2019-05-11

አዲሱ ፓርቲ በካባ ላይ ደበሎ!!! ሀይለገብርኤል አያሌው አዲሱ ፖርቲ የተለያዪ ድርጅቶችን ጨፍልቆ አንድ ሆኖ መውጣቱን አብስሯል:: አማራጭ ሆኖ ለመውጣትና የሕዝብን ትግል የመምራት ቁመና እንዲኖረው ሰብሰብ ብሎ መደራጀቱ ወቅታዊም ተገቢም ነው:: ቀደም ሲል ጀምሮ የአዲሱ ፖርቲ መሃንዲሶች ውስጥ  የአሮጌው መስመር መንገደኞች የሴራ ፖለቲካ ኤክስፐርቶችና አድርባይ ኤሊቶች መታየታቸው የፖርቲውን ውልደት ጥያቄ ውስጥ ከቶት ቆይቷል:: በእርግጥ በተጋድሏቸው የተከበሩ ጽናትና ቁርጠኝነታቸው የተመሰከረላቸው ጀግና የሕዝብ ልጆችም የዚሁ ፓርቲ አካል መሆናቸውም አይተናል:: እነሱን አይቶ ሕዝቡ ተስፉ ማድረጉም እርግጥ ነበር:: ካለው ነባራዊ ሁኔታ:: በፖለቲካችን ውስጥ ተፈጠሮ ከቆየው መከፋፈል አንጻር:: ለስልዎቹ ትውልዶች ካለው ሸውራራ አመለካከት አኳያ አዲሱ ፓርቲ የአዲሱን ትውልድ አመራር ይሰይማል ተብሎ ተጠብቆ ነበር:: የብዙዎቻችንም ግምት ያ ነበር:: የሆነው ግን ሌላ ነው:: አዲሱ ፓርቲ ዶር ብርሃኑን መምረጡ ይፋ ሆኗል:: ለለውጥ ናፉቂዎች ለዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኞች ይሄ ምርጫ የምስራች ሳይሆን መርዶ ይመስለኛል:: የአዲሱን ፓርቲ ጉዞ የሚያጨነግፍ ተስፋ እንዳይጣልበትም የሚያደርግ ደንቃራም ነው:: ዶር ብርሃኑ የካበተ ልምድና እውቀት እንዳላቸው አያከራክርም:: የፖለቲካ ስብዕናቸው በድርጅት ውስጥ በቆዩበት ዘመን ከሚተቹበት ኢዲሞክራሲያዊነትና የሴራ አራማጅነት መፈረጃቸው በቀላሉ የማይወጡት ችግር ነው:: ከታጣቂዎች እስከ ሰላማዊ ታጋዮች ከበረሃ እስከ ከተማ ከዘውገኞች እስከ ዜግነት ፖለቲካ አራማጆች ግለሰቡ በአግላይ ጠቅላይነት የሚተቹና በስልጣን ፍቅር የሚታሙ ፖለቲከኛ ናቸው:: ምንም ምርጫው የመስራቾቹ ቢሆንም ብዙ የተደከመበትና ተስፉ የተጣለበት ድርጅት አወዛጋቢ መሪ መምረጡ የድርጅቱን ፈተና ያከብዳል:: በዚህ የዘውግ አስትሳሰብ በናኘበት ወቅት ሃገር በቀውስ በተወጠረችበት ግዜ እንዲህ አይነት የቅቡልነት ችግር ያለበት መሪ መሰየም አስተዋይነት የጎደለውም ውሳኔ ነው:: ቤተመንግስቱ እንኳ በአዲሱ ትውልድ በተያዘበት ዘመን ጠቅላይ ሚንስትሩ ሳይውለድ ትግል የጀመረን ግለሰብ ዛሬ ላይ እንደገና ፊታውራሪ ማድረግ ፓርቲው ማታገያ መሆኑ ቀርቶ ማላገጫ እንዳይሆን ያሰጋል:: በእኔ እምነት ይሄ ፓርቲ በሃገራችን ፖለቲካ ውስጥ ትርጉም ያለው ስራ መስራት የሚችልበት እድል ይኖረው የነበረው በሕዝብ ዘንድ የተሻለ ተዐማኒነት ያለው መሪ ቢሰይም ነበረ:: አሁን ያለንበት ሁኔታ ለፖለቲካ ሃይሎች ከመቼውም ግዜ በላይ ፈታኝ የሆነበት አጋጣሚ ያለ አይመስለኝም:: ይሄን ሁኔታ የተረዳና ሊታመን የሚችል አዲስ የፖለቲካ መሪ ከአዲሱ ትውልድ ማዋለድ ሲገባ በኖረው የፖለቲካ ማጥ ውስጥ የኖረን ግለሰብ መምረጥ ይቅር የማይባል ስህተት ነው:: አንጋፋ ፖለቲከኞች እራሳቸውን ከስልጣን አቅበው አዲሱ ትውልድ መሪ ሆኖ እንዲወጣ  መቼ ነው የሚፈቅዱት:: ከጀርባ ሆኖ ብዙ መስራት ሲቻል በምክር በእውቀትና በምርምር ሊያብረክቱት የሚችሉት ብዙ ነገር እያለ ለመሪነት መሰየማቸው ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን የሚያከራክር አይደለም:: አበው በካባ ላይ ደበሎ እንዲሉ በአዲሱ ትውልድ የነጻነት ትግል ላይ አሮጌ አመራር ማምጣት ጉራማይሌ ብቻ ሳይሆን የትውልዱን ብቃትና ክብር ጥያቄ ውስጥ  የሚጥል የታሪክ ምጸት ነው::  እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይማር!!!! ሀይሌ ገብርኤል Filed in:Amharic