May 11, 2019
Source: https://ethiothinkthank.com

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በተደጋጋሚ አስተዳደራቸው የሕግ የበላይነትን ማስፈን እንደተሳነው ለሚቀርብላቸው ጥያቄ የሚሰጡት ምላሽ እጅግ ግራ የሚያጋባ እና መሰረታዊ የአስተሳሰብ ስህተትም ያለበት ነው። በመጀመሪያ ሕግ ማስከበርን እና ትዕግስትን ምን አገናኛቸው? ተደጋግሞ ለሚቀርብላቸው ጥያቄ ምላሻቸው እንታገስ ብለን ነው፣ ጉልበት አጥተን አይደለም፣ መሳሪያ በእጁ ያለን መንግስት እንዴት ኃይል ተጠቀም ይባላል የሚሉ እና ትላንት በጽ/ቤታቸው አዲስ ወግ በሚል በተዘጋጀው የውይይት መድረክም ላይ አጠንክረው ይሄንኑ አቋማቸውን እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፤ “ከማንም በላይ መንግስት ትዕግስተኛ መሆን አለበት”።ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሕግ ማስከበር እና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ከትዕግስተኝነት ጋር ምን አገናኘው? የትዕግስትዎትስ መለኪያ ምንድን ነው? ሥርዓት አልበኝነቱ ምን ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው የእርሶዎ ትዕግስተኝነት የሚያልቀው እና ሕግ ማስከበር የሚጀምሩት? ይህ መንግስት ሕግ በማስከበር በኩል ያሳየው ዳተኝነት ከሳምንት በፊት በተወካዮች ምክርቤት ቀርቦ በአገሪቱ እየታየ ያለው መፈናቀል፣ ግድያና ዝርፊያ እንዲሁም የመሳሪያ ዝውውር እና ሌሎች የወንጀል አድራጎቶች መበራከት ዋነኛው ምክንያት አስፈጻሚው አካል የተጣለበትን ሕግ የማስከበር እና ሥርዓት የማስፈን ኃላፊነቱን በአግባቡ ስላልተወጣ መሆኑ ጠንከር ባለ ቋንቋ ተገልጾ ፓርላማው ለአስተዳደርዎም ጥብቅ ማሳሰቢያ መስጠቱን ሰምተን ለፓርላማው ወፌ ቆመች ብለናል።
እንደ እኔ እምነት ከሕግ የበላይነት ጋር በተያያዘ ይህ አይነቱ የተዛባ አስተሳሰብ በእርሶ ደረጃ ካለ ሰው ሊመነጭ የሚችለው በሁለት ምክንያቶች ይመስለኛል፤
- አንድም ስለ ሕግ የበላይነት ያለዎት ግንዛቤ የተሳሳተ ነው። ሕግ ማስከበር ማለት አምባገነን ወይም ጨፍላቂ መሆን አይደለም። በሕግ ከተፈቀደው በላይ ኃይል እና ጉልበት መጠቀም እንጂ። መንግስት በሕግ ከተፈቀደው የኃይል እርምጃ በላ እንዲጠቀም የሚያስገድደው ሁኔታ ተፈጥሮ ነገር ግን እራሱብ በሕግ ብቻ ገድቦ ሥርዓት ለማስከበር እየጣረ ቢሆን የትዕግስት ነገር ሊነሳ ይችላል። በሕግ ከተቀመጠው በታች መሆን ደግሞ ትዕግስተኝነት ሳይሆን ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግስ መፍቀድ ነው። እርሶ በትዕግስት የሚጠብቁት ዜጎቸ በፈቃደኝነት ሙሉ በሙሉ ሕግ አክባሪ የሚሆኑበትን ዘመን ከሆነ እሱ መቼም አይመጣም። ጭራሽ የዛሬዎቹ አጥፊዎች ሌሎች አዳዲስ አጥፊዎችን ያበረታቱ ይሆናል እንጂ። ትዕግስትዎ ባለቀ ጊዜም ለመቆጣጠርም አስቸጋሪ ይሆናል። በዚህ እረገድ ያሳዩት ትዕግስት የሕግ አክባሪነትን ሳይሆን የሥርዓት አልበኝነት ባህልም ያሰርጻል። ባንክ ሲዘረፍ፣ የንጹሃን አንገት ሲቀላ፣ በመቶ ሺዎች ሲፈናቀሉ እና በማንነታቸው ሲጠቁ እያዩ የምን ትዕግስት ነው? ትዕግስት ካስፈለገስ መብቱን በአግባቡ ለሚጠይቅ ሕዝብ እንጂ ዜጎችን ለሚያሳድድ እና ባንክ ለሚዘርፍ የተደራጀ ነፍሰ ገዳይ እና ዘራፊ ነው ወይ?
- ሌላው ምክንያት ግን ከውስጥዎ ትንሽም ብትሆን የምትተናነቅዎት የአንባገነናዊ ስሜት ካለች እንዲህ እንዲያስቡ ልታስገድድዎት ትችላለች። ትዕግስት በሚለው ምሰጣዊ ንግግርዎት ጀርባ የትዕግስት ተቃራኒ የሆነው ጨፍላቂና አፋኝነትም ጎልቶ ይታያል። ይህንንም በገደምዳሜ በተለያዩ መድረኮች እና በትላንቱ ንግግርዎም ጠቆም አድርገውናል። መንግስት አቅም አለው፤ ልዩ ኃይልም በውጭ አገሮች ድጋፍ ጭምር እያሰለጠነ ነው የሚሉ እና ሌሎች ጥቆማዎችን ሰጥተውናል። ትዕግስትዎ ክርንዎ እስኪፈረጥም ከሆነ እሱም ጥሩ አይደለም። ሥርዓት አልበኝነት እና የፈረጠመ የመንግስት ጡንቻ ሲገናኙ መጨረሻው ግልጽ ነው። እሱን መንገድ ደግሞ እስኪያንገሸግሸን ስላየነው የምንጓጋለት አይደለም።
በዚሁ መድረክ ላይ መንግስት እርምጃ መውሰድ በፈለገ ጊዜ የሚሳነው ነገር እንደሌለ ገልጸው ጭራሽ ስላቅ በሚመስል አኳኋን አገሪቱ የሕግ የበላይነትን በማስከበር እረገድ የገጠማት ችግር በሚመከርበት መድረክ እርሶ መንገድ እናጽዳ የሚል የመፍትሔ ሃሳብ ማቅረብዎ አንድም ችግሩን ከቁጥጥሬ አይወጣም በሚል ስሜት ማቃለልዎት አለያም የውይይት አቅጣጫ ለማስሳቀየስ የተናገሩት ነው የሚመስለው።
አሁንም ደጋግመን የሕግ የበላይነት ይከበር ስንል አንባገነን ሁኑ ወይም የማይገባ እና ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃ ውሰዱ እያልን አይደለም። አጥፊዎች በሕግ አግባብ በወቅቱ ይቀጡ፣ መንግስት ያለውን ሰፊ መዋቅር ተጠቅሞ የቅድመ አደጋዎች እና ግጭቶች የመከላከያ እቅድ ነድፎ ይንቀሳቀስ፣ አደጋዎች መኖራቸው ሲገለጽ ዳር ቆማችሁ ይለይለት በሚመስል መንገድ ስትመለከቱ ከቆያችው በኋላ ተጎጂዎችን ማጽናናት እና ለቅሶ መድረስ ጥቅም የለውም። መንግስት የዜጎችን ደህንነት እና መብት የመጠበቅ እና የማስጠበቅ ግዴታውን ማክበር አለበት። ሕግ ሲጣስ ትዕግስተኛ መሆነ ግን ለጊዜው ወንበራችሁን ባይነቀንቀውም ሕዝቡን ግን የህይወት እና የንብረት ዋጋ እያስከፈለው መሆኑ ልታጤኑት ይገባል።
አሁንም የሕግ የበላይነት ይከበር!