
ትናንት በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አቅራቢያ በሚገኘው የስብሰባ ማዕከል አዲስ ፓርቲ ለመመስረት ሕዝባዊ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር።
ከዚህ ቀደም አዲሱን ፓርቲ ለመመስረት ሰባት ነባር ፓርቲዎች ተስማምተው እያንዳንዳቸው ራሳቸውን ማክሰማቸው ይታወሳል።
በዚህም አርበኞች ግንቦት7ን ጨምሮ ሰባት ፓርቲዎች ራሳቸውን አክስመው “የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ” ተብሎ የሚጠራ ፓርቲ መስረተዋል። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የዜግነት ፖለቲካ አራምዳለሁ ብሏል።
መስራች ጉባኤው በትናንትናው ውሎው በፓርቲው ደንብ፣ ስያሜ እና አርማ ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
ፓርቲው ዛሬ በሚኖረው ጉባኤው የፓርቲውን ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀመንበር እና ዋና ፀሃፊ እንደሚመርጥ ይጠበቃል።
የአርበኞች ግንቦት 7 ፓርቲ አመራር የነበሩት አቶ ኤፍሬም ማዴቦ እና አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የሌላ ሀገር ዜግነት ስላላቸው በአዲሱ ፓርቲ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ እንደማይኖቸራቸው ተገልጿል።
• “በአንድ ሀገር ውስጥ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ክልሎች ሊኖሩ አይገባም” ፕሮፌ. ብርሃኑ ነጋ
አቶ አንዷለም አራጌ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ከወዳጆቻቸው ጋር ፓርቲ ለመመስረት ያስቡ እንደነበር ጠቅሰው፤ በቀድሞው አርበኞች ግንቦት 7 እና በሰማያዊ ፓርቲ በኩልም ተመሳሳይ ሀሳብ በመኖሩ የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ አባላትን፣ አመራሮችንና ሌሎች ኢትዮጵያውያኖችን ማሰባሰባቸውን ይናገራሉ።
አቶ አንዷለም ከተለያዩ ወገኖች ጋር ላለፉት ስምንት ወራት ምክክር ሲያደርጉ እንደነበር ገልፀዋል።
አቶ አንዷለም እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊ ሀገር እንደመሆኗ፤ በአዲሱ ፓርቲ ሰው በሰውነቱ፣ ለኢትዮጵያ ባለው ራዕይና በአስተሳሰቡ ጥራት የሚመዘንበት በዜግነትን መሰረት ያደረገ ፓርቲ መመስረት ነው ሀሳባቸው።
“አላማችን ኢትዮጵያን የተስፋና የዲሞክራሲ ምድር ማድረግ ነው” ያሉት አቶ አንዷለም፤ ፓርቲው ዘረኝነትን ለመመከትና ሰዎች ሉአላዊ የሚሆኑበትን ስርአት ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
• ”እያሉ” በሌሉበት የተከሰሱት አቶ ጌታቸው አሰፋ
ራሳቸውን አክሰመው አንድ ፓርቲ ለመመስረት የተሰባሰቡት ፓርቲዎች የቀድሞው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የመላ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አርበኞች ግንቦት 7፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ የጋምቤላ ክልላዊ ንቅናቄና አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ናቸው።