May 8, 2019

ስለ መጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ – ዋና ሥራ አስኪያጅ ምደባ እና የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መጠናከር ካሰፈሩት ጽሑፍ
˜˜˜
- መንግሥት፥ በሚኒስትር እና በም/ል ሚኒስትር ማዕርግ ዋና ሥራ አስኪያጆችን ይሾም ነበር፤
- በመንፈሳዊ ጉባኤ አቅራቢነት በንጉሠ ነገሥቱ ፈቃድ ይሾሙ ነበር፤በዘመነ ደርግም ቀጥሏል፤
- በ3ኛው ፓትርያርክ ዘመነ ክህነት፣“ሊቀ ማእምራን” በሚል ስመ ማዕርግ የተጠሩም ነበሩበት፤
- ከቤተ ክርስቲያን ልዕልና ይልቅ የሿሚያቸውን ፍላጎት ስለሚያስቀድሙ የተሟሉ አልነበሩም፤
- ቤተ ክርስቲያን፣ አስተዳደሯን በሊቀ ጳጳስ ደረጃ ለመምራት ለብዙ ጊዜ ስትጠይቅ ቆይታለች፤
***
- ከነሐሴ 1 ቀን 1987 ዓ.ም ጀምሮ፣ በመረጠችው ዋና ሥራ አስኪያጅ መመራት ጀምራለች፤
- ብፁዕ ዶር. አቡነ ገሪማ፣ የመጀመሪያው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፤
- “ቤተ ክርስቲያን ሲሶ መንግሥት ናት ቢባልም የይዞታዋ ሙሉ ተጠቃሚ አልነበረችም”…
- “የአስተዳደር ሒደታችንን መገንባት የሚቻለው፣ትውልዱን በትምህርት ብቁ በማድረግ ነው”
- “ከመንበረ ፓትርያርኩ እስከ አጥቢያ ለዚህ በርትተን እንድንሠራ አደራ እላለኹ”/ብፁዕነታቸው/
***
የቤተ ክርስቲያናችን የአስተዳደር እና የሥራ አስፈጻሚ ከፍተኛ አካል የኾነው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ እንደ ዛሬው በሊቀ ጳጳስ ደረጃ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሳይመድበለት፣ በመሠረቱ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ባላቸውና ከመንግሥት በሚመደቡ ሹመኛ ሊቃውንት እና “ጥቁር ራሶች” ይመራ ነበር፡፡ ከ1966 አብዮት በፊት፣ በመንፈሳዊ ጉባኤ አቅራቢነት በንጉሠ ነገሥቱ ፈቃድ ይሰጥ የነበረው የዋና ሥራ አስኪያጅ ሹመት፣ ከለውጡም በኋላ በደርግ/ኢሕዴሪ መንግሥት ቀጥሎ እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ዘልቋል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን በ1951 ዓ.ም. የመንበረ ፕትርክናውን ነጻነት ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስትቀዳጅ የመጀመሪያው ፓትርያርክ ከነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ጋራ ለብዙ ጊዜ ከሠሩት አቶ ልሳኑ ሀብተ ወልድ ጋራ፣ አቶ በትረ ጽድቅ፣ ንቡረ እድ ድሜጥሮስ ገብረ ማርያም፣ ንቡረ እድ ኤርሚያስ ከበደ፣ አቶ ተድላ ዘዮሐንስ፣ አቶ መርሥኤ ኀዘን አበበ፣ አቶ መኰንን ዘውዴ፣ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል፣ አቶ ስሜነህ በቀለ፣ አቶ ገብረ ክርስቶስ መኰንን፣ ሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛው፣ ሊቀ ማእምራን ደምፀ ገብረ መድኅን እና ዶ/ር ማርቆስ ወልደ ኢየሱስ ይጠቀሳሉ፡፡
እንደ ንቡረ እድ ድሜጥሮስ ገብረ ማርያም እና እንደ አቶ መኰንን ዘውዴ ያሉት በሙሉ ሚኒስትር እና ምክትል ሚኒስትር ማዕርግ የተመደቡ ሲኾኑ፣ ከለውጡ በኋላ ደግሞ ለቦታው በተሰጠው “ሊቀ ማእምራን” በሚለው የቦታው የማዕርግ ስም እንዲጠሩ በወቅቱ በነበሩት ሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተፈቀደላቸውም ነበሩ፡፡ ሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛው እና ሊቀ ማእምራን ደምፀ ገብረ መድኅን፣ “ሊቀ ማእምራን” በሚለው ስመ ማዕርግ ተጠርተውበታል፡፡

ባለፈው እሑድ ረፋድ በሞተ ዕረፍት የተለዩን ብፁዕ ዶር. አቡነ ገሪማ፣ “የምሥራች” በሚል ርእስ በልሳነ ተዋሕዶ ዘኦርቶዶክስ መጽሔት 1987 ዓ.ም. እና በዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ኅዳር 1988 ዓ.ም. እትሞች ላይ ባስነበቡት እንዲሁም “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻” በሚለው መጽሐፍ በስፋት ባብራሩት ጽሑፍ እንደተቹት፣ “ከመንግሥት የሚመደቡት ዋና ሥራ አስኪያጆች ለቤተ ክርስቲያኒቱ ልዕልና ከማሰብ ይልቅ፣ የሿሚያቸውን ፍላጎት ለማሟላት ቅድሚያ ስለሚሰጡ፣ ለቤተ ክርስቲያን የተሟላ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡”
ከመንግሥት እየተሾሙ የመምጣታቸው ታሪክ፣ ቤተ ክርስቲያን “ከመንግሥት የአስተዳደር ይዞታ አንድ ሦስተኛውን ተጠቃሚ ነበረች” እየተባለ የሚነገርበትን የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ዘመነ ክህነት መነሻ ያደረገ የርስት ጉልት መተዳደርያ ጋራ የተያያዘ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ርስት ጉልት ሲባል ዓይነቱ ብዙ ነው፡፡
- መንቀያ እና መትከያ የሚባል የአገልግሎት ርስት፣
- ሑዳድ የሚባል የአንድነት ገዳማት መተዳደርያ ርስት፣
- ሪም ወይም ቀላድ የሚባል የስሪት መተዳደርያ ርስት፣
- የመስቀል መሬት፤
- መንቀያ፣ መትከያ፡- የሚባለው የመሬት ስሪት፤ የአድባራት አለቆች፣ የገዳማት መምህራን፣ የገጠር መሪጌቶች መተዳደርያ ነው፡፡ የይዞታው ዓይነት በየጊዜው የሚሾሙት አስተዳዳሪዎች በሹመቱ ላይ እስካሉ ድረስ ብቻ በአላባው እየተጠቀሙበት ቆይተው ከሹመቱ ሲነሡ ወይም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ የሚተካው አስተዳዳሪ ተረክቦ የሚተዳደርበት እንጂ የሚሸጥ የሚለወጥ፤ በውርስ በስጦታ ለሌላ የሚተላለፍ አይደለም፡፡ ይህ ዓይነቱ ስሪት ኹሉ በታቦቱ ስም ተመዝግቦ ሲገበርበት የኖረ ነው፡፡
- ሑዳድ፡- የሚባለው የመሬት ስሪት፣ በአንድነት ገዳም ተወስነው የሚኖሩ ጥሪት ቁሪት የሌላቸው መነኰሳት እያረሱ የሚጠቀሙበት የአንድነት ገዳም ርስት ጉልት ነው፡፡
- ሪም ወይም ቀላድ የሚባለው፣ በተራ ቁጥር 1 በተመለከተው ዓይነት የመሬት ስሪት፣ ለካህናት መገልገያ ተብሎ ከመንግሥት በጠቅላላው ተሰጥቶ በየደብሩ አለቆች ሓላፊነት ለካህናት ተደልድሎ በርስትነት የሚገበርበት ወይም ርስትነቱ የታቦቱ ኾኖ ካህናቱ በአላባው እየተጠቀሙበት በማደሪያ ያገልግሉበት ተብሎ የተሰጠ የቀላድ መሬት ነው፡፡
- የመስቀል መሬት፡- የሚባለው መኳንንትና ወይዛዝርት ሌሎችም ኹሉ ከገዛ ርስታቸው ቀንሰው ለቤተ ክርስቲያን መትከያ የሚሰጡት ርስት ጉልት ነው፡፡
እንግዲህ ቤተ ክርስቲያናችን ቅድመ ሰበካ ጉባኤ ስትተዳደር የነበረው፣ ከዚህ በላይ በየመልኩ ከተገለጹት የመሬት ዓይነቶች በሚገኘው የገቢ ምንጭ ነበር፡፡ የመተዳደሪያው ብዛት ጎልቶ ከመታየቱ በቀር ለካህናቱ መተዳደርያ ይኾን ዘንድ የተፈቀደው ርስት ጉልት የሚሰጠው ጥቅም፣ የአገልጋዮች ካህናትን ችግር ከመሸፈን አኳያ በቂ አልነበረም፤ ይዞታውን በተመለከተም፣ በስም “የሲሶ መንግሥት ባለቤት ናት” እየተባለ ከሚነገር በቀር፣ ከሰሞን መሬት እንኳ ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ እንዳልነበረች ብፁዕነታቸው አውስተዋል፡፡
ከዚህም በከፋ፣ ትጠቀምበት የነበረው የሰሞን መሬትና መጠነኛ የኪራይ ቤት ገቢ፣ ከየካቲት እና ከሐምሌ ከ1967 ዓ.ም. የመሬት፣ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት ዐዋጅ ወዲህ በመንግሥት ተወርሶ ቆይቷል፡፡ የሰሞን መሬቱ፣ በመሬት ለአራሹ መፈክር ተወሰደ፤ የኪራይ ቤት ገቢውም፣ ሕንፃዎቿና ቤቶቿ ሲወረሱ ቀርቷል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ ትሠራበት ወደ ነበረው የዐሥራት በኵራት አስተዋፅኦ እንድታተኩር የግድ አስፈላጊ ኾኖ በመገኘቱ፣ የሰበካ ጉባኤ እንዲቋቋምና ደረጃ በደረጃ እየተጠናከረ እንዲሔድ ተደርጓል፡፡ በ1965 ዓ.ም. በነጋሪት ጋዜጣ በወጣው ቃለ ዐዋዲ የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደሪያ ደንብ መሠረት፥ ከምእመናን በሚሰጥ አስተዋፅኦ፣ ከስእለት፣ ከሙዳየ ምጽዋት እና ከመንግሥት በሚገኝ የድጎማ ገንዘብ እንድትዳደር ተደርጓል፡፡

ሰበካ ጉባኤን በተጠናከረ መልኩ ለማደራጀት፣ የሕዝበ ክርስቲያኑን መንፈሳዊ ግዴታ በአግባቡ ለማሳወቅና ለማስፈጸም፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት አድርጎ ብዙ ማስተማርና ማስተባበር ያስፈልጋል፡፡ ጥንታዊት፣ ታሪካዊት፣ ብሔራዊት፣ ሐዋርያዊትና ሉዓላዊት ቤተ ክርስቲያን ከምትሰጠው አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሰፊ አገልግሎት ባሻገር፣ እምነትዋን፣ ሥርዓትዋንና ትውፊትዋን የሚቀናቀኑ ልዩ ልዩ ድርጅቶችን መቋቋም እንድትችል፣ የሰበካ ጉባኤን ገቢ በማጠናከር፣ መንፈሳዊውንና ማኅበራዊውን አገልግሎት ማስፋፋትና ማጎልበት ይኖርባታል፡፡
ካህናትና ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን ዓላማና ተልእኮ መሟላት፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው በተግባር ሊሰለፉ ይገባል፡፡ የካህናትና ምእመናን ኅብረት፣ ተሻሽሎ በወጣው ቃለ ዐዋዲ ተጠንቶ የቀረበውን የ20 በመቶ ክፍያ ተግባራዊ ሊያደርግ ይችላል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፤ የአጥቢያ አብያተ ክርስቶያናንም ኾነ በየደረጃው የተዋቀሩትን አካላት ያጠናክራል እንጂ የሚያስከትለው ጉዳት የለውም፡፡ ከዚህም ጋራ ቤተ ክርስቲያን፣ በየዓመቱ ከመንግሥት በተፈቀደው የ4 ሚሊዮን ብር የድጎማ በጀት እገዛም እያዘገመች መቆየቷ ግልጽ ነው፡፡
ሃይማኖት እና መንግሥት የተለያዩ እንደኾኑና መንግሥት በሃይማኖት፣ ሃይማኖት በመንግሥት ጣልቃ እንደማይገባ፣ በ1987 ዓ.ም. በጸደቀው ሕገ መንግሥት በግልጽ መቀመጡን የጠቀሱት ብፁዕነታቸው፣ የተለመደው አሠራር ከ1983 ዓ.ም. በኋላም ቀጥሎ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ይኹንና፣ ራስን በራስ ለማስተዳደርና ነፃ ለመውጣት ጥረት ከማድረግ በቀር አማራጭ እንደሌለን በመገንዘብ፣ በአምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ያልተቆጠበ ጥረት በቅዱስ ሲኖዶስ ወሳኝነት፣ በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ፣ ቤተ ክርስቲያናችን ራሷ በመረጠችው ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ አስተዳደሯን እንድትመራ መደረጉን አስፍረዋል፡፡

ይህን ተከትሎም፣ ከነሐሴ 1 ቀን 1987 ዓ.ም. ጀምሮ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አመዳደብ ሥርዓት፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ድንጋጌ ቦታ ተሰጥቶት፣ በየሦስት ዓመቱ የሥራ አስኪያጅነት ምርጫ እየተካሔደ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት፣ በሊቀ ጳጳስ ደረጃ የመጀመሪያው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ብፁዕ ዶር. አቡነ ገሪማ ናቸው፡፡
ብፁዕነታቸው፣ ከጎሠኝነትና ለዘመድ ከማድላት ፍጹም የጸዱ መኾናቸው በብዙዎች ይታመንባቸዋል፡፡ አብረዋቸው ከሠሯቸው ፓትርያርኮች ጋራ ፍጹም ታማኝነት ነበራቸው፡፡ ከማለዳ እስከ ምሽት የሚዘልቀው የቢሮ ሰዓታቸው፣ በደብዳቤ አጻጻፍ ሳይቀር ለሆሄያት አገባብ የሚያደርጉት እጅግ ጥንቃቄ፣ በተለይም በጽሑፍ የሚያስተላልፉት ትምህርትና ስብከት በልዩነት የሚታወሱባቸው ናቸው፡፡
ከብፁዕነታቸው በኋላ፦ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ፣ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ፣ ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እየተመረጡና በቅዱስ ፓትርያርኩ እየተመደቡ አገልግለዋል፡፡ በአኹኑ ወቅት በሓላፊነቱ ላይ የሚገኙትና በመጪው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ የሥራ ዘመናቸውን የሚያጠናቅቁት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ ዘጠነኛው ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡
የብፁዕነታቸው አደራ፡-

ያለፈውንና የጊዜውን ታሪካችንን መነሻ በማድረግ፣ ከአለፈውና ከአኹኑ ታሪካችን በመማር፣ የአኹኑንና የወደፊቱን የአስተዳደር ሒደታችንን መገንባት የሚቻለው፣ በአኹኑና በሚቀጥለው ትውልድ ጥረት ስለሚኾን፣ የአኹኑንና የሚቀጥለውን ትውልድ ለዚኹ ዓላማ በትምህርት ማዘጋጀቱና ብቁ ማድረጉ አማራጭ የማይገኝለት የቤተ ክርስቲያናችን ተቀዳሚ ሥራ መኾኑ ታውቆ በተግባር መታየት ይኖርበታል፡፡
ይህን ተልእኮ ለመፈጸምና ለማስፈጸም፣ ከመንበረ ፓትርያርኩ ቢሮ ጀምሮ፣ የሥራ ሓላፊነት የተጣለብን ሠራተኞች የየሀገረ ስብከቱ ሊቃነ ኤጲስ ቆጶሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳትና የየሥራ ዘርፉ ሓላፊዎች ኹሉ፣ የሚፈለግብንን ግዴታ በበለጠ መወጣት ይጠበቅብናል፤ የየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋይ ካህናትም ኹሉ ሊተባበሩ ይገባል፡፡ ለዚህም መርሐ ግብር አፈጻጸም፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች የኾን ኹሉ፣ በርትተን እንድንሠራ በቤተ ክርስቲያን ስም አደራ እላለኹ፤ በማለት ጽሑፋቸውን ቋጭተዋል፡፡