የአሜሪካ የደህንነት ቢሮ አንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ የነበረች የበረራ አስተናጋጅ (ሆስተስ) ከሀገሩ አስወጥቷል/deport አርጓል። ( Elias Meseret Taye )

የደረሰኝ መረጃ እንደሚያመለክተው መሰረት ግደይ የተባለችው ሰራተኛ ወደ ኢትዮጵያ እንድትመለስ (deport) የተደረገችው የዛሬ ሳምንት ገደማ ሚያዝያ 24 (May 2) ነበር። አየር መንገዱ ለሰራተኞቹ በለጠፈው ደብዳቤ ሌሎች ሁለት የበረራ አስተናጋጆችም ወደ ጣልያን እና ጀርመን ሄደው በመጥፋታቸው “ለከፍተኛ እንግልት እና ችግር” እንደተዳረጉ ጠቁሞ የካሳ ክስ እንደተመሰረተም ጨምሮ አስታውቋል።
አየር መንገዱ ቀደም ብሎ የካቲት 27 በፃፈው ማሳሰብያ አንዳንድ የበረራ አስተናጋጆች የበረራ ደህንነትን ለአደጋ አጋልጠው በመጥፋታቸው ድርጅቱን ለቅጣት ከመዳረግ ባሻገር እራሳቸውን ለተለያዩ እንግልት እንደዳረጉ ገልፆ ነበር።
በጉዳዩ ዙርያ ያናገርኳቸው የአየር መንገዱ ኮሚኒኬሽን ሀላፊ አቶ አስራት በጋሻው “የአሜሪካ መንግስት ሰራተኛዋን ህገወጥ ነሽ፣ በስራ ላይ እያለሽ ነው የጠፋሽው ብሎ መልሷታል። ሰራተኛዋ በወቅቱ ቪዛ አልነበራትም፣ በዛ ላይ ወደ ካናዳ ልታቋርጥ ስትል ነበር የያዟት።”
አቶ አስራት አክለውም “የሷ ለየት የሚያረገው የበረራ አስተናጋጅነት ስራዋን እየሰራች ነው እዛው የጠፋችው (defect ያረገችው)። ይህ ለመዝናናት ተብሎ ተሄዶ ከሚደረገው መጥፋት ይለያል። ይህ የበረራ ደህንነትን አደጋ ላይ ይጥላል፣ ስለዚህ በስራ ተሁኖ ሊደረግ የማይችል ነገር እንደሆነ በግልፅ ተቀምጧል።”