2019 May 7

Zaggolenews. የዛጎል ዜና

” ታላቅዋን ትግራይ በተባበረ የተጋሩ ትግል እንገነባለን! ”  በሚል ሃይለቃል ቃል ወደ መድረክ የመጣው  ብሄራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ (ባይቶና)! የተሰኘ የፖለቲካ ድርጅት የፌደራል መንግስትን አስጠነቀቀ። ” አህያውን ትቶ ዳውላውን እንደሚባለው በኢህአደግ ጥፋት ትግራዋይንና የትግራይን ህዝብ እፋረዳለሁኝ ቢል የሞራልና የታሪክ ተጠያቂነቱ የከፋ እንደሚሆን እንዳለ ሆኖ በተግባር የሚያመጣው መዘዝም ከባድ እንደሚሆን የዚህ ድርጊት ጠንሳሾች ጠንቅቀው እንድያዉቁ ባይቶና ያሳስባል” ብሏል።

በትግራይ ክልል አዲስ እንደተወለደ የሚያስታውቀው ይህ ድርጅት ይህንን ያለው ከለውጡ በሁዋላ ወደ ሃላፊነት የመጣው አመራር፣ በተለይም አዴፓና ኦዴፓ በትግራይ ህዝብ ላይ አነጣጥረዋል በሚል መነሻ ነው። አሁን የታሰበውን የበጀት ቅነሳም ወሬ የዚሁ አካል አድርጎታል።

በምንግስት ደረጃ በይፋ ስለበጀት መቀነስ ጉዳይ የተባለ ነገር ባይኖርም ባይቶና የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በመጥቀስ በትግራይ ላይ የበጀት ቅነሳ ለማድረግ መታሰቡን ኮንኗል። ሲኮንንም የኢህአዴግ መንግስት፣ የፌደራል መንግስት በማለት ነው። የኢህአዴግ መንግስት ሲል ግን ህወሃትን እንደሚያጠቃልል ይፋ አላደረገም።

የትግራይ ክልል በጀት ለሌላ ክልሎች ለማከፋፈል እቅድ እንዳለውና ሃሳቡም እንዲፀድቅ በውስጥ ለውስጥ ርብርብ ላይ እንደሚገኙ የትግርያ ክልል መሪ ዶክተር ደብረጽዮን ሰሞኑንን ይፋ መናገራቸውን በዋቢነት ያወሳው ባይቶና፣  “ጠቅላይ ሚኒስትሩና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ለዚህ ያቀረቡት ተልካሻና ዘረኛ ነው” ብሏል።

“የትግራይ ህዝብ ላለፉት 27 ዓመታት ልዩ ተጠቃሚ ነበር” የሚል ምክንያት መቀረቡን ያወሳው መግለጫ፣ ባለፉት 12 ወራት የፌዴራል መንግስት በመንግስት መዋቅር ተጠቅሞ በትግራይ ህዝብ ላይ በቀጥታ ያነጣጠረ ዘረኛ ጥቃት ሲሰነዝር እንደቆየ ያትታል።

ባይቶና “የ4ኪሎው መንግስት”ሲል የሚጠራውን የኢትዮጵያ መንግስት፣ የታሪክ እዳ ውስጥ እንዳይገባ ደጋግሞ አስጠንቅቋል። ታላቋ ትግራይን በጋራ እንገንባ ሲል ጥሪ አቅርቧል። የታላቋ ትግራይ ብሄራዊ ኮንግረንስ በሚል የእንግሊዘኛ መጠሪያ ራሱን የሰየመው ይህ ድርጅት ኦሮማራ በሚል የተጀመረውን ህብረትም አውግዟል። የትግራይ ህዝብም በላዩ ላይ የሚደረጉ ማናቸውም ፀረ ደቂ ዓባይ ትግራይ እርምጃዎች በተባበረና በሳይንሳዊ ትግሉ ከባይቶና ጎን ተሰልፎ እንዲመክት ድርጅታዊ ጥሪያችንን አቅርቧል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል

የኢህአደግ መንግስት በትግራይ ህዝብ ላይ እየጎነጎነ ያለው ሴራ በአስቾኳይ ያቁም! (ከባይቶና የተሰጠ መግለጫ)

ኢትዮጵያ በከባድ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖምያዊና ማህበራዊ ቀውስ እየተናጠች እንደሆነ ሁላችን የምናውቀው ፀሀይ ያሞቀው ሀቅ ነው። የሀገሪቱ ሁለንተናዊ ቀውስ ተከትሎም ኢህአዴግ በአዲስ አጀንዳና ፊት መጥቻለሁ ብሎ ማወጁ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ በዚህ ሂደት በርካታ ምስቅልቅሎች የተከሰቱ ሲሆን ገሚሶቹ መልካም ገፅታ ያላቸው ናቸው፤ የተቀሩትና ኣብዛኞቹ ደግሞ በሀገራችን ታሪክ አዲስ አሉታዊ ገፅታ እየፈጠሩ ኢትዮጵያ ወደ ማትወጣው ጥልቅ አዘቅት ይዘዋት እየነጎዱ ነው፡፡ ከነዚህ መሀከል በህወሓት ስምና ሰበብ በትግራይ ተወላጆች ላይ ሲደረሰ የቆየና እየደረሰ ያለው ስነ-ልቦናዊና አካላዊ ጦርነት፤ እንዲሁም ኢኮኖምያዊ መገለልና መድሎ ግምባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የትግራይ ህዝብ ፋሽሽቱን የደርግ ስርዓት ለመገርሰስ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ተደራጅቶ በንቃት እየተዋደቀ ተኪ የሌለው አስተዋፅኦ ማበርከቱ የማይታበል ጥሬ ሀቅ ነው፡፡ ከነዚህ አንዱ የሆነውና በሀገሪቱ የመንግስትነት ታሪክ በአወንታም ሆነ በአሉታ የሚነሳው ህወሓት ነው፡፡ ህወሓት በኢህአዴግ የግንባሩ ማዕቀፍ ውስጥ በአሉታም ሆነ በአወንታ የሚወሳ ስራ ከሌሎች የግንባሩ አባል ድርጅቶች ጋር አብሮ የድርሻውን በመወጣት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አገሪትዋን በኢህአደግ መስመር በመምራት ሂደት ላይ የራሱ ሚና እንደነበረው አሌ የማይባል ሀቅ ነው። ነገር ግን የኢህአደግ ጥፋት የራሱ የግንባሩ እንጂ በኢትዮጵያ እውነተኛ ዲሞክራሲ፣ ፍትህና ልማት እንዲመጣ ከማንም በላይ ብዙ ዋጋ የከፈለ የትግራይ ህዝብ ሀላፊነት የሚወስድበት አንዳች ምክንያት የለም።

ሆኖም ግን አሁን በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ አመራር በውስጥ የፖለቲካ ውሳኔ መሰረት የትግራይን ህዝብ የማግለልና የማጥቃት ስራ ተቋማዊና መደበኛ ስራው አድርጎ መሄድ ከጀመረ ሰንብቷል፡፡ የዚህ ማሳያም ኦሮማራ የተባለ ከአግላይነቱ በላይ በጥላቻ የተሰባሰበና ሀይለኛ የስልጣን ጥማት የተጠናወተው ሀይል በህዝባችን የፈጠረው ጠባሳ ታሪክ አይረሳውም፡፡ ውጤቱ ሂደቱን ይወስናል በሚል አምባገነናዊ ፈሊጥ ስልጣን ላይ ለመውጣት የትግራይ ህዝብ በህወሓትነት በመፈረጅና ህዝባችን የኢህአደግ ጉድፍ የመጨረሻ ተሸካሚው ህዝብ አድርጎ በመክሰስ በህዝባችን ላይ የተቀናጀ ጉዳት ማድረስ እንደ ትልቅ ጥበብ ተቆጥሮ ስፍር ቁጥር የሌለው በደል ሲፈፀም ከርመዋል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ይኸው ሀይል የትግራይን ህዝብ በህወሓትነት ፈርጆ ኢላማ በማድረግ ስልጣን ላይ ከወጣም በኋላ የቆየው እኩይና በአንድ ብሄር ያነጣጠረ እርምጃው መንግስታዊ ስራው አድርጎት እየቀጠለ ይገኛል፡፡

የሚያሳዝነው ነገር የትግራይን ህዝብ በህወሓት እየፈረጁ በህዝቡ ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ ያሉ ሰዎች በረዥሙ የኢህአዴግ አፈናና ጭቆና ታሪክ በተጨባጭ ዋነኛ መሪ ተዋናይ የነበሩ ሰዎች መሆናቸው ነው፡፡ ይሁንና ራሳቸውን ከጥፋቱ ነፃ አድርገውና መሲህ መስለው ብቅ በማለት፤ እንዲሁም በተግባር የአገሪትዋ ህዝቦች በነሱ የአመራር ድክመት እያለቁ ባሉበት ነባራዊ ሁኔታ “ለውጥ አምጪ ነን” የሚል አጉል ፈሊጥ ይዘው በመቅረብ በህዝባችን ላይ ከመጀመርያዋ የእለተ ሹመታቸው ሳምንት ጀምረው መጠነ ሰፊ ህዝባዊ የጥላቻና የፍረጃ ድርሰቶች በመፍጠር የህዝቡን ህልውና አደጋ ውስጥ ለመክተት መፍጨርጨር ከጀመሩ ዋል አደር ብሏል፡፡ አልተሳካም እንጂ እነሱ ባቀዱትና ከሽነው ባቀረቡት ዶክመንተሪ ፊልም መሰረት ህዝቡን ለማጥፋት የቻሉትን ሁሉ ለማድረግ ወደ ሁዋላ እንደማይሉ ታዝበናል፡፡ ይህንን በአንድ ብሄር ላይ ያነጣጠረ ዘረኛ መንግስታዊ እንቅስቃሴ አልሳተፍም ብሎ ለጥሪያቸው ዳተኛ የሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ባይቶና በዚህ አጋጣሚ ማመስገን ይፈልጋል፡፡

ሰሞኑን ደግሞ የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር በሰጡት መግለጫ መሰረት ዶ.ር ኣብይ መራሹ የኢህአደግ መንግስት የትግራይ ክልል በጀት ለሌላ ክልሎች ለማከፋፈል እቅድ እንዳለውና ሃሳቡም እንዲፀድቅ በውስጥ ለውስጥ ርብርብ ላይ እንደሚገኙ የክልሉ ፕረዚዳንት ለህዝቡ ይፋ አድርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትሩና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ለዚህ ያቀረቡት ተልካሻና ዘረኛ ምክንያትም “የትግራይ ህዝብ ላለፉት 27 ዓመታት ልዩ ተጠቃሚ ነበር” የሚል እንደሆነ ዶ.ር ደብረፅዮን ገልፀዋል። ባለፉት 12 ወራት የፌዴራል መንግስት በመንግስት መዋቅር ተጠቅሞ በትግራይ ህዝብ ላይ በቀጥታ ያነጣጠረ ዘረኛ ጥቃት ሲሰነዝር የቆየ የ4ኪሎው መንግስት አሁን ደግሞ ትግራይ በመሰረተ ልማት ከሌሎች በልዩ ተጠቅማለች የሚል ልበ ወለድ ድራማ ይዞ ብቅ ብሏል።

አሸናፊው የኢህአደግ ቡድን ትግራይ ልዩ ተጠቃሚ ነበረች ቢልም፤ እንዲሁም ህወሓት (በተለይ ደግሞ የአባይ ወልዱ አስተዳደር) በትግራይ የሌለ የውሸት ዳታ እየጋገረ ለሚድያ ፍጆታ እያቀረበ በህዝባችን ላይ ከባድ ጥቃት እያደረሰ ቢቆይም፤ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ኤጄንሲ ባወጣው የክልሎች የድህነት መጠን መሰረት ትግራይ ከሁሉም ክልሎች የድሃ ድሃ እንደሆነች ፤ ክልላችን ከታዳጊ ክልሎች እንኳን መወዳደር እንዳልቻለች በሰነዱ አውጥቷል። የኢህአደግ መንግስት በትግራይ ህዝብ ላይ ከልክ በላይ ግብር ጥሎ ነጋዴዎቻችን ስራቸውን ጥለው እስከ መሰደድ ያደረሰ ከፍተኛ ብዝበዛ ሲያካሂድ ቆይተዋል። የፌዴራል መንግስት ከክልሉ የሚሰበስበው ብርና የሚለቀው አመታዊ በጀትም እጅግ የተራራቀ ነው። ባጭሩ ህዝባችን በልዩ ሊጠቀም ቀርቶ በልዩ ሲበዘበዝ እንደነበረ፤ ያላየውን እድገት አደግክ እየተባለ የውሸት ዳታ በሚድያ ሲናፈስ እንደነበረ ባይቶና በደንብ ይረዳል።

በመሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ሀቅ ይህ ሆኖ ሳለ በትግራይ ህዝብ ጥላቻ አይነ-ህሊናው የታወረ የፌዴራል መንግስት ግን የመንግስት ተቋሞች ካውጡት መግለጫ በተቃራኒ ትግራይ ልዩ ተጠቃሚ ነበረች የሚል ሀሳብ አዝሎ የትግራይ ህዝብ በጀት ለመቀነስ ሴራ እየጎነጎኑ መሆኑ ከራሳቸው የትግል አጋሮቻቸው ሰምተናል። ይህንን ምክንያት የሌለው መሰረተ ቢስ እርምጃ በኢህአደግ መድረክ ያለው የፖለቲካ ሹኩቻ ተቀጥላ መሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም። ህወሓት ኣኩርፏል፤ ሊታዘዝልኝ አልቻለም በሚል እንቅልፍ ያጣው የፌዴራል መንግስት አንዴ በህዝባችን ዶኪሞንታሪ ፊልማ ሰርቶ በህዝባችን ላይ ጆኖሳይድ ያውጃል፤ ሌላ ጊዜ ለተላላኪ የክልል መንግስታት ቀጭን ትእዛዝ ሰጥቶ የትግራይ ህዝብ መንገድ እንዲዘጋበት ይሰራል፤ በሌላ መልኩ ደግሞ የትግራይ ህዝብ በዚህ እኩይ ድርጊት ኣልንበረከክም ብሎ በፅናት ሲመክት-የትግራይ ህዝብ የሚጠቀምበት ብቸኛ የአፋር ክልል መንገድ ለመረበሽ እና አፋር ክልልን የትርምስ ማእከል ለማድረግ ብዙ ሙኮራዎች ከማድረግ ኣልፎ የህዝባችን በጀትም ለመዝጋት ብዙ ድንጋይ እየፈነቀለ እንደሆነ በግልፅ እየታዘብን ነው። ይህ ሁሉ የቀቢፀ ተስፋ ከንቱ መፍጨርጨር እንደሆነ ይገባናል።

በትግራይና በትግራይ ህዝብ ላይ የሚደረጉ ማናቸውም አደገኛ መንግስታዊ መድሎና ዘረኛ አሰራሮች በዚህ ከቀጠሉ ሌላ የታሪክ ዕዳ እንደሚወልዱ በደንብ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ መንግስት እውነተኛ ቁርጠኝነት ካለው እርምጃውን መጀመር ያለበት አቅፎ እሽሩሩ ከሚላቸው በያንዳንዱ ድርጅት ተወሽቀው የሚገኙ የራሱ የኢህአዴግ ቱባ ሙሰኛ ባለስልጣናትን ነው፡፡ ሆኖም ግን አህያውን ትቶ ዳውላውን እንደሚባለው በኢህአደግ ጥፋት ትግራዋይንና የትግራይን ህዝብ እፋረዳለሁኝ ቢል የሞራልና የታሪክ ተጠያቂነቱ የከፋ እንደሚሆን እንዳለ ሆኖ በተግባር የሚያመጣው መዘዝም ከባድ እንደሚሆን የዚህ ድርጊት ጠንሳሾች ጠንቅቀው እንድያዉቁ ባይቶና ያሳስባል፡፡

የኦሆዴድ ሀጥያት የኦሮሞን ህዝብ፣ የብአዴን ሀጥያት የአማራን ህዝብ እንደማይወክል ሁሉ በህወሓት ሀጥያት በመደርድር በንፁውና ከትርፍ መስዋእትነት ውጪ አንዳች ትርፍ ያልተጠቀመው የትግራይ ህዝብ ላይ የሚወሰደው ማንኛውም እርምጃ የሚኮነንና ፀረ ህዝብ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

እነዚህ አድልዎ፣ ቂም በቀልና ቀቢፀ ተስፋ የወለዳቸው በአንድ ብሄር ላይ ያነጣጠሩ መንግስታዊ እርምጃዎችና ውሳኔዎች ለመቀልበስ ድርጅታችን ባይቶና ከትግራይ ህዝብ፣ የትግራይ ህዝብን ከሚያከብሩ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችንና ድርጅቶች እንዲሁም ከመላው የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር በመሆን አበክሮ በፅናት እንደሚታገል ይገልፃል፡፡ ይነስም ይብዛም የሀጥያቱ ፈጣሪና ተቋዳሽ የሆነው ኢህአዴግ ምንም እንኳ ቀለሙ ቢቀያይር ሀጥያቱን ህዝባችን ላይ እንዲያራግፍ ከቶ አንፈቀድለትም፡፡ የትግራይ ህዝብም በላዩ ላይ የሚደረጉ ማናቸውም ፀረ ደቂ ዓባይ ትግራይ እርምጃዎች በተባበረና በሳይንሳዊ ትግሉ ከባይቶና ጎን ተሰልፎ እንዲመክት ድርጅታዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ክብርና ሞጎስ ለጀግና ሰማእታት!

ብሄራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ (ባይቶና)!

ሚያዝያ 29/2011 ዓ.ም

መቐለ!