንዲህ አይነት ብዙ ብር አይቼም ሆነ ይዤ ስለማላውቅና የሚያልቅ ስላልመሰለኝ ወደ መሐል አዲስ አበባ ገባሁ፡፡

ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ኪሴ ባዶ ሆነ፡፡ ሲርበኝ የምጠጋው የማውቀው የዘመድ ቤት ስላልነበረኝና ተቀብሎ የሚያሳድገኝ ህፃናት ማሳደጊያ ስለሌለ የተወሰነ ጊዜ የሸቅል ሥራ (ሸክም) ሞከርኩና ሲመረኝ ወደ ጎዳና ህይወት ወጣሁ፡፡
መጀመሪያ የተሰማራሁት ጊዮርጊስ ፒያሳ አካባቢ ነበር፡፡ እዛ ግን ከነባር ጎዳና ተዳዳሪዎች ጋር አልተስማማሁም፤ ምናልባትም የሚያውቀኝ ሰው በአጋጣሚ በመኪና ተሳፍሮ ሲወርድ ሊመለከተኝ ይችላል በማለት ወደ ለገሃር እና ስታዲዮም ዙሪያ አመራሁ፣ እናም እዛው ከተምኩ፤ ይላል ልጅ ዳዊት፡፡

(ዳዊት የሚናገረው ቋንቋ ቃላት በተለምዶ የአራዳ ወይም የዱርዬ ቋንቋ የሚባለውን ዘዬ ነው የሚጠቀመው፤ እርሱ የሰጠኝን መረጃ ይዤ በተለምዶ ጸባይ ማረሚያ የሚባለው ቦታ ውስጥ ያሉ የእርሱ ብጤ ‹‹ወጣት ጥፋተኞችን›› ሳናግርም ይኸው የዳዊት የቋንቋ አጠቃቀም ነው በብዙዎቹ አንደበት የጠበቀኝ፡፡) የዳዊት ቀጥተኛ አንደበት ሲደመጥ እንደሚከተለው ነበር፡-
‹‹ከጓደኞችህ ጋር ተማክረህ ከጸባይ ማረሚያ ለምን አምልጣችሁ ወጣችሁ፤ ከጎዳና ህይወት ‹‹ጸባይ ማረሚያ›› አይሻልም?
ዳዊት፡- ቦታው አይነፋም! አንተ ውስጡን ስለማታውቀው ነው፡፡ አሰልቺ፣ አታካች ለሰው ልጅ ምንም የማይመች ማጎሪያ ነው፡፡

እረ ቦታው አይነፋም!
ቦታው አይነፋም ማለት?
ደንበኛ ሸቤ (እስር ቤት) ነው!
‹‹ጸባይ ማረሚያ›› ተቋም አይደለም እንዴ?
እንደርሱ የሚሉት ሲያንቆለጳጵሱት ነው!
ማነው ያሳሰረህ?
እሙካ ናት! (እናቴ)
ለምን?
ጸባዬ እንዲሻሻልና እንድስተካከል!
‹‹ጸባይ ማረሚያ›› ተቋም ጸባይህ እንዲሻሻልና እንዲስተካከል አልረዳህም?
እንዲያውም በእልክ አብሰውኝ ነው የወጣሁት፡፡ ከዚያች ጠባብ ግቢ ውጪ (የፍርድ ቤት ቀጠሮ ወይም ህክምና) ከሌለህ የትም አያንቀሳቅሱህም፤ በትንሽ ጥፋት ይጋረፋሉ፤ ይደበድቡኃል፤ ከልጆች ጋር ከተጣላህ ድንጋይ ላይ ያንበረክኩኃል፤ በስፖርት ይቀጡኃል፤ ለተወሰነ ጊዜም ለብቻ አግልለው ያስቀምጡሃል፤ ቦታው ከባድ ነው- አይነፋም ብዬሃለሁ እኮ፡፡
እነማን ናቸው ስታጠፉ የሚደበድቧችሁ?

መጉዚቶችም፣ ጥበቃዎችም፣ ሁሉም ናቸው አይለዩም፤ ሶሻል ወርከሮቹና የህክምና አባላቶች ግን ይሻላሉ እነርሱ አይማቱም፤ ይመክራሉ፡፡

በመደብደብህ የደረሰብህ ነገር አለ?
ጣቴን በዱላ ሰብሮኛል፤ (ተጎጂ አውራ ጣቱን እያሳየኝ) ወገቤን በውሃ ጎማ ለምጦኛል (ሰውነቱ ላይ የወጣውን የግርፊያ ሰምበር እያመላከተኝ)
ማነው የመታህ?
አንድ ገገማ ጠባቂ ነው፡፡ ጥምድ አድርጎኝ ነበር፡፡ ከዛ ያላደረግኩትን ያወራል፤ ሊያመልጥ እየሞከረ ነው ብሎ ለሌሎች ያሳብቅብኛል፡፡

ልክ እንደ ልጅ ዳዊት ሁሉ፣ በአዲስ አበባ/ኢትዮጵያ በርካታ ታዳጊ ወጣቶች በቤተሰብ መለያየት፣ ባልተረጋጋ የቤተሰብ ህይወት (ግጭት)፣ በቤተሰብ ድህነትና በቤተሰብ ምጣኔ አለማወቅ፣ በሕገወጥ የህፃናት ዝውውር፣ በጎዳና ላይ ኑሮ ውስጥ በመወለድ፣ በሱሰኝነት፣ ኋላ ቀርነትና የማኅበረሰቡ ልጆችን አያያዝና አስተዳደግ ላይ ያለው አባታዊ (ፓትሪያርኪያል) የግንዛቤ ጉድለት (Poor Parenting style)፣ በአቻ ግፊት፣ በብዙሃን መገናኛ (ሚዲያ) እና ፊልሞች ግፊት እና በተለያዩ ወቅታዊና መጤ ባህሎች ተጽእኖዎች ሳቢያ ወደ ጎዳና ህይወት እንደሚወጡ የማህበረሰባዊ ሳይንስ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ኤደን ማቴዎስ (የአባት ሥም የተለወጠ) ‹‹በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው የተገኙ ህፃናት ማቆያና ተሀድሶ ተቋም›› በተለምዶ ‹‹ጸባይ ማረሚያ›› ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የምትገኝ የ14 ዓመት ታዳጊ ወጣት ናት፡፡ ተወልዳ ያደገችው በኢትዮጵያ ፌዴራል ግዛት በህዝብ ብዛት ከፍ፣ በቆዳ ስፋት አነስ ብላ በምትገኘው የ56 ብሄር ብሄረሰቦች ዋና ከተማ በሆነችው በደቡብ ክልል ሀዋሳ ከተማ ነው፡፡

ኤደን ቀይ ዳማ ፊቷ እና ለግላጋ ረዘም ያለ ቁመናዋ ልጅነቷን ይመስክራሉ፡፡ የአነጋገር ዘይቤዋ ወደ ወላይትኛ ቀበሌኛ ቅላፄ ይወስዳታል፡፡

በአንድ የተረገመ ቀን ከጎረቤት ልጅ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ተደባድባ ልጅቷን በመፈንከቷና ጉዳት በማድረሷ በወጣት ጥፋተኝነት ተከሳ፣ ብይን ተሰጥቶባት ወደ ጣቢያ እንደወረደች ነግራኛለች፡፡ በፍርድ ሂደትም (የስምንተኛ ክፍል ትምህርቷን መቀጠል እንዲያስችላት ) በሚል ከሀዋሳ ወደ አቃቂ ቃሊቲ (ገብርኤል ቤ/ክርስቲያን) አካባቢ ያለ ጣቢያ ተዛውራ፣ ከዚያም እድሜዋ ከግምት ገብቶ ወደ ‹‹ጸባይ ማረሚያ›› ወርዳለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ (ዓርብ ህዳር 14 ቀን 2011 ዓ.ም) በተቋሙ ውስጥ ከሚገኙ 97 ወንዶችና 10 ሴቶች መካከል አንዷ እንደሆነች የተቋሙ ሠራተኞች ገልጸውልኛል፡፡

እኔ በዚህ ተቋም ውስጥ በተገኘሁበት ጊዜ (ዓርብ ህዳር 14 ቀን 2011 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ) የተቋሙ የህክምና ሠራተኞች የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ነፃ ምርመራ በፈቃደኝነት አድርገው ስለነበር፣ ይህን ምክንያት አድርገው የልጆቹን ማህበራዊ ህይወት ለማጠናከር በሚል በደጋፊ አካላት ለስላሳ መጠጦች፣ ድፎ ዳቦ እና ቆሎ እየተመገቡ ልዩ ልዩ ስፖርታዊ ትዕይንቶች ከቀረቡ በኋላ ሙዚቃ ተከፍቶ የተወሰኑ ጭፈራና ዳንስ የሚችሉ ልጆች ተጋበዙ፡፡

ከዘጠና ሰባት ወንድ ልጆች ውስጥ በዳንስ ችሎታ ጎበዝ የተባሉ ሦስት ልጆች ወጥተው ውዝዋዜ (ዳንስ) ተወዳደሩ፡፡ ዓለማየሁ (ቻይና)፣ ናዖል እና ፍሬዘር ነበሩ፡፡ እንደስማቸው ቅደም ተከተል ከአንድ እስከ ሦስተኛ መውጣታቸው በማህበራዊ አገልጋዮች ተነገረና ተጨበጨበላቸው፡፡

ከአሥሩ ሴቶች ውስጥ ደግሞ ኤደን፣ አምሳል እና አንዲት ልጅ (ስሟን አልያዝኩም) ወጥተው ዳንስ ተወዳደሩ፡፡ ኤደን የደቡብ ሙዚቃ ሪትምን ተከትላ በደንብ መወዛወዝ (መደነስ) ትችላለች፡፡ ከውድድሩ መልስ ጠጋ ብዬ (የተቋሙ ሠራተኞች ሳይሰሙ)፡-
የተቋሙ አያያዝ ለልጆች እንዴት ነው፤ ልጅነታችሁን ከግንዛቤ ያስገባል፤ መብታችሁ ይጠበቃል? ስል ጠየቅኳት
ኤደን፡- (የተቋሙ ሠራተኞች እንዳይመለከቷት ዘወር- ዘወር ብላ መልከት ካደረገች በኋላ) እስር ቤት ውስጥ ደግሞ ምን መብት አለ?! (በማለት እኔኑ መልሳ ጠየቀችኝ፡፡)

የጓጓሽለትን የስምንተኛ ክፍል ትምህርት እዚህ በተሟላ ሁኔታ እያስቀጠሉሽ ነው?
ወይ ትምህርት! ፌዝ ነው- ቀልድ፤ ከጠዋቱ 2፡30 እስከ 6፡00 ሰዓት ክፍል እንገባለን፤ ብዙ ጊዜ አስተማሪዎች ይቀራሉ፤ ሥራም የለቀቁ አሉ፡፡ ከሰኃት በኋላ ሁልጊዜ እንዲሁ ሜዳ ላይ ተበትነን እንደ ከብት እየጠበቁን ያለነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በመኪና እጥረት የፍርድ ቤት ቀጠሮም ያልፈናል፤ በአግባቡ አይወስዱንም፡፡ እኔ ትምህርቴን ለመቀጠል እችላለሁ ብዬ ነበር ወደ እዚህ እንድዘዋወር የጠየቅኩት፤ እዚህ ወንድሜ እና አጎቶቼም ስላሉ እየመጡ ይጠይቁኛል የትምህርት ጊዜዬ አይቃጠልም ብዬ ተስፋ በማድረግ ነበር፤ ነገር ግን ቤተሰብ በሳምንት ሁለት ቀን (ማክሰኞና ዓርብ፤ ከስምንት እስከ አስር ሰዓት) ለ30 ደቂቃ ብቻ እንዲያነጋግረን ነው የሚፈቅዱት፡፡
ቤተ-መጻሕፍት ትጠቀማላችሁ፤ ለማጥናት?
ትቀልዳለህ?! ወፍ የለም፡፡
ወፍ የለም ስትይ?
የለም፤ አይሰራም፡፡
ገላችሁን መታጠቢያ ቦታስ አላችሀ?
አዎን፤ በሳምንት አንድ የገላ፣ አንድ የልብስ ሳሙና ይሰጡናል፤ ልብሳችንንም እናጥባለን፡፡ አሁን አሁን ለሴቶች በየወሩ ‹‹ሞዴስም›› ይሰጡን ጀምረዋል፡፡
ሰብዓዊ መብታችሁ ይከበራል?
ታሾፋለህ መሰል፤ እዚህ ውስጥ …
(እኔ እና ኤደን በማውራት ላይ ሳለን፣ አንድ የማህበራዊ ባለሙያ ወደ አጠገባችን መጥታ ‹‹ልጆቹን አሁን ማናገር አትችልም፤ ወረቀት ካመጣህ በኋላ ነው ማናገር የምትችለው›› በማለት ከገሰጸችኝ በኋላ፣ ንግግርችንን አስቆመች፤ ዔደንንም በዓይን የሆነ መልዕክት ነገረቻት፤ ኤደን እኔ ካለሁበት ራቅ አለች፡፡)

ከዛ ሞቅ ያለ የደቡብ ሙዚቃ ተከፈተ፡፡ አስጌ ‹‹ዴንዴሾ››! ብዙ ልጆች አቧራማው ጠጠር ሜዳ ላይ ወጥተው ይጨፍራሉ፡፡ ኤደንም አንድ ጠቆር ያለች (ስሟን ያልያዝኩት) ልጅን አስከትላ ጭፈራው ውስጥ ተቀላቀለች፡፡ ቅድም ዳንስ ሲወዳደሩ የነበሩ ልጆች የቤቱ ምርጥ ደናሾች ናቸው መሰል ቦታ ለቀቅ ተደርጎላቸው ሌሎቹ ልጆች እነርሱን ያጅቧቸዋል፡፡ በእግር እንቅስቃሴያቸው የሚቦነው አቧራና ሁሉም ለመጨፈር አንድ ቦታ ላይ በመሰባሰባቸው ኤደንን በደንብ እንድመለከታት አላደረገኝም፡፡ ብቻ ከጓደኛዋ ጋር በደቡብ ኢትዮጵያ የዳንስ ውዝዋዜ ስትደንስ ትታየኛለች፡፡ ለእነዚህ ታዳጊ ወጣቶች ህይወት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይም (ለዳዊት)ም ሆነ፣ በዚህ ‹‹ጸባይ ማረሚያ›› ተቋም ውስጥ ለምትገኘው ኤደንና ጓዶቿ የሚያስጨፍር፣ የሚያዝናና እና መኖርን የሚያስናፍቅ አይደለም፤ ይልቅ የሚያሳዝን፣ የሚያስለቅስና በልጅነት የዋህ አንደበት እረ የፈጣሪ ያለህ የሚያስብል ነው፡፡