2019-04-27 Author: ጥበቡ በለጠ

የአማራ ሕዝብ

ይሄ ርዕስ መቅረቡ ትክክለኛ መልስ ይሰጠዋል ከሚል መንፈስ የቀረበ አይደለም፡፡ ጥያቄው ለዘመናት መልስ ሲሠጠው ቢኖርም የተሟላ መልስ ግን ማግኘት አልተቻለም፡፡ አይቻልም፡፡

በዘመነ ደርግ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ብሔረሰቦች በሙሉ ተጠንተው ማንነታቸውና አንዳንድ መረጃዎቻቸውን እንዲፃፍ አንድ የምሁራን ቡድን ተቋቁሞ ነበር፡፡ ያ ቡድን ዛሬ በሕይወት የሌሉትን ለምሣሌ ዶ/ር እሸቱ ጮሌን፣ ዶ/ር አሰፋ መድንን፣ ዶ/ር ኃይሌ ወ/ሚካኤልን፣ ዶ/ር ክንፈ እርግብ ዘለቀን፣ ዶ/ር ዲበኩሉ ዘለቀን እና ሌሎችንም በርካታ ስመ ጥር ኢትዮጵያዊያንን ያካተተ ነበር፡፡ ቡድኑ ኢትዮጵያን በሙሉ ተዘዋውሮ ብሔረሰቦችዋን አጥንቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ያ የጥናት ውጤት ለሕትመት ሳይበቃ ደርግ ወደቀ፡፡ ደርግ በወደቀ በ25ኛ አመቱ በዚያ የምሁራን ቡድን ውስጥ አባል የነበሩ ዶ/ር ፍስሐ አስፋው ጥናቱ በእጃቸው ስለነበረ በ2008 ዓ.ም ያንን የምሁራን ጥናት አሣተሙት፡፡ ትልቅ የታሪክ እዳ ከላያቸው ላይ አወረዱ፡፡ የዚህ መጽሐፍ ርዕስ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን የሚገለጥ ጥናታዊ መዘክር፣ ብዛት ምንነት ማንነትና አሰፋፈር ይላል ግሩም ርዕስና ጥናት ነው፡፡

ይህ መፅሐፍ ጠቀሜታው በእጅጉ የጐላ ነው፡፡ ምክንያቱም የተዘጋጀበት መንፈስ የፖለቲካ ግር ግር እና ሁካታ ባልበዛበት ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ አዘጋጆቹም በእውቀታቸውም ሆነ በስብጥራቸው በምንም ጫና ያልተነካኩ እና በብሩህ ሕሊና ያዘጋጁት በመሆናቸው ጥናታቸውን ተአማኒ ያደርገዋል፡፡ ይህ መጽሐፍ ከተደበቀበት ወጥቶ እንዲታተም የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉት አቶ ሰለሞን በቀለ እና ዶ/ር ዘካሪያስ አምደ ብርሃኑ ጥሩነህ ላቅ ያለ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ታሪካቸው ከተፃፈላቸው 75 ብሔረሰቦች መካከል አንዱ አማራ ነው፡፡ እንደ መጽሐፉ ገለፃ አማራ በኢትዮጵያ ከሚኖሩ ጥቂት ባለብዙ ብሔረሰቦች አንዱ ነው ብሎ ይጀምራል፡፡

ዛሬ አማራ የሰፈረበት አካባቢ ሰሜን ሸዋን ከጥቂት ምስራቃዊ ወረዳዎች በቀር መላ ወሎን ከምዕራብ ጠረፎች በቀር ጐጃምንና ጐንደር በሙሉ ይሸፍናል፡፡ ብሔረሰቡ በደቡብ ኦሮሞና፣ በምስራቅ አፋርን፣ በሰሜን ምስራቅ ትግራይ ትግሪኝና አገውን፣ በሰሜን ምዕራብ ጉምዝና አገውን፣ በደቡብ ምዕራብ ሽናሻና የጉምዝ ብሔረሰብን ይጐራበታል ይላል ሰነዱ፡፡

የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም አማራ

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ሲከራከሩ ስለ አማራ የሚከተለውን አሉ፡-
“ይሔ አማራ የሚባለው ነገር መነገር እና መነጋገር ያለብን ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ውክልና ለውክልና አስቸጋሪ ነው፡፡ የሌለ ነገር መወከል አይቻልም፡፡ የለም አማራ የሚባል ነገር፡፡ እኔ እንደማውቀው፣ ጐጃሜ አለ፤ ጐጃሜጋም ስንሔድ ዳሞቴ አለ፤ ዋናው Proper ጐጃም አባይን ሲሻገሩ ያለው ጐጃሜ አለ፤ ጐንደሬ አለ፤ ስሜን አርማጭሆ፣ ወልቃይት ጠገዴ አለ፡፡ ሸዋም እንኳን ትንሿጋ ስንመጣ፣ ጣራ፣ መንዝ፣ ቡልጋ፣ ተጉለት፣ ምንጃር ምናምን ተብሎ ይበጣጠሣል፡፡ ወሎም ስንገባ እንደዚያው ነው፡፡ ሰው Identify የሚያደርገው ያልመጣ ነገር ኢትዮጵያዊ የሆነ ይሄ በትግራይም ቢሆን ያው፣ ኤርትራም ቢሆን ያው፣ ያልመጣ እና በእውነት ውክልና የሚያስፈልገው ነገር ነው፡፡ እዚህ ሀገር ከኢትዮጵያ መሠረት ከተነሣን፣ በኢትዮጵያ መሠረት መነሣት ብንፈልግ ኖሮ አገሩ የሚባለው ነገር ነው፡፡ አገርህ የት ነው ተብሎ ሲጠየቅ፣ አገሬ አማራ ነው የሚል ሰው የለም፡፡ መንዜ ነው? ከመንዜም እንኳን ይከፋፍላታል፡፡ ይህች እንኳን ትንሿ መርሃቤቴ ወይ ታች ቤት፣ ወይ ላይ ቤት እያለ ይከፋፍላታል፡፡ ሰው ራሱን ማንነቱን የሚገልፀው በመሬቱ ነው፡፡ ባካባቢው ነው፡፡ አብዛኛው የደጋው ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ በዚያ ነው የሚጠቀመው፡፡ በተለይ በሰሜኑ ክፍል ያለው እና አማራ የሚባል ነገር፣ አማራን እወክላለሁ ብሎ አንድ ሰው እዚያ ኮንፍረንስ ላይ ቢኖር ኖሮ እኔ የምለው ያ ሰውዬ ወይ አብዷል ወይ ችግር ያለበት ሰውዬ መስሎ ነው የሚታየኝ ፡፡ በምንም አይነት መንገድ የሌለን ነገር አንድ ሰው መወከል አይቻልም፤ የለም!

እኔ ለምሣሌ በማደርገው ጥናት ሁሉ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ገበሬዎችን አነጋግሬያለሁ፡፡ እና ይሔንን ጥያቄ ጠይቄያቸዋለሁ፡፡ አማራ ነህ ወይ? እላቸዋለሁ፡፡
አይደለሁም! ይለኛል፡፡
ምንድነህ ታዲያ?
እስላም ነኝ፡፡
ቋንቋህ ምንድን ነው?
“አማርኛ”

በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ገበሬዎች ናቸው እነዚህ፡፡ ባሌም ብንሔድ ያው ነው፡፡ አርሲም ብንሔድ ያው ነው፡፡ አማራ ለብዙ ሰው እንደ ክርስቲያን ማለት እንጂ የዘር፣ ያንድ ሕብረተሰብ፣ ያንድ መኖርያው የተወሰነ የኢትዮጵያዊያን ክፍል ሆኖ የሚገምት የለም፡፡

ምሣሌ ጥራ ብባል እንደዚህ አይነት ነገር እኔ የማውቀው አንድ ብቻ ነው፡፡ በጣልያን ጊዜ በአምስቱ አመት ጣልያን ኢትዮጵያን ሲከፋፍል በጌምድርን፣ ወሎን፣ ጐጃምን፣ ሰሜን ሸዋን አንድ ላይ አደረገና አማራ አለው፡፡ ያ ብቻ ነው፡፡ እንጂ እነዚያ ሰዎች ራሳቸው እዚህ ውስጥ ያሉት ሰዎች እኛ አማሮች ነን፤ የአማራ ስሜት፣ የአማራነት ስሜት አለኝ የሚል የለም፡፡ እንደምታውቁት በአክሡም፣ በአድዋ ያለ ሕዝብ፣ ከቤጌምድር ጋር የበለጠ ግንኙነት አለው፡፡ በጌምድር ካለው አማርኛ ተናጋሪና ሸዋ፣ በጋብቻ እንኳን ቢሆን ጐንደሬ ወደዚያ ከትግሬ ጋራ ሊጋባ ይመርጣል፤ ከሸዋ ጋራ ትንሽ ቅር ይለዋል፡፡ ይቀፈዋል፡፡
በብዙ አይነት ነገር ስንመለከተው በእውነት የሌለ ነገር ነው፡፡ እዚህ አገር አሁንም የለም፡፡ አለመኖሩ ደግሞ ለኔ ጥሩ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ጥሩ ነው ባይ ነኝ፡፡ አሜሪካን አገር እየተፈጠረ ነው፡፡ ይሔው አማራ የሚባል ነገር አሜሪካን አገር እየተፈጠረ ነው፡፡ ያ እንደማይጋባብን ተስፋ አለኝ፡፡”

የመለስ ዜናዊ አማራ

የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ፣ ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የአማራነት ገለጻ ምላሽ ሰጡ፡-
“ በመጀመሪያ ደረጃ ይሄ አማራ የሚባል ሕዝብ አለ ወይስ የለም የሚባለው ነገር ላይ ፕሮፌሰር መስፍን አሁን የያዙት አቅጣጫ ለአማራ ብቻ የሚሰራ ሣይሆን ለሁሉም ብሔረሰቦች የሚሠራ ነው፡፡ በዚህ ከተኬደ ኦሮሞ የሚባል ሕዝብም የለም፡፡ በዚህ ከተኬደ ትግራይም የሚባል ሕዝብ የለም፡፡ አንዱ ሽሬ ነኝ ይላል፤ አንዱ አድዋ ነኝ ይላል፣ አንዱ እንደርታ ነኝ ይላል፡፡ ነገር ግን ከዚህ በላይ ደግሞ አንድ ትግራይን ትግራይ የሚያደርግ አስተሳሰብ (Concept) አለ፡፡ ቋንቋ አለ፤ ባሕል አለ፡፡ ስነ አእምሮ አለ፡፡ እነኚህን ግምት ውስጥ በማስገባት ግን ከባቢያዊ ልዩቶች እንዳሉ ሆነው፤ አካባቢያዊ (Reginal) የሆኑ ልዩነቶች እንዳሉ የታወቀ ነገር ሆኖ፣ ግን በዚህ ክልልም ቢሆን አንድ ትግራይ የሚባል ነገር አለ፤ አንድ ኦሮሞ የሚባል ነገር አለ፤ አንድ አማራ የሚባል ነገር አለ፡፡ ይሄን ስል ጐንደሬው፤ ጐጃሜውና ሸዋው ከታሪክም ጋር የተያያዘ ነገር አለ፡፡ ቅድም ፕሮፌሰር ያመጡት ሃሣብ አለ፤ ምናልባት ወደ ትግራይ ክልል ያለው ጐንደሬ ባብዛኛው ከትግራይ ጋር በይበልጥ ይጋባ ይሆናል ከሸዋ ይልቅ፡፡ ሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን አማራ የሚባል ሕዝብ አለ፡፡ የአማርኛ ቋንቋ አለ፡፡

የወሎ ያነሱት ነገር ለየት ያለ ነው፡፡ አማራ እና እስላም የሚባል ነገር አለ፡፡ ወሎ ውስጥ እሱ የሚመስለኝ ከሰዎቹ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እስላም ነኝ የሚለው ቀደም ሲል ኦሮሞ የነበረው ነው፡፡ እና በሂደት ቋንቋ ምናምኑን እያጠፋና የሌላ ቋንቋ እየወሰደ የመጣው ሴክተር አሁን እስላምና አማራ ብሎ ይለያል፡፡ ኦርጂናሊ ግን እነዚያ ሰዎች በፊት ኦሮሞ የነበሩ ናቸው፡፡ የጁ ወዘት ወዘት አካባቢ፡፡ በተረፈ ግን ጐንደር አሁን ለምሳሌ እስላምና አማራ ብሎ አይለይም፡፡ ወሎ ብቻ ነው ይሄ ነገር ያለው፡፡ ጐጃምም እስላምና አማራ ብሎ የሚለይ ነገር አላየሁም፡፡ ሰሜን ሸዋም እንደዚህ አይነት ነገር የለም፡፡ በርግጥ መንዝ መንዜ ነኝ ነው የሚለው፡፡ ምናልባት መንዝም ቅድም ባስቀመጡት ሁኔታ ይለያይ ይሆናል፡፡ ግን ይሔ የትም ቦታ ያለ ነው፡፡ በሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች አካባቢ ያለ ነገር ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን አንድ ሕዝብ እንደ አንድ ሕዝብ ካታጐራይዝድ አድርገን ለማየት የሚያስችለን ነገር ያለ ይመስለኛል፤ እናም የሄኛውም ለአማራ ይሰራል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ይሔ ውጭ ሃገር ተጀምሯል ያሉት እንዳይጋባብን የሚሉት እንዳይጋባብን እኔም እፈራለሁ፡፡ ምክንያቱም አማራ ስላለ ሣይሆን፣ የአማራ ሕዝብ መብት ጥቅም መጠበቅ አለበት በማለቱ ሣይሆን የሌሎችን ብሔሮች መብት በሚጋፋ መልኩ ስለሚያየው ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ መብትና ጥቅም ከሌላው ሕዝብ ጋር ተፃራሪ አይደለም፡፡ የእኛም እምነት ይሔ ነው፡፡ እነኛ እንዳይጋባብን የምንፈራው አስተያየት ግን ተፃራሪ ነገሮች አድርጎ ያስቀምጣቸዋል፡፡ ተፃራሪ ግን አይደሉም፡፡ የጭቁን ብሔሮችና ብሔረሰቦች መብት ማስከበር ማለት የአማራውን መብትና ጥቅም መጉዳት ማለት አይደለም፡፡ በኛ እምነት በብሔራዊ ጭቆና ተጠቃሚ የሆነ የአማራ ብሔረሰብ የለም፡፡ በኛ አምነት ስል ደግሞ ተጨባጭ ያልሆነ Abstractive አይደለም፡፡ በተግባር እናውቀዋለን፡፡ ሰሜን ሸዋን በተግባር እናውቀዋለን፡፡ ጐጃምን በተግባር እናውቀዋለን፤ ጐንደርን በተግባር እናውቀዋለን፡፡ እዚያ ያለው አርሶ አደር ምን አይነት ሁኔታ ላይ እንዳለ እናውቃለን፡፡ ተጠቃሚ አይደለም፡፡ ከነበረው ሁኔታ ተጠቃሚ የነበረ ክፍል ካለ በጣም ጥቂት ነው፡፡ ሕዝቡን አይወክልም፡፡ ስለዚህ እነኚህን ነገሮች ተፃራሪ አድርጎ የሚያስቀምጠው አመለካከት እንዳይጋባብን በጣም በጣም መጠንቀቅ ያለብን ሆኖ፡- ነገር ግን አማራ የሚባል ሕዝብ፣ ባሕል አለ፤ ቋንቋ አለ፤ ታሪክ አለ፡፡ በርግጥ የአማራ ታሪክ ከትግራይ ጋር ለያይቶ ማየት በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ከአገው ታሪክ ጋር ለያይቶ ማየት በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እንደ ሕዝብ እንደ ኦሮሞ፣ እንደ ጉራጌ እንደ ሌላውም ሁሉ አንድ ሕዝብ አለ ብለን ነው እኛ የምናምነው እንደ ኢሕአዲግ፡፡

በተረፈ ኢትዮጵያ Nationalism ነው ወይም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ስሜት አልተንፀባረቀም የሚለው ምናልባት ከኤርሚያስ (አወያዩ) ጋር የምንለያየበት አንደኛው ነገር ይሄ ሣይሆን አይቀርም፡፡ እኔ የኢትዮጵያ ስሜት፣ የኢትየጵያዊነት ስሜት፣ ኢትዮጵያ ከብሔሮቿ እና ከብሔረሰቦቿ ውጪ የለችም፡፡ እና ኢትዮጵያዊነት ማለት ለኔ የሁሉም ብሔሮች መብትና ጥቅም የሚጠበቅበት ሁኔታ መፍጠር ማለት ነው፡፡ ከብሔሮችና ከብሔረሰቦች ውጭ የሆነ Supra የሆነ ነገር ማስቀመጥ አይደለም፡፡ እነኝህን ሁሉ የሚያስተሣስርና፣ የነኝህን መብትና ጥቅም ሁሉ የሚጠብቅ ሀሣብ ማምጣት ማለት ነው፡፡ እና በዚህ መልኩ ስናየው ለምሣሌ ከንባታው ተበድሏል ማለት ኢትየጵያዊነትን መጉዳት አይደለም፡፡ በእውነት ተበድሏል፡፡ አንድ ላይ ለመሆን ከፈለግን ይህን በደል እናስወግደውና አንድ እንሁን፡፡ ጠቅላላ ኮንፈረንሱ የነበረው ስሜት ግን ይሔ ነው፡፡ እንበታተን አልነበረም፡፡ የነበረውን በደል እናስወግደውና አንድ ላይ ትልቅ ሀገር እንፍጠር፡፡ ከዚህ በላይ ኢትዮጵያዊነት ያለ መስሎ እይታየኝም፡፡

እና ኢትዮጵያዊነትን ወክሎ የቀረበ ድርጅት የለም ማለት ብቻ ሣይሆን በኔ እምነት ኮንፍረንሱ ራሱ ኢትዮጵያዊነትን ነበር ከያንዳንዱ ተወካይ ያንፀባርቅ የነበረው፡፡ ከዚህ በተረፈ አማራው አልተወከለም የሚባለው አባባል በሁለት ምክንያቶች በኛ በኩል ትክክለኛ ነው ብለን አናምንም፡፡ አመለካከቶች ናቸው የተወከሉት፡፡ አመለካከቶችን በርግጥ ከሰው ሙሉ በሙሉ መነጠል አይቻልም፡፡ እነኛን አመለካከቶች ይዞ የሚራመደው ሰው ነው፡፡ ስለዚህ የከንባታው አመለካከት ምንድን ነው ብሎ በድምፅ ብልጫ ማረጋገጥ እስካልተቻለ ድረስ የተደራጀ አካል ካለ ማምጣት ነው፡፡ እሱን የከንባታን አመለካከት አውቃለሁ፣ እሱን እወክላለሁ ያለውን እሱን እንዲወክል ማድረግ ነው፡፡ በዚህ መልኩ አማራን Specifically እወክላለሁ ብሎ የመጣ ድርጅት የለም፡፡ ነገር ግን አንደኛ በአመለካከት ደረጃ የጭቁኑን ለምሣሌ የአርሶ አደሩን አካባቢ የወሰድክ እንደሆነ አንድ አይነት የአማራ አመለካከት የለም ያልከው እኔ በጣም ትክክለኛ የሆነ አባባል ነው የሚመስለኝ፡፡ የአርሶ አደር በትግሉ ሂደት ያየውና ያንቀሣቀሰው ድርጅት ማነው ብንል ኢሕአዴግ ነው፡፡ በአባል ድርጅቶቹ አማካይነት ሰሜን ሸዋን ብዙ ጊዜ ፣ወሎን ለብዙ ጊዜ፣ጐጃምን ደግሞ በቅርቡ፣ገጠሮችን በሙሉ እየተቆጣጠረና እያጠራና እያንቀሣቀሰ ያለው ግን በትግልም አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ይሄ ዝም ብሎ አካባቢን መቆጣጠር ብቻ አልነበረም፡፡ የኢሕአዴግ ሠራዊት በቁጥሩ የጐጃም ሕዝብ አንድ መቶኛም አይሆንም፡፡ እና የሕዝቡ ድጋፍ ከሌለው በስተቀር ያን አካባቢ በፍፁም ሊቆጣጠር አይችልም፡፡ ፕሮፌሰር በዚህ ውይይት ላይ ሣይሆን ከዚህ በፊትም በደርግም ጊዜ የተወሠነ ምልክት ሠጥተዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ በሚመለከት እና ይሔ ያለ ነገር ነው፡፡

ሁለተኛ ይሄ ከፍተኛውን ክፍል ይወክላሉ ብለን ያሠብናቸው ክፍሎች ገብተዋል፡፡ ይሔ እንግዲህ በአመለካከት ነው፡፡ ምናልባት Necessarly በብሔራዊ ተዋፅኦዎቸው አማሮች ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የጭቁን ብሔሮች መብት ማስከበርና የአማራው ሕዝብ መብት ማስከበር፣የጭቁን ብሔሮች መብት ማስከበርና የኢትዮጵያን በአጠቃላይ ጥቅም መጠበቅ፡፡ እነኚህ ነገሮች ተፃራሪ መስለው የሚታያቸው ሀይሎች በኛ አጠራር ትምክተኛ ምናምን የምንላቸው ሀይሎች እንዲገቡ አድርገናል፡፡

ቅድምም አንስቸዋለሁ፣ የዩኒቨርሲቲን ጉዳይ በምናነሣበት ጊዜ ሌሎችንም ድርጅቶች እንግዲህ ግምገማ ላይ ልንሣሣት እንችላለን፡፡ ምናልባት እንደዚህ አይነት አመለካከት አላቸው ብለን ያሰብናቸው የተለየ አመለካከት ይዘው ሊቀርቡ ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ኮንፈረንሱ ላይ እንዳየነው ብዙም የተሣሣትን አይመስለንም ግምታችን ላይ፤ ስለዚህ በኛ እምነት በአማራው አካባቢ አሉ የሚባሉት አመለካከቶች የተለያዩ አመለካከቶች ናቸው እነሱ ሁሉ ተወክለዋል፡፡ ልክ ለምሣሌ የኦሮሞ የተለያዩ ድርጅቶች ተወክለዋል፡፡ በኦሮሞ ውስጥ ያሉ የተለያዩ አመለካከቶች ከሚል አኳያ ነው ያየነው፡፡ እና በዚህ መልኩ የአማራውም ታይቷል የሚል እምነት ነው ያለኝ፤ ምንም እንኳ ድርጅት ነኝ ብሎ ተወክሎ የቀረበ ባይኖርም፡፡ አንዳንዶቹ ምናልባት ይቺ አማራ የምትባለዋ እየተጠላች ነው፤ ለምን እንደሆነ እኔ አይገባኝም፡፡ ልክ እንደ ኦሮሞ፣ እንደ ትግራይ ተራ ስም ነው፡፡ የአንድ ሕዝብ ስም ነው፤ የሚያሣፍርበት ምክንያት የለም፡፡ አንዳንዶቹ የመሐል አገር ሰው ነኝ ይላሉ፤ እና መሐል ሐገር ማለት በጆኦግራፊ ነው? አማራ ነኝ ማለት ምን ችግር ነው ?

የመንግስቱ ኃ/ማርያም አማራ

በዘመነ ደርግ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት የነበሩት ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም በስልጣናቸው የመጨረሻው አመት አካባቢ ስለ አማራ የሚከተለውን ንግግር አድርገው ነበር፡-

ለመሆኑ አማራ ማለት ምን ማለት ነው? ይሔስ ስያሜና ቃል መቼ የመጣ እና ወይም የተገኘ ነው? በጣም ራቅ ባለው በጥንት ጊዜ እስራኤላውያን ኢትዮጵያን ሊጐበኙ ይመጣሉ፡፡ ያገራችንን በደን እና በዱር አራዊት ያሸበረቁ የተራራ እና የኮረብታ ሠንሠለቶች፣ በእነኚህ መካከል ያሉትን ቁጥራቸው የበዛ ወንዞችና ሸለቆዎች፣ ባጠቃላይ የኢትዮጵያ መልክአምድር ገፅታ እና የሕዝቡን ባህልና አኗኗር፣ እነሱ ከሚኖሩበት ማዕከላዊ ምስራቅ መልካኣ ምድር አቀማመጥና እና ሕዝብ ጋር በማነፃፀር በጣም ይደነቃሉ፡፡ ይመሰጣሉ፡፡ እነዚህ ጐብኚዎች ከብዙ ቆይታ በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የአማራን አገር አየን፣ ወይም “በአማራ አገር ጉዞ” የሚል ፅሁፍ አውጥተው ኢትዮጵያን ከሕዝባቸው ጋር ያስተዋውቃሉ፡፡

በእብራይስጥ ወይም በሂብሩ ቋንቋ “አማ” ማለት ሕዝብ ማለት፣ “ሐራ” ማለት ተራራ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሰረት እስራኤሎቹ ሊገልፁ ወይም ሊሉ የፈለጉት በተራራ ላይ የሚኖር ሕዝብ ማለታቸው ነው፡፡ ስለሆነም “አምሐራ” አሉ፡፡
ይህ ቋንቋ እና ስያሜ ከዚህ በፊት በሀገራችን አይታወቅም፡፡ በዚህ የሚጠራ ብሔረሰብ የለም፡፡ በኢትዮጵያዊያን ትርጉምና አነጋገር አማራ ማለት ደገኛ ማለት ነው፡፡ ታዲያ ይህ ከሆነ አማራው ወይም ደገኛው ደጋማው ኤርትራ ነው? ጐንደሬው ነው? ጐጃሜው ነው? ወሎዬው ነው? ኦሮሞው ነው? ጉራጌው ነው? ከፋው ነው? ጊምራው ነው? ጋሞ ነው? ሀዲያው ነው? ወላይታው ነው? ከንባታው ነው? አርጐባው ነው? ወዘተ ተረፈ ማን ነው?

ታዲያ አማራ ማለት ምንድን ነው?

የኢትዮጵያ የቋንቋ ሊቁ ደስታ ተክለወልድ ዐማራ ለሚለው ቃል በመዝገበ ቃላቸው ትርጉም ሠጥተውታል፡፡ እንደ እርሣቸው ገለፃ ዐማራ ለሚለው ቃል የሚከተሉትን ገለፃዎች ሠጥተዋል፡፡
ዐማሐራ፤ /ዐም’ሐራ/፤ ዐም ሕዝብ፤ ሐራ ነፃ፡፡ በተገናኘ’ ነፃ ሕዝብ’ ተገዥነት የማይስማማው ማለት ነው ይላሉ፡፡ ይቀጥሉና ደግሞ፡-
ዐማራነት፤ ዐማራ መሆን’ተገዝሮ /ተገርዞ/፣ ተጠምቆ፣ ማተብ አስሮ፡፡ ይላሉ ደስታ፡፡ ይቀጥሉና፡-ዐማራ ሣይንት፤ የሣይንት ዐማራ፣ ሣይንት ባለቤት ዐማራ ኹኖ ቢተረጐም ግን ያማራ አገር ሣይንት ማለት ነው፡፡ ይኸውም ዐማርኛ የሚናገሩ ሰዎች በመጀመሪያ በሣይንት እንደ ነበሩ ያስረዳል፡፡ በማለትም ደስታ ተክለወልድ ይተረጉማሉ፡፡ ቀጥለውም እንዲሀ አሉ፡-

ዐማሮች፤ ሺዎች/ሸዋዎች/፣ ላስታዎች፣ በጌምድሮች፣ ጐዣሞች/ጐጃሞች/ ወሎዎች፣ እንደሆኑ ፀሐፊው ይገልፃሉ፡፡ እንደገና እንዲህ ይላሉ፡-

ዐማርኛ፤ ያማራ ቋንቋ፣ ከግዕዝ የሚወለድ፤ ከሱርስትና፣ ከዕብራይስጥ፣ ከዐረብ የሚዛመድ ሴማዊ ልሳን፡፡
ዐማርኛ፤ ተዛዋሪ፣ ምስጢራዊ ነገር መልካምና ክፉ ባንድ ጊዜ የሚያናግር ኀብር ቃል፡፡ /ማስረጃ/፤ አትሙት፤ በክፉ አታንሱት፤ /ኢትሙት/፤ ሞት አይንካህ፡፡ አትሙት፤ /ኢትሕምይዋ/፤ ስሙን በክፉ አታንሱት፤ አታጥፉት፡፡ ዐትሙት፤ /ኀትምዋ/፤ደብዳቤውን ማተም

ዐማሬ፤ የዐማራ ተወላጅ፣ የዐማራ ዘር፡፡ የሣይንትም አባት ዐማሬ ይባል ነበር ይላሉ፡፡
ዐምሐራ፤ /ዐም ሐራ/፤ ዐማራ፤ ጨዋ ሕዝብ፤ ነፃነት ያለው፤ በነፃ፤ ግዑዝ አግዓዚ፡፡
ዐምሐራይ፡ዊ፤ ያማራ ወገን፤ ልሣን ቋንቋ፤ ዐማርኛ፤ ከዐረብና ከዕብራይስጥ ከግእዝ ከአራም የወጣ፡፡

በማለት ሰፊ ትርጉም ይሠጣሉ፡፡ ይህ የደስታ ተክለወልድ መዝገበ ቃላት ፍቺ ነው፡፡ እንደ እርሣቸው አባባል ዐማራ የተሠኘው ሕዝብ በሸዋ’ በወሎ’ በጐጃምና በጐንደር የሚኖረው ነው፡፡ በዚያ ላይ የተገረዘና የተጠመቀ ሕዝብ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ይህ ማለት ክርስቲያን የሆነውን የማሕበረሰብ ክፍል ነው አማራ የሚሉት፡፡ Related news