
አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በ26 የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ ክስ መመስረቱን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ማክሰኞ ዕለት ማስታወቁ አይዘነጋም።
በቁጥጥር ሥር ያልዋሉት በከፍተኛ የሙስና እና ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም በሚሉ ወንጀሎች ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ጌታቸው፤ በትግራይ ክልል እንደሚገኙ ጠቅላይ ሚንስትሩ እና የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ቀደም ሲል በተለያየ ጊዜ ጠቁመዋል።
ታዲያ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አሰፋ በትግራይ ክልል እንዳሉ እየታወቀ ለምን ”በሌሉበት” የሚል ክስ ተመሰረተባቸው የሚለው በርካቶችን አነጋግሯል። እኛም በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የሕግ ባለሙያው አቶ ዮሃንስ ወ/ገብርኤልን ጠይቀናል። አቶ ዮሃንስ የደርግ ከፍተኛ አመራሮችን ለመክሰስ ተቋቁሞ በነበረው ልዩ አቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት እንዲሁም በሥነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በዋና ዓቃቤ ሕግ ከዚያም በቀድሞው የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን የሕግ ክፍል ሃላፊ ነበሩ።
”በሌሉበት”
አቶ ዮሃንስ ”አንድ ተጠርጣሪ ሃገር ውስጥ ሳለ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሕግ አስከባሪ አካል እንዲያዝ እና እንዲቀርብ ታዞ ሳይቀርብ ቢቀር እንኳ ተጠርጣሪው በሌለበት ጉዳዩ በፍርድ ቤት መታየቱ አይቀርም” በማለት ያስረዳሉ።
አንድ ተከሳሽ በሌለበት በፍርድ ቤት ውሳኔ ከተላለፈበት፤ ፍርደኛው ለፍርድ ቤቱ በሌለሁበት ጉዳዩ መታየቱ አግባብ አይደለም ብሎ ሊያመለክት ይችላል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ተከሳሹ ሆነ ብሎ አልያም መጥሪያው ሳይደርሰው ቀርቶም ከሆነ ፍርድ ቤት የሚያጣራው ጉዳይ ይሆናል። ተከሳሹ ሆነ ብሎ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ከቀረ የተላለፈበትን ውሳኔ የመከላከል እድሉን እንዳልተጠቀመ ተደርጎ ይወሰዳል። ይሁን እንጂ ተከሳሹ መከሰሱን ሳያውቅ ውሳኔ እንደተላለፈበት ፍርድ ቤቱ ካመነ፤ ተከሳሹ ማስረጃውን እና መከላከያውን ሊያቀርብ የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ የሕግ ባለሙያው አቶ ዮሃንስ ያስረዳሉ።
እሳቸው እንደሚሉት ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ባይውልም የፍርድ ሂደቱ ይቀጥላል። ”ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ሕግን ምስክሮች መስማት ይጀምራል። በሌለበት ውሳኔ ይሰጣል። በተጨማሪም ተከሳሹ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ በጠበቃ ሊወከል አይችልም። በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሰረት በእንዲህ አይነት ወንጀል ክስ የተመሰረተበት በውክልና ሊከታተል አይችልም።” ይላሉ።
አቶ ጌታቸው አሰፋን በተመለከተም፤ የወጣባቸው የእስር ትዕዛዝ እና ክስ በመገናኛ ብዙሃን በስፋት ተሰራጭቷል ተብሎ ስለሚታመን ተከሳሹ የፍርድ ቤቱ መጥሪያ ደርሷቸኋላ ብሎ ፍርድ ቤቱ ሊደመድም እንደሚችል የሕግ ባለሙያው ይገልፃሉ።
”የትግራይ ክልል አሳልፎ አይሰጥም”
በሰብዓዊ መብት ጥሰት እና በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸውን ከዚያም ክስ የተመሰረተባቸውን የቀድሞ የስለላ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋን የትግራይ ክልላዊ መንግሥት አሳልፎ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆኑን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከወራት በፊት አሳውቆ ነበር። ይህን ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ብርሃኑ ጸጋዬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመስሪያ ቤታቸውን የአምስት ወራት የሥራ ሪፖርት ይፋ ባደረጉበት ወቅት ነበር።
በወቅቱ የፌደራል መንግሥት ከትግራይ ክልል ፍቃድ እና እውቅና ውጪ ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚያስችለው የሕግ አግባብ አለ? አቶ ጌታቸው አሰፋ በየትኛው የሕግ አግባብ ለፌደራል መንግሥት ተላልፈው ሊሰጡ ይችላሉ? የሚሉ ጥያቄዎችን ለሕግ ባለሙያዎች አቅርበን ነበር።
የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ሥልጣን ለመወሰን በወጣው የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1996 አንቀጽ 4.3 መሠረት የፌደራል ፍርድ ቤቶች በሰው ልጆች መብት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች የዳኝነት ሥልጣን እንዳላቸው ይደነግጋል።
የሕግ ባለሙያው አቶ አዲ ደቀቦ፤ በወንጀል የተጠረጠረው ግለሰብ ማንም ይሁን ማን፤ ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረበት ወንጀል በፌደራል መንግሥት ስልጣን ስር የሚወድቅ እስከሆነ ድረስ፤ የፌደራል መንግሥቱ የማንንም ፍቃድ ሳይጠይቅ ወደ የትኛውም ክልል ሄዶ በወንጀል የተጠረጠረውን ግለሰብ በቁጥጥር ሥር የማዋል ስልጣን አለው ይላሉ።
የፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ከሚኖረው የወንጀል እይነቶች መካከል፤ በሰው ልጆች መብት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ጨምሮ በውጪ ሃገራት መንግሥታት ላይ የሚፈጽሙ ወንጀሎች፣ የበረራ ደህንነትን የሚመለከቱ ወንጀሎች እና የመሳሰሉት በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚታዩ የወንጀል አይነቶች ናቸው።
አቶ አዲ አንደሚሉት አንድ ግለሰብ የፌደራል መንግሥት ሰራተኛ ሳለ ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረበት ወንጀል ካለ፤ የፌደራል መንግሥት የየትኛውንም ክልል ፍቃድም ይሁን ይሁንታ ሳያስፈልገው ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር አውሎ የመመርመር ስልጣን አለው ይላሉ።
• ሜጀር ጄኔራል ክንፈ: ‘‘ቤት የለኝም፣ መኪና የለኝም፣ ንብረት የለኝም፤ ያለኝ ሰውነቴ ብቻ ነው’’
በተመሳሳይ መልኩ ሌላው የሕግ ባለሙያ ሆኑት አቶ ኤፍሬም ታምራት አንድ የክልል መንግሥት በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠረን እና በፌደራል አቃቤ ሕግ ክስ የተመሰረተበትን ግለሰብ አሳልፌ አልሰጥም ቢል፤ ሕገ-ምንግሥቱን፣ የፌደራል የወንጀል ሕጉን፣ የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ሥልጣን ለመወሰን የወጣውን የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅን፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉን እና የፌደራል ፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅን ይተላለፋል ይላሉ።
አቶ ኤፍሬም ሃሳባቸውን ሲዘረዝሩ፤ በሕገ-መንግሥቱ ሦስተኛው ምዕራፍ ላይ በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌዴራል መንግሥትና የክልል ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና የዳኝነት አካሎች የመብቶችና የነፃነቶች ድንጋጌዎችን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለባቸው ተጠቅሷል።
”የማክበር ግዴታ ማለት እራሱ የመንግሥት አካል ወንጀል እንዳይፈጽም መከላከል ሲሆን የማስከበር ማለት ደግሞ ወንጀል የፈጸመውን ግለሰብ የመመርመር እና ሕግ ፊት የማቅረብ ኃላፊነት ማለት ነው” ይላሉ።
አቶ ኤፍሬም የክልሉ ውሳኔ የፌደራል ፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 720/2004 እንዴት እንደሚጻረር ሲያስረዱ፤ አንቀጽ 6 ሥር የተቀመጠውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን ሥልጣን እና ተግባርን በመዘርዘር ያስረዳሉ። አቶ ኤፍሬም እንደሚሉት ከኮሚሽኑ ሥልጣን እና ተግባራት መካከል በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሥልጣን ክልል ስር የሚወድቁ ወንጀሎችን ይከላከላል፤ ይመረምራል።
የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ሥልጣን ለመወሰን የወጣውን የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1996 የፌደራል ፍርድ ቤቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የተፈጸሙ የወንጀል ተግባራትን ማየት የሚችለው የፌደራል ፍርድ ቤት መሆኑን በመጥቀስ ለፌደራል መንግሥት የተሰጠ ስልጣን ክልሎች እንደማይኖራቸው የሕግ ባለሙያው ያስረዳሉ።
የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉም ማንኛውም ዜጋ በተግባሩ ጉዳት እስካልደረሰበት ድረስ፤ በወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብ አሳልፎ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት እንደሚያትት የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው የክልል መንግሥታትም ቢሆኑ ይህን የሕግ ኃላፊነት ከመወጣት ወደኋላ ማለት አይችሉም ይላሉ።
• አቶ ጌታቸው አሰፋ የእስር ትዕዛዝ እንደወጣባቸው ተገለፀ
በወንጀል የሚፈለግን ግለሰብ አሳልፌ አልሰጥም ማለት በራሱ ፍትህን የማስተጓጎል ወንጀል ነው የሚሉት አቶ ኤፍሬም፤ ዛሬ ላይ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠረን ግለሰብ አሳልፌ አልሰጥም የሚል የሕግ አስፈጻሚ አካል፤ ነገ ሰልጣንን ያለ አግባብ በመጠቀም በሚል በወንጀል ሊጠየቅ ይችላል ይላሉ።
ይህን ተግባራዊ ሊያደርግ የሚችለው የየትኛው የፌደራል አካል ነው?
የሕግ ባለሙያው አቶ አዲ ይህ ከወንጀል ምርመራ ጋር የተያያዘ ሰለሆነ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር የማዋል ስልጣኑ የፌደራል ፖሊስ ነው ይላሉ። የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመጣመር ሥራውን ሊያከናውን እንደሚችልም ይጠቁማሉ።
የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ለአቶ ጌታቸው አሰፋ ከለላ ሰጥቷል ለሚለው ክስ እስካሁን ምንም አይነት ይፋዊ ምላሽ አልሰጠም። ነገር ግን ቀደም ብሎ ከሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው እስር ጋር በተያያዘ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳደር የሆኑት ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ክስ እና እስሩን በመኮነን ጠንከር ያለ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።
የቀረቡት ክሶች በአንድ ወገን ላይ ያነጣጠረ መሆኑን አንስተው ”የኛ ሰው ለምን ታሰረ? አንልም።. . . ሁሉም መጠየቅ አለበት” በማለት እርምጃው ፖለቲካዊ አላማን የያዘ መሆኑን ተናገረዋል።
ጨምረውም ክሱ የተለየ ዘመቻ መሆኑንና ማንነታቸውውን በግልጽ ያላስቀመጧቸው ወገኖች እጅ እንዳለበት “ትግራይን ለማዳከም የውጪ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እየታየ ነው፣ በትግራይ ህዝብ ላይ አዲስ ዘመቻ ተጀምሯል” በማለት ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ክስ እና እስሩን ተቃውመውት ነበር።