ሁሌ እናስታውሳቸው
ተቀብሮ እንዳይቀር
አኩሪ ታሪካቸው!!!!!!!

ይስሀቅ ደብረጽዮን ማን ነው??.

Image may contain: one or more people

ይስሀቅ ደብረጽዮን የተወለደው በአዲስ አበባ ከተማ መርካቶ ከሚባለው ሰፈር ነው። ይስሀቅ አዲስ አበባ በሚገኙት የመድሐኒ ዓለም ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ትምህርቱን በኮተቤ በሚገኘው በዚያን ቀ.ኃ.ሥ ተብሎ በሚጠራው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ፤ ቀ.ኃ.ሥ ወይም በአሁኑ ስሙ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብቶ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። ይስሀቅ ዩኒቨርስቲ በነበረበት ወቅት በዘመኑ በተማሪዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ግምባር ቀደም ተሳታፊ ነበር። የተማሪዎችን አድማና እንቅስቃሴ ለማስተባበር በተቋቋሙ በአብዛኞቹ ኮሚቴዎች ውስጥ ተሳትፏል፤ በወቅቱ በተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች፤ አድማዎች ወዘተ… በግምባር ቀደምትነት ተሳትፏል፤ የተለያዩ ተልኮዎችን በመውሰድ ተግባራዊ አድርጓል። ይስሀቅ በተደጋጋሚ በፖሊስ ተይዞ ታስሯል፤ ተመርምሯል።

በ1963 ዓ.ም. ከዩኒቨርስቲ ከተመረቀ በኋላ ሥራ አግኝቶ የሄደው በደቡብ ኢትዮጵያ ዋዱ (ወላይታ አግሪከልቸራል ዲቬሎፕመንት ዩኒት) በሚባለው ተቋም ነበር። ፓርቲው በ1964 ከተመሰረተ በኋላ በአገር ውስጥ የአደራጅነት ተልእኮ ከተሰጣቸው መካከል ይስሀቅ አንዱ ስለነበር በወላይታ አካባቢ አባላትን በመመልመልና በማደራጀት የማይናቅ ድርጅታዊ ሥራ ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላም አዲስ አበባ ወደ ሚገኘው የቴሌኮሙኒኬሽን ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት ውስጥ ሥራ አግኝቶ የተዛወረ ሲሆን በዚህም የማደራጀት ተግባሩን ቀጥሎበታል። ቴሌኮሙኒኬሽን አካባቢ የሠራተኛ ማህበሩን በማጠናከር ሆነ የፓርቲ አባላትን በመመልመልና በማደራጀት በኩል ከፍተኛ አስተዋጾ ካደረጉት መካከል ይስሀቅ አንደኛው ነው። በ1969 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ በነበረው የሠራተኞች አድማ ይስሀቅ በአደራጅነት በመጠርጠሩ የደርግ የጸጥታ ኃይሎች ከሚፈልጓቸው መካከል አንዱ ነበር። በዚያን ወቅት በተገኙበት ተይዘው እንዲገደሉ ፎቶግራፋቸው በየቦታው ከተሰራጨው ታጋዮች መካከል ይስሀቅ አንዱ ነበር። ይስሀቅ ከደርግ አፋኞች አምልጦ ለስድስት ወራት ያህል በአዲስ አበባ በሚስጥራዊ ቦታ ድርጅታዊ ሥራ ሲሰራ ቆይቶ በመጋቢት 69 ዓ.ም. ትግራይ ውስጥ ሲንቀሳቀስ የነበረውን የኢ.ሕ.አ.ሠ አካል ተቀላቅሏል። ይስሀቅ በሠራዊቱ ውስጥ የብዙሃን ድርጅት አመራር፣ የኃይል ኮሚሳርና እንዲሁም የሪጅናል የሠራዊት የፓርቲ ኮሚቴ አባል ሆኖ ያገለለገለ ሲሆን በ1976 ዓ.ም. በተደረገው የፓርቲ ጉባዔ የኢሕአፓ የአመራር አባል ሆኖ ተመርጧል።

ይስሀቅ የኢሕአፓ ከፍተኛ የአመራር ኮሚቴ አባል ሆኖ ከተመረጠ ጀምሮ በወያኔ እጅ እስከወደቀበት ድረስ ሠራዊቱ ነጻ ባወጣቸው አካባቢዎች ወሳኝ አመራር በመስጠትና በትግሉ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን ድርጅቱን አገልግሏል። ይስሀቅ ገና ከለጋው ዕድሜ ጀምሮ የአገር እና የወገን ፍቅር ያቃጠለው፤ ለአገሩና ለወገኑ ለሕዝቡ ኑሮውን ምቾቱን እንዲሁም ህይወቱን መሰዋእት ያደረገ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጅ ነው። ምንም እንኳ በሁለቱም በኩል ከኤርትራ ከመጡ ወላጆች ቢወለድም ይስሀቅ የዘርንም ሆነ የቋንቋ ልዩነትን በጽኑ የሚኮንን፤ ለአገርና ለሕዝብ አንድነት የታገለ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ነበር። ይስሀቅ የወያኔ አገዛዝ ወደ ስልጣን ሲመጣ በአደጋ ይዞ በቁጥጥር ስር ካደረጋቸው ከኢሕአፓ አመራር አባላትና እንዲሁም ከሌሎች ነባር አባላት መካከል አንዱ ሲሆን እስካሁን ድረስ መዳረሻቸው ሳይታወቅ ቆይቷል። ይስሀቅንና አብረው የታሰሩ ጓዶቹን ወያኔ በአሰቃቂ ሁኔታ እንደገደላቸው አንዳንድ ክፍሎች ይፋ ቢያደርጉም እስካሁን ከወያኔ ባለስልጣኖች በኩል የተሰጠ መረጃ የለም። በይስሀቅና በጓዶቹ ላይ ግፍ የፈጸሙ ወንጀለኞች ለፍርድ እስኪቀርቡ ድረስ ትግላችን ይቀጥላል።

ይስሀቅ ደብረጽዮን በአሁኑ ሰአት ከወያኔ ጋር እየተዋደቀ ላለው ወጣት ትውልድ አርአያና ምሳሌ ነው። በጣም እንኮራበታለን!!!!!

የተለያዩ የህዝብ ልጆችና ሰማዕታት አጭር ታሪክ (BIO)ይቀጥላል !!!