በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰብ/ የተቃጠለው ገዳሙ ክፍል

ከትናንት በስቲያ ሚያዚያ 28 ቀን 2011 ዓ. ም. በምስራቅ ጎጃም ዞን፤ አዋበል ወረዳ በምትገኘው እነጋትራ ሐና ገዳም አስተዳዳሪ የሆኑ መነኩሴ ከጦር መሣሪያ ጋር በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የወረዳው ባለስልጣናት ለቢቢሲ አስታወቁ።

የወረዳው አስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ይሄነው አበባው ከመነኩሴው ጋር 7 የጦር መሣሪያዎች የተያዙ ሲሆን፤ ስድስቱ ለገዳሙ መጠበቂያ ተብሎ ከመንግሥት ወጭ ተደርጎ ነው የተሰጣቸው ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ ሕጋዊ ያልሆነ አንድ ሽጉጥ የተገኘባቸው መሆኑን ገልፀዋል።

እምቦጭ የጣና ቂርቆስ መነኮሳትን ከገዳሙ እያስለቀቀ ነው

“ስድስቱ መሣሪያዎች ከመንግሥት ወጭ ተደርገው ይሰጡ እንጂ በማን ሥም እንደተመዘገቡ ገና እየተጣራ ነው” ሲሉ ኃላፊው አክለዋል።

ኃላፊው የገዳሙ አስተዳዳሪ ከዚህ ቀደምም ከኅብረተሰቡ ጋር ቅራኔ ነበራቸው ሲሉ ይገልፃሉ።

“ሌላ የኃይማኖት መገልገያ ቦታ ባለመኖሩ ኅብረተሰቡ ማንኛውንም የኃይማኖት አገልግሎት የሚያገኙት እዚያ ነበር፤ እኚህ ግለሰብ ወደገዳሙ ከገቡ ጀምሮ ሕዝቡ ወደገዳሙ እንዳይገባ መከልከሉን ኅብረተሰቡ ቅሬታ ሲያሰማ ቆይቷል” ይላሉ የአስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊው አቶ ይሄነው።

ለገዳሙ ተብሎ ከተፈቀደው መሬት ውጭ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ አስፋፍቶ ይዟል፤ በኃይል ነጥቆናል የሚሉ ቅሬታዎችንም ኅብረተሰቡ ሲያሰማ መቆየቱን ያክላሉ።

የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን መነኮሳት ጳጳስ በመግደል ተከሰሱ

ኃላፊው እነዚህም ቅሬታዎች በመኖራቸው መነኩሴው ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር እንደማይግባቡ ያስረዳሉ። ከትናንት በስቲያ የተፈጠረው ግጭትም መነሻው እነዚሁ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች መሆናቸውን ገልፀውልናል።

ግጭቱ የተፈጠረበትን ምክንያት ሲናገሩም፤ “በኅብረተሰቡ ቅሬታ ያሳደረውን መሬት ለማረስ መነኩሴው በሬዎች ይጠምዳሉ፤ ከዚያ በኋላ መሬቱ አይታረስም ከሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ግጭት ተፈጠረ” ይላሉ።

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ መንግሥት ቢጋር ለቢቢሲ እንደገለፁት፤ ቦታው ‘የወል መሬት’ ሲሆን የአካባቢው ማኅበረሰብ ታቦት ሲወጣ የሚያከብሩበት ነው።

ከዚህ ቀደም መነኩሴው ቦታውን አርሰው እንደሚያመርቱበት የሚናገሩት አስተዳዳሪው፤ ኅብረተሰቡ ቅሬታ በማሰማቱ ሰብሉን ለጋራ እንዳደረጉት ያስታውሳሉ።

ይህ ብቻም ሳይሆን ከእምነት ውጭ የሚያከናውኗቸው ተግባርት አሉ ሲሉም ኃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ጥያቄዎችን ኅብረተሰቡ ይሰነዝራሉ። ለመነኩሴነትና ለገዳሙ የሚመጥን አይደለም ሲሉ አቤቱታቸውን እንደገለፁላቸው ያነሳሉ።

ተዓምራዊቷ ቅድስት ማርያም ውቕሮ ገዳም

እስካሁን ድረስ የኅብረተሰቡ ጥያቄ ለምን ምላሽ ሳይሰጠው ቆየ? ስንል የጠየቅናቸው የወረዳው አስተዳዳሪ፤ በአካባቢው ማኅበረሰብ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ባለፉት ወራት ከምስራቅ ጎጃም ዞን ሀገረ ስብከት ጋር እርሳቸው ባሉበት ውይይት እንደተደረገ ያስታውሳሉ።

በዚህ ጊዜም መስተካከል አለባቸው ያሏቸው ስድስት ጉዳዮችን ከመነኩሴው ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ይናገራሉ።

ከእነዚህም መካከል ሥርዓተ ቀብር እንዲካሄድ፣ ቅዳሴ እንዲፈፀም፣ ሰበካ ጉባዔ እንዲኖረው፣ ምክትል ሊቀመንበርና የገንዘቡን ፍሰት የሚያስተዳድር አካል እንዲኖረው እንዲሁም መነኩሳት ተቀጥረው እንዲቀድሱ የሚሉ ነበሩ።

ስለ ጠልሰም ወይም በተለምዶ የአስማት ጥበብ ተብሎ ስለሚጠራው ምን ያህል ያውቃሉ?

ባሳለፍነው የካቲትና መጋቢት ወር ላይ ሕጉን በመከተል እንዲሠሩና ሕዝቡም አገልግሎቱን እንዲያገኝ ውሳኔ እንደተላለፈ ይገልፃሉ።

የወረዳው የአስተዳደርና የፀጥታ ኃላፊ አቶ ይሄነው እንደሚሉት፤ “መነኩሴው ለ28 ዓመታት በገዳሙ ውስጥ የኖሩ በመሆናቸው፤ ገዳም ስለሆነ ማንኛውም ሰው ኃይማኖታዊ አገልግሎት ማግኘት አይችልም” የሚል አቋም አላቸው።

በሌላ በኩል ኅብረተሰቡ ሌላ የኃይማኖት ተቋም የለም፤ የት እንሂድ? አለበለዚያ ሌላ ቤተክርስቲያን ሊሠራልን ይገባል የሚል ጥያቄም ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ያክላሉ።

“በዚህ አለመግባባት ምክንያትም የአካባቢው ማኅበረሰብ ሰው ሲሞት ሌሎች አጎራባች ቀበሌዎች በመሄድ የቀብር ሥነ ሥርዓት ያስፈጽማሉ” ይላሉ።

እየሩሳሌም ለምን የኢትዮጵያዊያን ህልም ሆነች?

ይሁን እንጂ ከእሳቸው ጋር የሚቀራረቡና እሳቸውን የሚደግፉ ሰዎች በገዳሙ ውስጥ ኃይማኖታዊ አገልግሎት ያገኙ ነበር፤ ሲሞቱም የሚቀበሩት እዚያው ገዳሙ ውስጥ ነው፤ ይህም በኅብረተሰቡ መካከል መከፋፈልን ፈጥሯል ይላሉ አቶ ይሄነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ መነኩሴው ከሕዝቡ ጋር በሚያጨቃጭቃቸው መሬት ላይ ለማረስ በሬዎቻቸውን ጠመዱ ይላሉ።

በዚህ ጊዜ ኅብረተሰቡ ማረስ የለባቸውም ሲል ተቃወመ፤ እንዲያውም አንፈልጋቸውም ይውጡልን የሚል ጥያቄ ማሰማታቸውን ይገልፃሉ።

በመሀል ከማን እንደሆ ባልታወቀና ከገዳሙ ውስጥ በተተኮሰ ጥይት የአካባቢው ነዋሪ የሆነ የ22 ዓመት ወጣት እንደቆሰለ ያስረዳሉ።

ሰዎችን ከሲኖ ትራክ የገለበጠው አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ዋለ

በግጭቱ በገዳሙ ውስጥ ያሉት 10 በጭቃ የተሰሩ ቤቶች የተቃጠሉ ሲሆን፤ አምስት ትንንሽ የዕቃ ማስቀመጫ ቤቶችም በከፊል ተቃጥለዋል። በገዳሙ ውስጥ በተቃጠሉ ቤቶችና በቆሰለው ልጅ ምክንያት ምርመራ ለማድረግ ሲባል መነኩሴው በቁጥጥር ሥር ውለው እየተጣራ መሆኑን ነግረውናል።

‘ኅብረተሰቡ ከእኔ ጋር የማይስማማው ከሌላ ብሔር ስለመጣሁ ነው’ የሚል ቅሬታ በመነኩሴው ዘንድ ይነሳ እንደነበር የጠየቅናቸው አቶ ይሄነው፤ “አስተዳደሩ ከየትም ይምጣ ከየት? ሕጋዊ ሆኖ መቆየት አለበት የሚል አቋም ነው ያለን” ይላሉ።

“ነገር ግን መነኩሴው ያለመግባባት ችግር ነበረባቸው በዚህም ምክንያት ከኅብረተሰቡ ጋር በሚፈጠር ግጭት ‘ከሌላ ብሔር ስለመጣሁ ነው’ የሚል ቅሬታ ያሰማሉ” ብለዋል።

በስህተት የተሰጣቸውን 1 ሚሊየን ብር የመለሱት መምህር

አክለውም ግለሰቡ ለ28 ዓመታት በሠላም ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር የኖሩ ሲሆን፤ ከየት ብሔር እንደመጡም የሚታወቅ ነገር የለም ሲሉ ተናግረዋል።

“በአሁኑ ሰዓት ገዳሙ ሌላ ችግር እንዳይደርስበት በፀጥታ ኃይሉ እየተጠበቀ ሲሆን፤ ከሚመለከታቸው የኃይማኖት አባቶች ጋርም እየተነጋገርን ነው፤ ባለቤት የሆነ አካል ንብረቶችን እንዲረከብ ጥረት እየተደረገ ነው” ሲሉ ገልፀዋል።

በገዳሙ የዚያው አካባቢ የሆኑ ሦስት መነኮሳት የነበሩ ሲሆን እነርሱም ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅለዋል ብለዋል።

እነጋትራ ሐና ገዳም

መነኩሴው የገዳሙ አስተዳዳሪ እንዴት ሆኑ?

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀብርሃናት ካህሌ በቃሉ በገዳሙና በኅበረተሰቡ መካከል የሚነሳ የቆየ አለመግባባት ነበር ይላሉ።

የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ የገዳሙ አባቶችንና የወረዳው ኃላፊዎችን አሰባስበው ይህንን አለመግባባት ለመፍታት እንደሞከሩ ይናገራሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት ገዳሙ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት የተመሠረተ ሲሆን ሁሉም ሕዝብ ይገለገልበት የነበረ ቤተክርስቲያን ነበር። እኝህ አባት ከተመደቡ ጀምሮ ወደ ገዳምነት ተቀይሮ በአንድነት ገዳም እንዲተዳደር የሚል ውሳኔ አግኝቷል።

ቤተ ክርስቲያኑ ወደ ገዳም ሲቀየር ሀገረ ስብከት ውሳኔ ያሳረፈበት ሳይሆን ከመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ፅ/ቤት በቀድሞ በነበሩ አባቶች ውሳኔ እንደመጡ የሚያመለክት መረጃ እንዳገኙም ያስረዳሉ።

ሊቀብርሃናት ካህሌም ይህንኑ ሀሳብ ሲያፀኑ “የዞንም ሆነ የወረዳ አስተዳዳሪዎች ከዚህ ቀደም ገዳሙ ይመራ የነበረው እዚህ አካባቢ ባሉ ባለስልጣነት አለመሆኑን አያውቁም ” ይላሉ።

ሥራ አስኪያጁ ከዚህ ቀደም የአካባቢው ሰው በፍርሃት መንፈስ ወደ ገዳሙ ደፍሮ መግባት እንደማይገባ አስረድተው “ቦታው የሚታወቅበትና አስተዳደሩ በውል የማይታወቅበት ደረጃ ላይ ነበር የነበረው” ሲሉ ያስረዳሉ።

አሁን ግን ሕዝቡ ሲወያይ “የሰራነው ቤተክርስቲያን ነው፤ የፈለግነውን አገልግሎት ማግኘት አለብን፤ የገዳሙ አስተዳዳሪ ለሚፈልጉት ሰው አገልግሎት ይሰጣሉ፤ ሌላውን ያባርራሉ” ሲል ቅሬታ ማሰማታቸውን ይናገራሉ።

ከውይይቱ በኋላ ሀገረ ስብከቱ ውሳኔዎችን አስተላለፈ።

ገዳሙ የአንድነት ገዳም ከሆነ መስፈርቱን ማሟላት አለበት፤ በርካታ መናኒያን መኖር አለባቸው፤ ገዳም ቢሆንም ለኅብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት አለበት የሚል ነበር ውሳኔው።

በመሆኑም ይህም ገዳም ሰበካ ጉባዔ ተቋቁሞለት፤ የሰበካ ጉባዔ አባልነት ክፍያ እየተከፈለ፤ ህዝቡ የራሱን ተመራጮች አድርጎ እንዲገለገል ተወስኗል።

ከዚህ በኋላ የወረዳው ቤተ ክህነት ሠራተኞች የሰበካ ጉባዔ ሊመሰርቱ በሚሄዱበት ጊዜ ምዕመኑ እኚህ አባት ካልተነሱ አንመርጥም ሲሉ ተቃወሙ።

“ግለሰቡ ራሳቸውን የቻለ ልዩ ባህሪ ሊኖርባቸው ይችል ይሆናል” የሚሉት ሥራ አስኪያጁ መነኩሴው የተለያዩ ቦታዎች እየሄዱ እየለመኑ ገንዘብ በመሰብሰብ እዚህ አድርሰውታል ያስተዳድሩት ተብሎም ነበር። ሕዝቡ ግን አልተስማማም ይላሉ።

ከትናንት በስቲያም በተነሳው ግጭት ሕዝቡ በጡሩምባ ተቀሳቅሶ በመውጣት በገዳሙ የሚገኙ የፀበልተኞችን ቤት እንዳቃጠሉና አንድ ሰውም በጥይት መቁሰሉን እንደሰሙ ነግረውናል።

ለጥበቃ የተሰጠ መሳሪያ እንዳለ እንደሚያውቁ የተናገሩት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መሳሪያዎቹ እውቅና እንደተሰጣቸውና በየዓመቱ ቆጠራ እንደሚያደርጉ ሰዎቹ ሲገልፁ ነእንደነበር እንደሰሙ አስረድተዋል።

መነኩሴውም ከ30 ዓመታት በፊት በቦታውየተመደቡ ስለሆነ በሀገረ ስብከቱ ደረጃ የተመደቡበት ህጋዊ ደብዳቤ አላገኘንም ብለዋል።

ይሁን እንጂ ከህብረተሰቡ ጋር ካላቸው ቅራኔ በስተቀር ቦታውን ለውጠውታል ሲሉ ይመሰክራሉ።