2019-05-08 Author: ብርሃኑ ሰሙ

ዘመቻና የሕዝቦች አሻራ – በአዲስ አበባ

የዛሬዋ አዲስ አበባ፤ አብርሃና አጽብሀ ግዛታቸውን ለማስፋፋት መጥተው ዱካቸውን ካኖሩባት ጀምሮ፤ ከንጉስ ዳዊት እንቅስቃሴ፣ ከኦሮሞዎች ፍልሰት፣ ከግራኝ አሕመድ ወረራ፣ ከአፄ ልብነ ድንግል ዘመቻ ጋር በተያያዘ በርካቶች በተለያየ ዘመን የተለያየ አሻራቸውን አኑረውባታል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ በመንግስት መቀመጫነት ይታወቁ የነበሩት አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጎንደር ‹‹ስልጣናቸውን›› ለባለተራው ሸዋ በክብር ከሰጡ በኋለ፤ ሁነኛ መቀመጫውን በማፈላለግ እዚህም እዚያም ሲረግጡ የከረሙት የሸዋ መኳንንት፤ የመጨረሻው ማረፊያቸው እንጦጦ ሆነ፡፡

አፄ ምኒልክ የመንግስታቸውን መቀመጫ አዲስ ዓለም ላይ ለማድረግ አቅደው፣ ቤተ መንግስታቸውን ማሳነጽ በጀመሩበት በ1880ዎቹ መጀመሪያ፣ ሐረርን ለማስገበር ወስነው እንቅስቃሴ ሲጀምሩ፣ የመጀመሪያ ማረፊያቸውን በእንጦጦ ተራራ አደረጉ፡፡ ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱንና ጥቂት ተከታዮቻቸውን እዚያው ትተው ወደ ሐረር ተጓዙ፡፡ በድል የተመለሱት አፄ ምኒልክ፣ እቴጌይቱ ‹‹አዲስ አበባ›› ብለው የሰየሙትን ስፍራ ስለወደዱት፣ በአዲስ ዓለም እንዲሆን ተወስኖ የነበረው የመንግስት መቀመጫ ወደ አዲስ አበባ ለማዛወር ሽር ጉዱ ተጀመረ፡፡

በ1879 ዓ.ም አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መንግስት መቀመጫ ዋና ከተማ መሆኗ ሲበሰር፤ ንጉሠ ነገሥቱን ተከትሎ የመጣ ከ60 እስከ 80 ሺህ ሕዝብ በአካባቢው ይኖር ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ የሚበዛው ንጉሠ ነገሥቱን ተከታይና ዘማች ነበር፡፡ ግዛት ከማስፋፋት፣ ከፍልሰት እና አገርና ሕዝብን ከወራሪ ጠላት ከመከላከል ጋር በተያያዘ በርካታ የዘመቻ ታሪኮችን ያስተናገደቸው አዲስ አበባ፤ ባለፉት 123 ዓመታት፤ ወንድማማች ሕዝቦች እርስ በእርስ ያደረጉትን ‹‹ልፊያ›› እና ‹‹ትግል›› ሳይጨምር፤  የአገርና ሕዝብን አንድነትና ሰላም ለማስጠበቅ ሦስት ታላላቅ ዘመቻዎች ሲካሄዱ፤ አዲስ አበባ የታሪክ አሻራው ታትሞባታል፡፡

ቀዳሚው የ1888ቱ የጣሊያን ወረራ ነው፡፡ የወራሪውን ዓላማ ለማክሸፍ ኢትዮጵያዊያንን የጠሩት አፄ ምኒልክ፤ ጥሪያቸውን አክብሮ የተከተላቸው ሕዝብ ስብጥር ሁሉንም ኢትዮጳያዊ የሚወክል ነበር፡፡ ከአድዋ ድል መልስ ንጉሠ ነገስቱን ተከትሎ አዲስ አበባ መጥቶ መኖር የጀመረው ሕዝብ፤ ከአስር ዓመት በፊት በ60 እና 80 ሺህ ይገመት የነበረውን ቁጥር በብዙ እጥፍ ከማሳደጉም በላይ የአዲስ አበባ ከተማን ነዋሪ ስብጥር ‹‹ኢትዮጵያን›› እንዲወክል የሚያስችል ዕድል ፈጠረ፡፡ የቀድሞውን ዘመን ሳይጨምር፤ ከ1879 ዓ.ም በኋላ በአዲስ አበባ ላይ በኢትዮጵያዊያን የታተመው አንዱ፣ ትልቁና ቀዳሚው አሻራ ይህ ነበር፡፡

በአድዋ ድል ሽንፈት ቁጭት የገባው ፋሽስቱ የጣሊያን መንግስት፣ በ1928 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ያደረገው ወረራም በድል ሲጠናቀቅ፣ ለድሉ መፍጠን የአዲስ አበባና የነዋሪዎቿ ሚና ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም 30 ሺህ የከተማው ነዋሪ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወቱን ማጣቱ፤ በየጦር ግንባሩ ፋሽስቱን ይፋለሙ ለነበሩ አርበኞች ቁጭትና እልህ የፈጠረ ክስተት ነበር፡፡ በዚህ የወረራ ዘመን የኢትዮጵያዊያን አርበኝነት ጎልቶ ከመታየቱ ጎን ለጎን ‹‹ባንዳ››ዎችን ቢፈጥርም፤ ከድል በኋላ የንጉሠ ነገሥቱ መንግስት፣ በአገርና ሕዝብ መሐል ክፍተት እንዳይፈጠር፣ ሁሉንም በማቀፍ፣ ልማትና ዕድገት ላይ ትኩረት አድርገው፣ ኢትዮጵያዊያን ለኢኮኖሚ፣ ለትምህርት፣ ለጤና … መሻሻልና መስፋፋት እንዲረባረቡ ማድረጋቸው፤ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የታተመውን የሕዝቦች አሻራ ማሳደጉ፤ ፍቅር፣ ሰላምና መቻቻል የሸገር አንዱ መገለጫ እንዲሆን አስተዋጽኦ አደረገ፡፡

ከ1950ዎቹ አንስቶ ኢትዮጵያን የመውረር ሙከራ ታደርግ የነበረቸው ሶማሊያ፤ በአገራችን በ1967 ዓ.ም የተደረገውን ለውጥ ማዕከል አድርጋ፣ በመቶ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን አልፋ ኢትዮጵያን ለመወረራ ያደረገችውን ጥቃት ለመመከት የተደረገው ጥሪና ምላሽም፤ ለአድዋ ዘመቻ ሲሆን ከታየው ጋር ተመሳሳይ ብቻ ሳይሆን አንድ ዓይነት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከተለያዩ ክፍላተ ሀገራት የሕብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጣው 300 ሺህ የሚሊሺያ ጦር ተሰብስቦ ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ የዘመተው፣ የአንድነትና የሕብረት ስሜት አሻራውን አዲስ አበባ ላይ በማኖር ነበር፡፡

የቀድሞውን ትውልድ ከአሁን፣ የትላንቱን ታሪክ ከዛሬው … ጋር ያያያዙት እነዚህ አሻራዎች እንዳይጠፉ፣ ጎልተው እንዲታዩ በሚገባው መጠን ተሰርቷል ወይ? ቢባል አፍን ሞልቶ ምላሽ መስጠቱ ሳያስቸግር አይቀርም፡፡ በቅርቡ የአድዋ ድል 123ኛ ዓመት በዓል በአዲስ አበባ ሲከበር፣ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ ‹‹ለአድዋ ጀግኖች መታሰቢያ የሚሆናቸው ታላቅ ሥራ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለመሥራት ቃል እንገባለን›› በሚል ከሰጡት የተስፋ ቃል መረዳት የሚቻለው ጉዳዩ ብዙ ትኩረት ሳያገኝ ለዚህ ዘመን መድረሱን ነው፡፡

ለአድዋ ጀግኖች በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን፣ ጦርነቱ የተካሄደባት ትግራይን ጨምሮ በሁሉም ከልልና ከተሞች መታሰቢያ መሠራት አለበት ከሚለው ይልቅ፣ እስካሁን አለመሰራቱ ነው ይበልጥ ሊያነጋግር የሚገባው፡፡ ከላይ በቀረበው ምክንያት የአድዋን ድልና የአድዋ ጀግኖች መዘከሪያ ለመስራት በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ትኩረት ቢሰጠው ተገቢነቱ አጠያያቂ አይሆንም፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በየዓመቱ የአድዋ ድል በዓል የሚከበርበት አራዳ ጊዮርጊስ አደባባይ፣ በ1895 ዓ.ም የአድዋ ድል 7ኛ ዓመት ከተከበረበት አንስቶ አገልግሎት መስጠቱን እስካሁን ቀጥሏል፡፡ በአደባባዩ የሚገኘው የአፄ ምኒልክ ሐውልት ንግስት ዘውዲቱ ለአባታቸው መታሰቢያ እንዲሆን ያሰሩት ነው፡፡

ለአድዋ ድልና ጀግኖች አዲስ አበባ ከተማ ተገቢውን ክብር ሳትሰጥ ለዛሬ ደርሳለች፡፡ በ1960ዎቹ ብሔራዊ ባንክ ፊት ለፊት ያለው አደባባይ በአድዋ ስም ተሰይሞ እንደነበር ‹‹INTERMEDIATE AMHRIC CULTURAL READER ›› በሚል ርዕስ WOLF LESLAU በ1973 እ.ኤ.አ ባሳተሙት የታሪክ ጥናት መድብል አንዱ በሆነውና ስለ አዲስ አበባ ከተማ ታሪክ በወርቁ ደገፉ በተቀነባበረው ጽሑፍ ተገልጻል፡፡ በኋለኛው ዘመን ከአዋሬ ወደ ሲግናል የሚያቋርጠው አደባባይና ድልድይ ለአድዋ ድልና ጀግኖች መዘከሪያነት ቢሰየምም፤ ከስያሜው በዘለለ የታሪኩን ታላቅነት ማሳያ አንዳች ምልክት በአካባቢው የለም፡፡ በአደባባዩ የራሳቸውን ታሪክና ሐውልት ለማቆም የተለያዩ አካላት እየተሻሙበት መሆኑም ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው፡፡

የፋሽስት ጣሊያን ወረራንም በድል ላጠናቀቁት ኢትዮጵያዊያን በአዲስ አበባ ከተማ በ6 ኪሎ እና በ4 ኪሎ መታሰቢያ መቆሙ በአንጻራዊነት ጥሩ ነው ካልተባለ በስተቀር፤ ድሎ የትላንቱን ትውልድ በምን ያህል ጥንካሬ አስተሳስሮ እንደነበር ለአሁኑ ትውልድ ማሳየት የቻለ አይመስልም፡፡ ለየካቲት 12 ሰማእታት በየዓመቱ የመታሰቢያ ስነ ስርዓት ሲፈጸም፣ 6 ኪሎ አደባባ ተጨናንቆ ያውቃል ወይ? ቢባል መልሱ ግልጽ ነው፡፡ የድል በዓል ሚያዝያ 27 ቀን በየዓመቱ በ4 ኪሎ አደባባይ ሲከበርም የኢትዮጵያ ጥንታዊ አርበኞች ማህበር ተሳትፎ ቢቀነስ ውጤቱ ከላይኛው ጋር ተመሳሳይ ነው የሚሆነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን የ1969ኙን የሶማሌ ወረራ በአሸናፊነት ያጠናቀቁበትን ታሪክ ለመግለጽ ‹‹የካራማራ ድል›› ዋነኛው ማሳያ ነው፡፡ ድሉ 40 ዓመታት ቢያስቆጥርም ዓመታዊ የድል በዓል የመሆን ዕድል ቀርቶ የመታሰቢያ ስነ ስርዓት ማከናወኛ መድረክ ተነፍጓል፡፡ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ የሚገኘው ‹‹ትግላችን ሐውልት››፤ በወንድማማቾች ‹‹ልፊያ››፣ ‹‹ትግል›› እና ‹‹ብሽሽቅ›› ምክንያት ክብር ያጣ አደባባይ ከሆነ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ የካራማራን ድል መዘከሪያ ከ‹‹ትግላችን ሐውልት›› መገኛ የሚሻል ስፍራም ሆነ አደባባይ በአዲስ አበባ ከተማ የለም፡፡

ብዙ ኢትዮጵያዊያን ከአዲስ አበባ የተላለፈላቸውን ጥሪ በመስማት፣ አዲስ አበባ ላይ በመሰባሰብና መነሻ በማድረግም፤ ለአገርና ሕዝባቸው አንድነትና ሰላም፤ አጥንትና ደማቸውን ከስክሰው ያኖሩት አሻራ የሚያደበዝዝ ክፍተት በምን ምክንያት ተፈጠረ? ከሚለው ይልቅ ክፍተቱ ምን አስከተለ? የሚለው ጥያቄ ቢነሳ፣ አሁን አዲስ አበባ ከተማን ማዕከል አድርጎ የሚሰማውና የሚታየው ጭቅጭቅ የዚህ ውጤት መሆኑ ግልጽ ስለሆነ፤ የደበዘዘው አሻራ እንዳይጠፋ መጠንቀቅ ተገቢነቱ አጠያያቂ አይሆንም፡፡