
በማይናማር ታስረው የነበሩት ሁለቱ የሮይተርስ ጋዜጠኞች መለቀቃቸው ተሰማ። ጋዜጠኞቹ የታሰሩት ማይናማር ውስጥ በሮሂንግያ ሙስሊሞች ላይ የደረሰውን በደል በማጋለጣቸው ነበር ተብሏል።
እነዚህ ጋዜጠኞች ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ በተከበረው የፕሬስ ነፃነት ላይ በተወካያቸው አማካይነት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የ33 ዓመቱ ዋ ሎን እና የ29 ዓመቱ ኪያው ሶኤ ሶ የተለቀቁት የሚያንማር ፕሬዝዳንት ባደረጉላቸው ይቅርታ ነው ተብሏል። ጋዜጠኞቹ ለ500 ቀናት ከማይናማር ዋና ከተማ ርቆ በሚገኘው ያንጎን ከተማ ነበር የታሰሩት።
ጋዜጠኞቹ ሮሂንግያ ሙስሊሞች ላይ የደረሰውን በደል በማጋለጣቸው ጥፋተኛ ተብለው እያንዳንዳቸው የሰባት ዓመት እስር ተፈርዶባቸው ነበር።
የሁለቱ የሮይተርስ ጋዜጠኞች እስር በማይናማር የመገናኛ ብዙኃን ላይ እንደተቃጣ ጥቃት ተቆጥሮ የነበረ ሲሆን በሀገሪቱ ስላለው ዲሞክራሲም ጥያቄዎች ተነስተዋል።
• ግጭትን ለማባባስ ፌስቡክ ጥቅም ላይ ውሏል ተባለ
ጋዜጠኛ ዋ ሎን ከእስር እንደተለቀቀ ለቢቢሲ በሰጠው ቃል፤ በጋዜጠኛነት እንደሚቀጥልበት ተናግሯል።
“ቤተሰቦቼንና ባልደረቦቼን ለማግኘት ናፍቄያለሁ፤ ወደ ዜና ክፍልም እስክሄድ ድረስ ጓጉቻለሁ” ብሏል።
• ቦይንግ አደጋው ከመድረሱ በፊት ችግሩን አውቅ ነበር አለ
ጋዜጠኞቹ የተለቀቁት ከሌሎች በርካታ እስረኞች ጋር ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ በየዓመቱ ለማይናማር አዲስ አመት ከሚደረግ ይቅርታ ጋር የተያያዘ ነው።
የሮይተርስ ከፍተኛ ዋና አዘጋጅ ስለ ጋዜጠኞቹ ሲናገር፤ ለፕሬስ ነፃነት “ቀንዲል” የሆኑ ሲል አሞካሽቷቸዋል። አክሎም “ብርቱ ጋዜጠኞቻችንን የማይናማር መንግሥት በመልቀቁ በጣም ደስተኞች ነን” ብሏል።
• “የአደገኛ ግለሰቦች” የፌስቡክ ገጽ መዘጋት ጀመረ
የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ሂይውመን ራይትስ ዎች በበኩሉ፤ ጋዜጠኞቹን እንኳን ደስ አላችሁ ካለ በኋላ “አሁንም በርካታ ጋዜጠኞች በማይናማር በእስር ላይ ይገኛሉ።” ሲል አስታውሷል።
እነዚህ ጋዜጠኞች የማይናማር ዜግነት ያላቸው ሲሆን ለሮይተርስ ነበር የሚሰሩት። በቁጥጥር ስር ሲውሉም በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በፀጥታ ኃይሎች ስለተገደሉ 10 ወንዶች መረጃ እየሰበሰቡ ነበር ተብሏል።

በቁጥር ስር የዋሉት ዘገባው ከመውጣቱ በፊት ሲሆን፤ መረጃ አለን ብለው በአንድ ሆቴል የቀጠሯቸው እና መረጃ ያቀበሏቸው ሁለት የፖሊስ አባላት አሳልፈው እንደሰጧቸው በኋላ ላይ ለፍርድ ቤት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
• ጋዜጠኞች ስለ ለውጡ ማግስት ሚዲያ ምን ይላሉ?
እነሱ በእስር ላይ እያለ እያጠናቀሩት የነበረው ዘገባ የወጣ ሲሆን፤ ዘገባው በርካታ መረጃዎችን በመያዙና የደረሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና ሞት በማጋለጡ ተደንቆ ነበር።