
የእናት አገር ጥሪ
ሚያዝያ 27 ቀን 2011 ዓም(05-05-2019)
“ አገር አፍ አውጥታ ጮሀ ትጣራለች፣
ልጆቼ በህብረት አድኑኝ ትላለች።”
ለአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ
ኢትዮጵያ ሀገራችን በተደጋጋሚ የሚደቀንባትን አደጋና ወረራ በሕዝቧ አንድነትና የጋራ ትግል እያከሸፈች ለአያሌ ዘመናት ነፃነቷን አስከብራ ኖራለች፡፡ ምንም እንኳን ከባዕዳን ቅኝ አገዛዝ ነፃ ሆና ብትኖርም ከአገር በቀል አምባ ገነኖች፣ ከጨቋኝ ሥርአቶችና ከዘራፊዎች መዳፍ አላመለጠችም፡፡ በተለይም ላለፉት 28 ዓመታት የሰፈነው የጎሰኞች ሥርዓት የሁሉንም ዜጋ መብት የገፈፈ፣ የአገር ህልውናን ከአደጋ ውስጥ ያስገባ፣ የህዝቡን አንድነት በጎሳና በሀይማኖት ተዋረድ ያናጋና ደም ያፈሰሰ፣ ያገር ሀብትና ንብረት ያወደመ፣ዘርፎ ያዘረፈ፣ቋንቋን መሰረት ያደረገ ክልል የተባለ የልዩነት ግንብ ገንብቶ የኢትዮጵያውያንን ማንነት ያኮሰሰ አገራዊ ስሜት አልባ የሆነ የዘራፊ ቡድን እንደፈለግ የሚያዝበት ሥርዓት ነው፡፡
ይህንን ኢሰብአዊና ፀረ ኢትዮጵያ የሆነ ሥርዓት ለማስወገድና የዲሞክራሲን ባህል እንዲሁም የህግ የበላይነትን ለማስፈን አገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶች አባላት፣ የሲቪል ማህበራትና ምሁራን፣ ጋዜጠኞችና ወጣቶች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች በጋራና በተናጠል ብዙ ታግለዋል፤ ብዙ መሰዋዕትነትም ከፍለዋል፡በውጭ አገር በስደትና በልዩ ልዩ ምክንያት የሚኖረው ኢትዮጵያዊም የክረምት ዝናብ፣በረዶና ቁር፣የበጋ ቃጠሎ፡ሳያግደው ካገር አገር እየተንከራተተ ለዬአገራቱ መንግሥታት የወገኑን ብሶት ሲያሰማና ለወንጀለኛው መንግሥት ነኝ ባይ አገር አጥፊ ቡድን የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲመረምሩና ከሕዝቡ ጎን እንዲቆሙ ሲጠይቅ ኖሯል። የዚህ ሁሉ የረጅም ጊዜ ትግል ውጤት አሁን ላለንበት፣ በነበረው ሕገ መንግስትና የአስተዳደር መዋቅር ላይ ለሚተማመን፣ የባለሥልጣኖች ልውውጥ አብቅቶናል። ይህ የጎሳ መተካካት ተወግዶ አስተማማኝ በሆነ አገራዊ መሰረት ላይ እንዲቆም የማድረጉ ሥራ የአንድነት ሀይል በሚባለው አገር ወዳዱ ዜጋ ላይ የወደቀ ሀላፊነት ነው፡፡ ይህንን ብሔራዊ ትልቅ ሃላፊነት በተናጠል የሚወጡት እንዳልሆነ ካለፈው ትግልና ከደረሰው ውድቀት ተመክሮ ገብይተናል፡፡ በግልና ቡድናዊ ጥቅምና የስልጣን ሹክቻ ለአጥፊ ሀይሎች የተመቸ እድልን ከመፍጠር ሌላ የሰጠው ጥቅም እንደሌለ ማንም አይክደውም፡፡ ይህንን የጋራ ድክመት አስወግዶ የአገርን ህልውና ለማስከበር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መተባበር ከሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ አሁን አደጋ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ አንድነትና እንደ አገር የማስቀጠሉን አደራና ሀላፊነት ተቀብለን፣በመጃጃል ለውጥ አለ ብለን ላለው ስርዓት አጃቢና ተለጣፊ ከመሆን ወጥተን ለሕዝቡ የተስፋና አስተማማኝ አማራጭ በመሆን እጅ ለእጅ ተያይዘን የፀረ ኢትዮጵያ የጎሰኞችን የፖለቲካ ሴራ የምናከሽፍበት ህብረት መፍጠር ለነገ የማንለው ግዳጅ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻልን ለሚከሰተው ጥፋት የታሪክ ተጠያቂ እንሆናለን።አሁን አለ የሚባለው ለውጥ መለስተኛ የጥገናና የጎሳ መተካካት ከመሆን ያለፈ አለመሆኑን አምኖ መቀበል ያሻል።
ከሁለት አመት በፊት በአሜሪካ አገር በሲያትል ከተማ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ክፍላተሃገር ህብረት ሁለገብ የሲቪክ ማህበር፣ ክልል የተባለው አንዱን ባለቤት ሌላውን ጭሰኛ ያደረገ፣ በቋንቋና በጎሳ መሰረት ላይ የቆመ የልዩነት ግንብ ፈርሶ በዘመናዊና ዲሞክራሲያዊ ክፍላተ ሀገር አወቃቀር ለተመሰረተ ፌደራሊዝም የድርሻውን ለማበርከት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ድርጅት አሁን አገራችን ኢትዮጵያ ያለችበትን አሳሳቢ ደረጃና የአገር አቀፍ ጅርጅቶችን ተለያይቶ መጓዝ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተበታተነው የአንድነት ሀይል ተቀራርቦ በመነጋገር ወቅቱ የሚጠይቀውን ህብረት መሰርቶ አገራችንን ከተደቀነባት አደጋ ለማዳን ይችላል በሚል ሙሉ እምነት ባለፈው የካቲት 21 ቀን 2011 ዓም በአዲስ አበባ ከሃያ በላይ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱትን የፖለቲካ ድርጅቶችን ሰብስቦ አንድ ብሔራዊ የትብብር መድረክ ፈጥሯል።መድረኩም በውስጡ የተለያዩ የሙያና ማህበረሰብአዊ ማህበራትን ያቀፈ ለማድረግ በመጣር ላይ ይገኛል።የተቀላቀሉም አሉ።ዝርዝሩም በወቅቱ በተለያዩ የዜና ዘርፎች ለሕዝብ ተገልጿል።
ለጥቃት ያጋለጠንን የመለያየት ድክመት አስወግደን፣ ያጣነውን ህብረት መስርተን፣ ለወሳኙ ትግል በጋራ የምንቆምበት፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና አገራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ አስተማማኝ ቁመና የምንፈጥርበት ጊዜ አሁን በመሆኑ በዚህ ብሔራዊ የትብብር መድረክ ውስጥ በመሳተፍ ፣በሃሳብና በገንዘብ በመርዳት እንዲጠናከርና ዓላማው ከግቡ እንዲደርስ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ከሁሉም አገር ወዳድ ይጠበቃል።
ለውጥ አለብለን የምንዘናጋበት ወቅት ላይ አይደለንም፤አሁንም ሕዝብ በጎሳ ማንነቱ ይገደላል፣ይፈናቀላል ሠራተኛው ሠርቶ እንዳይበላ፣ነጋዴው ነግዶ እንዳያድር በልዩ ልዩ ግዳጆች ወከባ ውስጥ ገብቷል።አሁንም እርሃብ፣በሽታ፣ስደትና ግጭት መታወቂያችን ናቸው።አገራዊ መንፈስ በጠባብ ክልለኛነት መንፈስ ተበክሏል።ያገሪቱ ፖለቲካ፣ ኤኮኖሚው፣ የመከላከያና የደህንነቱ ዘርፍ የሚሽከረከረው በጎሳ ስሌት ነው።በጎሳ መብትና ነጻነት ስም የውጭ አገር ቅጥረኞች(ባንዳዎች)የሽብር መረባቸውን እያሰፉ በጠራራ ጸሃይ ሕዝብ እንዲጨርሱ መንግሥት ተብዬውም አይቶ እንዳላዬ ስውር ድጋፉን የሚያደርግላቸው ይመስላል።ታጥቀው ሲንቀሳቀሱና የኛ ነው የሚሉትን ክልል ተቆጣጥረው ለዘመናት በቦታው የኖረውን ሰላማዊ ሕዝብ ስቃዩን ሲያሳዩት፣ሲገሉት፣ሲዘርፉት፣ሲያባርሩት እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥቧል።ከዚያም አልፎ ተርፎ የሁሉም ከተማ የሆነችውን አዲስ አበባን የነጠላ ጎሰኞች ንብረት አድርጎ ልዩ ጥቅም በሚል ሽፋን ኗሪውን ለማፈናቀል የሚጎነጎነው ሴራ ከመንግሥት በኩል ሕጋዊ ሽፋን የተሰጠው መመሪያ ሆኗል።የኗሪውን ስብጥር በሚጻረር መልኩ በከተማዋ የአንድ ጎሳ ቁጥር የበላይነቱን እንዲያገኝ አንዱን አፈናቅሎ ሌላውን የመትከል እርምጃ በገሃድ በመፈጸም ላይ ነው።
መንግሥት የሚከተለውን ወገንተኛ አሰራር የማያቆም፣ ያሸባሪዎቹን አመጽ የማይቆጣጠርና የማይገታ፣ወንጀለኞቹንም ለሕግ የማያቀርብ ከሆነ ጥቃቱን ለመከላከልና የአሸባሪዎቹን ክንድ ለመስበር የጥቃት ሰለባ የሆነው ሕዝብና አገር ወዳዱ ከሚገደድበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።ያ ደግሞ ሁኔታውን ስለሚያባብሰውና ለውጭ ሃይልም ለመግባት ምክንያትና ዕድል ስለሚሆን በወቅቱ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ መፍታቱ ይመረጣል፤ብቸኛው አማራጭም የጎሳን ፖለቲካና የክልል አወቃቀር በሕግ መከልከልና ማሶገድ ነው።የቀውሱ መነሻ የሆነውም “ሕገመንግሥት”ሕዝቡ በተሳተፈበትና በተቀበለው ሕገመንግሥት መለወጥ ይኖርበታል።
የተቋቋመው የብሔራዊ ትብብር መድረኩ ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው
1 ከሁሉም በፊት አደጋ ውስጥ የምትገኘዋን ኢትዮጵያ አገራችንን ተባብረን ህልውናዋንና አንድነቷን ለማስከበር
2 የጋራና ህገመንግሥታዊ ስርዓት እንዲመሰረት አብሮ ለመታገል
3 በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን ሕዝቡ በእኩልነት ተጠቃሚ የሚሆንበትን መርሃ ግብር ወይም ፍኖተ ካርታ ለመንደፍ
4 የጋራ እቅድ በማውጣት በኢትዮጵያዊነት ካስማ ላይ የቆመ ስርዓት ለመመስረት፣በተናጠል የሚደረገውን ትግል ለማቀናጀትና ለማስተሳሰር፣የሕግ የበላይነትና የዲሞክራሲ ስርዓት እንዲሰፍን፣የሰብአዊና የዜጎች መብት እንዲከበር ከሚታገሉ ተመሳሳይ አቋም ካላቸው ከአገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት የተውጣጣ አንድ ብሔራዊ መድረክ(National solidarity Forum)ለመፍጠር
5 የአንድነቱን ጎራ የሚያጠናክርና የሚያስተባብር የጋራ ዓላማ በመንደፍ የጎሳ ፖለቲከኞች ጎራ ብቸኛ ሃይል ሆኖ እንዳይወጣ እስከመጨረሻው ለመታገል
6 ቋንቋና ጎሳ መሰረት ያደረገው የክልል አወቃቀርና አስተዳደር ሕዝብን ከፋፍሎ የሚያጫርስና የሚያፈናቅል፣የአገርን አንድነት የሚያናጋ ስለሆነ ተወግዶ በተሻሻለና ዴሞክራሲያዊ ይዘት ባለው የክፍላተ ሃገር አወቃቀር ቢተካ ለሰላሙ፣ለአብሮነቱና ለአገራዊ እድገቱ ዋስትና እንደሚሰጥ በማመን ተግባራዊ ለማድረግ
7 በየክልሉ በግልጽና በሚስጥር ፣በቡድንና መንግሥታዊ አካል በስፋት የሚካሄደውን የሰው ልጅ በጎሳ ማንነቱ እየተፈረጀ መበደሉንና መፈናቀሉን ፣ሰብአዊ መብቱን መገፈፉን በመቃወም ይህ ሁኔታ ካልተቀዬረ በአፍሪካ ቀንድና በአካባቢው ሊፈጥር የሚችለውን ቀውስና አለመረጋጋት ለዓለም ህብረተሰብ ለማሳወቅና ለማጋለጥ ፣ለተበደሉትም ድጋፍ ለማሰባሰብ፣ድርጊቱን የፈጸሙት ለሕግ እንዲቀርቡ ለማድረግ
8 ሕዝቡ እምነትና ተስፋ ጥሎበት የነበረው የለውጥ ጅማሮ መዋቅራዊ ባለመሆኑና በነበረው ስርዓት ቢሮክራሲ(ማሽነሪ)የሚንቀሳቀስ በመሆኑ አቅጣጫውን የመሳት አዝማሚያ ይታይበታል፤ለመጨናገፍም ያለው ዕድል ከፍተኛ ነው።ያንን አደጋ ተከላከሎ ከጥገና ለውጥና ከጎሳ መተካካት አውጥቶ ወደ መሠረታዊ ለውጥ የሚሸጋገርበትን መንገድ ቀይሶ ሕዝቡ እንዲነቃና እንዲደራጅ የሚረዱ ሥራዎችን ለመሥራት
9 በአገራችን ላይ የሚታዬውን የፖለቲካ፣የኤኮኖሚና የማህበረሰብ ችግሮች ለመፍታት በሚያስችለው ተግባር ላይ ለመሳተፍ
10 የሕዝቡን ስጋትና ጭንቀት፣የኑሮ ውድነት ለማቃለል ከሚጥሩ ሃይሎች ጋር ለመተባበር
እነዚህን ዓላማዎች የሚደግፍና የጎሳን ፖለቲካ የሚቃወም ኢትዮጵያዊ ሁሉ በድርጅትና በግለሰብ የእንቅስቃሴው አካል እንዲሆንና ድጋፉን እንዲያበረክት ጥሪ እናደርጋለን።
ኢትዮጵያ አገራችን በአንድነትና በነጻነት ለዘላለም ትኑር!
የኢትዮጵያ ክፍላተሃገር ህብረ